ጌታቸው ረዳ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጥሪ ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ ተናገሩ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ ፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ቀውስ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ ያቀረቡት ሕጋዊ ጥያቄ እንደሌለ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። በሕገመንግሥቱ መሠረት የፌደራል መንግሥት በክልሎች ጣልቃ እንዲገባ መጠየቅ የሚችለው በምርጫ የተቋቋመ ምክር ቤት መኾኑን የጠቀሱት ጌታቸው፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ግን የፌደራል መንግሥቱ አካል እንደኾነ ተናግረዋል። ጌታቸው፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የጠየቀው ፌደሬል መንግሥቱ ከኃይል ርምጃ ውጭ ችግር ፈጣሪውን ቡድን አደብ እንዲያስገዛ ብቻ መኾኑን ጠቅሰዋል። ችግር ፈጣሪው ቡድን የርዕሰ መስተዳደርነት ሥልጣን ለመቀበል ሲል ከፌደራል መንግሥት ጋር ለመደራደር ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ይችላሉ ያሉት ጌታቸው፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ “ለራሱ የግልና የቡድን ጥቅም ሲል የሕዝብን ሠላም፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነትና የአገሪቱን መረጋጋት እንደ መያዣ ከተጠቀመ አካል” ጋር እንዳይደራደሩ ጠይቀዋል። ትግራይ ውስጥ ከሚፈጠረው ትርምስ እናተርፋለን ብለው ከሚጠብቁት ኃይሎች መካከል፣ አንዱ የኤርትራ መንግሥት መኾኑንም ጌታቸው ጠቁመዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጥሪ ወደ አዲስ አበባ እንደመጡና፣ በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ ወደ ትግራይ እንደሚመለሱ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። ጌታቸው፣ የሰሜን ምሥራቅ እና ማዕከላዊ ትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ቁጥጥር ውጭ እንደወጡ ተናግረዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የሕወሓት ክንፍ ለመቀሌ ከተማ ከንቲባነት የሾማቸው ረዳኢ በርሄ ለሦስት ወራት በውዝግብ ተዘግቶ የቆየውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተረክበው ሥራ ጀምረዋል። የደብረጺዮን ቡድን መቀሌ የሚገኘውን መንግሥታዊውን የኤፍኤም ሬዲዮ መቆጣጠሩም ተገልጧል።