ሰራዊታችንን በመበተን የትግራይ ህዝብን ለከፋ አደጋ ማጋለጥ አይቻልም! ( የደብረፂዮን ሕወሓት የሰጠው መግለጫ)
የትግራይ ሰራዊት የመከተ ትግሉ የሰላ-ጫፍ ሆኖ የትግራይ ህዝብን ከጠቅላላ ጆኖሳይድ ለማዳን በከፈለው መስዋእትነት ለዘልአለሙ የማይረሳ ወርቃማ ታሪክ ያስመዘገበ ህዝባዊ ሃይል ነው፡፡ ሰራዊታችን ለህዝቡ የከፈለው እጅግ ከባድ መስዋእትነት በቃላት መግለፅ ኣይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ ሰራዊታችን ከባድ መስዋእትነት ከፍሎ በፈጠረው ዕድል ወደ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መግባታችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ይኸንን የመከታ ትግላችን የሰላ-ጫፍ ሃይል የሆነውን ሃይል ሳይዙ የሚረጋገጥ የህዝባችን ደህንነትና ሰላም እንደዚሁም ብሄራዊ ጥቅም ሊኖር አይችልም፡፡ በድምር ሰራዊታችን ትላንትም ሆነ ዛሬ የትግራይ ህዝብ ሰላም፣ ህልውናና ደህንነት ዋስ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ልክ ህወሓትን ከውስጥም ከውጭም ለማፍረስ ሲደረግ እንደነበረው እንቅስቃሴ፣ ሰራዊታችንም ተሰላችቶና ተስፋ ቆርጦ እንዲበተን ከውስጥና ከውጭ የተቀናጀ ሴራ ሲሰራ ቆይቷል፣ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ይኸንን ሴራ በሚገባ የተገነዘበው የትግራይ ሰራዊት ደግሞ የትግራይ ህዝብን ብሄራዊ ጥቅም አጥብቆ በመያዝና ሁሉም ዓይነት ፈተናዎችን በመቋቋም፣ ትግራይ ውስጥ ያጋጠሙ ፖለቲካዊ ችግሮች በህገመንግስታዊ ስርዓቱና በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር ኣግባብ እንዲፈቱ በትጋት እየታገለ ቆይቷል፡፡ ሰራዊቱ የተሰዉ ጓዶቹ አደራ በመጠበቅ ያጋጠሙትን ሁሉም ዓይነት ሴራዎች በሆደ ሰፊነትና በትዕግስት እየታገለ ቢሆንም ስሙን በማጥላላትና ጥላሸት በመቀባት ከህዝቡ እንዲነጠልና እንዲበተን ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም፡፡
ድርጅታችን፣ ሰራዊቱና ህዝቡ “የተወሰኑ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ኣመራሮች ከተልዕኳቸው ወጥተው የውጪ ሃይሎች መሳሪያ በመሆን የትግራይ ህዝብን ብሄራዊ ጥቅም ኣሰልፈው እየሰጡ ነው፣ እንደዚሁም የትግራይ ሕገ-መንግስትን በመጣስ በክልሉ ህግና ስርዓትን በማፍረስ ማቆሚያ የሌለው ኣደገኛ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው” የሚል ተጨባጭ ግምገማና ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ይታወቃል፡፡ ይኸንን የጋራ ድምዳሜ መሰረት በማድረግ ህግና ስርዓትን ለማስክበር የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማምከን በሰራዊቱና በአመራሩ ላይ ያነጣጠረ ስም ማጥፋትና ማጥላላት፣ እንደዚሁም ማስፈራራት በተለያዩ ሚዲያዎች በተቀናጀ መንገድ ሲነዛ ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ ሰራዊቱ ያለ መሪ በማስቀረት አደረጃጀቱን ለመበተንና ህዝባችንን ለከፋ አደጋ ለማጋለጥ ያለመ በጀግኖች የሰራዊቱ አመራሮች ላይ ያነጣጠሩ በእገዳና ከሃላፊነት የማንሳት ስም ግልፅ ብሄራዊ ክህደት ተፈፅሟል፡፡
ይሁን እንጂ ሰራዊቱ ይሁን አመራሩ በአንድ ግለሰብ ፈቃድ የሚታገድና የሚባረር ሳይሆን ለህዝባችን ብሄራዊ ጥቅምና ህልውና ግንባሩን የሚሰጥ ህዝባዊ የመከተ ሃይል ነው፡፡ ይኸንን ህዝባዊ ሃይል ማንም ግለሰብ እየተነሳ እንደፍላጎቱ እንዲታገል የሚያደርገው፣ የሚያግደው ወይም የሚያባርረው ኣይደለም፡፡ ስለሆነም አራት የሰራዊቱ ከፍተኛ ኣመራሮች ለማገድና ለማባረር በትግራይ ግዚያዊ ኣስተዳደር የቀድሞው ፕሬዚዳንት ተፈርሞ የተፃፈው ደብዳቤ ከሃላፊነት ውጪ የተደረገና ተፈፃሚነት የሌለው መሆኑ ኣሁንም በግልፅ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከስልጣን ውጭ የተፃፉት ደብዳቤዎች የያዙት ዓላማ ደግሞ እጅግ አደገኛ በመሆኑ በፅኑ የምንታገለው ይሆናል፡፡ ክልላዊ፣ አገራዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች እጅግ በተወሳሰቡበት በአሁኑ ወቅት ሃላፊነት በጎደለው መንገድ ሰራዊቱን ያለ አመራር በማስቀረት ህዝባችንን ለከፋ የህልውና አደጋ ለማጋለጥ ያለመ ሆን ተብሎ የተፈፀመ አደገኛ ስራ መሆኑ ህዝቡና ሰራዊቱ ሊገነዘበው ይገባል፡፡
ህወሓትና የትግራይ ሰራዊት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እና የግዚያዊ ኣስተዳደሩ ዋና ባለቤቶች ናቸው፡፡ ትግራይ ውስጥ የተጀመረው ህግና ስርዓት የማስከበር ስራ ደግሞ ግዚያዊ አስተዳደሩና የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የሚያፈርስ ሳይሆን የተጀመረውን የሰላም ስምምነት ትግበራ ይበልጥ የሚያጠናክር፣ የትግራይ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት የሚያስከብር፣ የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ፣ በትግራይ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ የሚያሰፍን እና ብሄራዊ ጥቅሞቻችን ለማስጠበቅ የሚያስችል ነው፡፡ ይሁን እንጂ የክህደት ቡድኑ ሃላፊነት የጎደለው ስራውን ኣጠናክሮ በመቀጠል ህወሓትና የትግራይ ሰራዊትን ጥላሸት በመቀባትና በመወንጀል “ትግራይ ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችል” በመግለፅ እያደናገረ ሶስተኛ ወገን ወደ ትግራይ እንዲገባ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ጥሪ እያደረገ ነው፡፡
ከዚህ በመነሳት በእግድ ስም የተፃፉት ደብዳቤዎች ከስልጣን ውጪ የተደረጉ፣ ተቀባይነትና ተፈፃሚነት የሌላቸው መሆናቸውን እየገለፅን፣ ትግራይ ውስጥ ያጋጠሙት ችግሮች ለመፍታት የህወሓት፣ የህዝቡና የሰራዊቱ ውሳኔዎች መተግበር አማራጭ የሌለው መሆኑን እናሳውቃለን፡፡ በተጨማሪም ትግራይ ውስጥ በፀጥታ ሃይሉ የተጀመረው ሕገ-መንግስትንና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የሚያከብር እንጂ የሚያፈርስ እንዳልሆነ እናረጋግጣለን፡፡ ሰራዊታችንና አመራሩ እንደዚሁም ህወሓት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እውን እንዲሆነ ከባድ መስዋእትነት የከፈሉ እና በአሁኑ ወቅትም ለተግባራዊነቱ በፅናት እየሰሩ ያሉ ፅኑ የሰላም ሃይሎች ናቸው፡፡ ህወሓት፣ የትግራይ ህዝብና ሰራዊቱ ግዚያዊ ኣስተዳደሩ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣ የአመራር ማስተካከያ እንዲደረግ ጠየቁ እንጂ ግዚያዊ ኣስተዳደሩ ይፍረስ ኣላሉም፡፡ ስለሆነም የክህደት ቡድኑ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሶስተኛ ወገን ትግራይ ውስጥ እጁን እንዲያስገባ የሚያደርገው ጥሪ ግልፅ ብሄራዊ ክህደት እና የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት አደጋ ውስጥ የሚከት በመሆኑ በፍፁም ተቀባይነት የለዉም፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስትና የዓለም ማህበረሰብ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በሙሉነትና በፍጥነት በመተግበር ወደ ዘላቂ ሰላምና መልሶ መቋቋም በሚወስድ መንገድ አወንታዊ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እያቀረብን፣ መላው ህዝባችን ትግራይ ውስጥ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ለማስከበር፣ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ፣ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን በሚደረጉ ስራዎች እንደተለመደው ወሳኙን ድርሻ እንዲጫወት እናስታውሳለን፡፡
ክብርና ሞገስ ለተሰዉ ሰማእታት!
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)
03 መጋቢት 2017 ዓ.ም
መቐለ