እንደ ሃጫሉ ሞትም ተድበስብሶ እዳይቀርብኝ፤ ልጄ እርኩስ መንፈስ የለባትም፤ የልጄን እውነት አፈላልጉኝ የሟች ወጣቷ ቀነኒ አባት

” የልጄን እውነት አፈላልጉኝ ! … የፍትህ አካላት ተከታትለው የልጄን ሀቋን ያውጣልኝ ፤ ደሟን ያወጣልኝ ” – አባት አቶ አዱኛ ዋቆ

የወጣቷ ቀነኒ አዱኛ ስርዓተ ቀብር ዛሬ በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

ለጋዋ ወጣት ቀነኒ ከፍቅረኛዋ ድምጻዊ አንዱዓለም ጎሳ ጋር ከሚኖሩበት መኖሪያ ቤት ለሊት 10 ሰዓት ግድም ከ5ኛ ፎቅ ወለል ወድቃ ሕይወቷ እንዳለፈ መነገሩ ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ቀነኒ አዱኛ ከቤቷ የማብሰያ ክፍል በኩል ካለው በረንዳ 5ኛ ፎቅ ላይ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ወድቃ ለህክምና እርዳታ እየተወሰደች ባለበት ወቅት ህይወቷ እንዳለፈ ገልጿል።

በወቅቱ አብሯት የነበረውን ድምጻዊ አንዱዓለም ጎሳን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያከናወነ እንደሆነ አስረድቷል።

ዛሬ በቅድስት ሥላሴ በተፈጸመው ስርዓተ ቀብሯ ላይ ፍቅረኛዋ አርቲስት አንዱኣለም ጎሳ በፖሊሶች በመታጀብ ተገኝቶ እርሙን በማውጣት ስርዓተ ቀብሯ ላይ ተገኝቷል፡፡

የቀብር ስነስርዓት ከተፈጸመ በኋላ አባት አቶ አዱኛ ዋቆ ለቀስተኞች ፊት ባስተላለፉት መልእክታቸው የልጃቸውን ፍትህ በእጅጉ እንደሚሹ አሳውቀዋል፡፡

” ሁላችሁንም የምጠይቃችሁ፤ አርቲስቶቻችንም ለናንተ የማስተላልፈው መልእክት የልጄን እውነት አፈላልጉኝ፡፡ እንደ ሃጫሉ ሞትም ተድበስብሶ እዳይቀርብኝ ” ብለዋል

” እኔ ለማስተማር ነበር ከእቅፌ ያወጧሃት እንጂ እንዲህ እንድትቀጠፍብኝ አልነበረም፡፡ ሌላ የምለውም የለም ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አባት አቶ አዱኛ ዋቆ  ” እኔ ቀነኒን የማውቃት እጅግ ታታሪ፣ ስራን የምትፈጥር፣ ደግሞም ሥራ አክባሪ ናት፡፡ እንዲህ እርኩስ መንፈስ ይዟት እራሷን ታጠፋለች የሚለውን ውሸት ነው የምለው፡፡ እሷ ሲቸግርህ ተበድራ እንኳ የምትሰጥ እንጂ ከሷ ይህ አይጠበቅም ” በማለት በልጃቸው ኅልፈት መሪር ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

” እኔ አሁንም ቢሆን የፍትህ አካላት ተከታትለው፤ ሀቋን ያውጣልኝ ነው ፤ ደሟን ያወጣልኝ ነው ሌላ ምንም የምለው የለኝም ” ብለዋል፡፡ 

ለጋዋ ወጣት ቀነኒ አዱኛ ዛሬ ከአባቷ አቶ አዱኛ ዋቆ እና እናቷ አስቴር መኮንን መጋቢት 07 ቀን 1991 ዓ.ም. ነው የተወለደችው።

የፊታችን ቅዳሜም 26ኛ ዓመት ልደቷን ለማክበር ስትዘጋጅም ነበር።