ምርታቸውን ለወረዳው ከሸጡ በኋላ ለ2 ወራት ክፍያ ያልተፈጸመላቸው አርሶአደሮች ቅሬታ!
🟢 ” ለፍተን፣ ደክመን ያገኘነውን ምርት ወረዳው ቀምቶናል፣ አርሷደሮች ናቸው አያቁም ብለው ሸውደውናል፣ ቤተሰቦቻችን ችግር ላይ ወድቀዋል ” የደቦና ሰነን አርሶአደሮች
🟢 ” በአርሶአደሮቹ አካውንት እስከ 6 ሚሊየን ብር ገደማ ገቢ ተደርጓል፣ ነገር ግን ለአከፋፈል ስላልተመቸን አልተሰጣቸውም ” የደቦና ሰነን ቀበሌ አስተዳዳሪ
በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ የደቦና ሰነን ቀበሌ አርሶአደሮች በባለፈው አመት ከወረዳው የገብስ ዘር በብድር መልክ ወስደው ሰብሉ ሲደርስ የወሰዱትን እንዲመልሱ እና ከዘሩ የተረፈውን ምርት ባለው የገበያ ዋጋ ላይ 15 በመቶ ጨምሮ እንደሚገዛቸው ይነገራቸዋል።
በዚህም በብድር መልክ የወሰዱትን የገብስ ዘር ካመረቱት ምርት ላይ በመመለስ የተረፈውን ምርት በስምምነታቸው መሰረት ለወረዳው መሸጣቸውን ይገልጻሉ።
ታዲያ ወረዳው የሸጡበትን ገንዘብ ሳይሰጣቸው ሁለት ወር ገደማ አካባቢ በማለፉ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን አርሶአደሮቹ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታ አቅርበዋል።
በዚህ የተነሳም አሁን ላይ ድንች ለመትከል ዘር የሚገዙት ቋሚ ንብረታቸውን እየሸጡ መሆኑን በመግለጽ አልፎም የ2017/18 የምርት ዘመን በመድረሱ ለአፈር መዳበሪያ መግዣ መቸገራቸውን ተናግረዋል።
የደቦና ሰነን ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ታፈሰ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደገለጹት በዚህ ስምምነት 200 አርሶአደሮች ተሳትፈዋል ያሉ ሲሆን እስከ 6 ሚሊየን ብር ገደማ ገቢ ተደርጓል፤ ነገር ግን ለአከፋፈል ስላልተመቸን አልተሰጣቸውም ሲሉ ተናግረዋል።
አርሶአደሮቹ በዝርዝር ምን አሉ ?
የቀበሌው ነዋሪ የሆኑ ስማቸወን እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ አርሶአደር የገብስ ዘሩ ሲሰጣቸው መሸጥ የምንፈልገውን በጥሩ ዋጋ ሊገዙን ተነጋግረን ስለነበር ነው የሰጠናቸው ብለዋል።
ሆኖም ገንዘባችን ስላልደረሰን በማናውቀው ነገር ቤተሰቦቻችንን ችግር ላይ ጥለውብናል ሲሉ ያስረዳሉ። የልጆች አባት መሆናቸውን የገለጹልን እኚሁ አርሶአደር “ያመረትኩትን ገብስ ሁሉ ማጥቀሻ (ለቁርስ) ሳላስቀር ነው የወሰዱት” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም በተደጋጋሚ ወረዳውን መጠየቃቸውን እስተው በየጊዜው ቀጠሮ ከመስጠት በዘለለ መፍትሔ አለማግኘታቸውን ጠቅሰው የተወሰነ ገንዘብ እንስጣችሁ የሚሉ ማታለያዎችን ጭምር እየተጠቀሙ መሆኑን ጠቁመዋል።
ስምምነት የወሰዳቹሁበት ውል ነበራችሁ ? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄም “እኛ ምንም አይነት ውል የለንም፣ የመሬት ካርታችሁን አምጡ አሉን ሰጠን፣ ሰብሉ ሲደርስም መኪና ይዘው መጡ እየመዘናቹህ መኪናው ላይ ስቀሉ የሚል አጭር ትዕዛዝ ሰጡን፤ ገንዘባችንስ ስንላቸው ነገ ይሰጣችኋል ሲሉ ነገሩን፣ የገበሬ ነገር ምን እናውቃለን ሁሉንም እሽ አልን” በማለት ይገልፃሉ።
ሌለኛው አርሶአደር ደግሞ ያመረቱትን ሰብል በሙሉ እንደተወሰደባቸው እና ምርቱን ሲጭኑ የቀበሌው ግብርና ባለሙያዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በሰዓቱም 100 ኪሎውን ምርት በ8510 ብር እንደሚገዟቸው እንደነገሯቸው ገልፀው አሁን ግን ገንዘቡን ሳይሰጧቸው ሁለት ወር ገደማ መቆየቱን አስረድተዋል።
ችግር ላይ መሆናቸውን ያነሱት አርሶአደሩ፤ ስለሁኔታው የሚያናግሩት በማጣታቸው “በጉልበታችን ለፍተን ያገኘነውን ንብረት አልተማሩም ብለው ሸውደውናል” ሲሉ ችግራቸውን በምሬት ገልጸዋል።
አርሶአደሮቹ አክለውም የተሰጣቸው የገብስ ዘር ደጋማ መሆኑንና አካባቢው አፈር ጋር አለመስማማቱን በማንሳት ምርቱን ማምረት የቻሉት በብዙ ልፋታና ድካም መሆኑን ጠቅሰው ወረዳውን የልፋታችንን ወስዶብናል ሲሉ ከሰዋል።
የደቦና ሰነን ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ታፈሰ በጉዳዩ ላይ ምን አሉ?
ከ200 በላይ የሚሆኑ አርሷደሮች የመሬት ካርታቸውን አሲዘው ውል ገብተው የገብስ ዘሩን መውሰዳቸውን አስተዳዳሪው አንስተዋል።
በውሉ ወቅትም ከሚያመርቱት ምርት ላይ ምንም ማስቀረት እንደማይችሉ እና የተሰጣቸውን መልሰው የተረፋቸውን ባለው የገበያ ዋጋ ላይ 15 በመቶ ጨምረው እንደሚገዟቸው ተነግሯቸው መስማማታቸውንም ገልጸዋል።
አርሷደሮቹ ያመረቱትን ምርት ምንም ሳያስቀሩ መስጠታቸውን የመሰከሩት አቶ ታፈሰ፥ በወቅቱም ገንዘባቸውን ለመስጠት ከቀበሌው 21 አርሷደሮች ተመርጠው የባንክ አካውንታቸው ተወስዶ እንደነበር አስታውሰዋል።
የተጫነው ምርት በብር ከ8 ሚሊየን በላይ ነው ሲሉ ያስረዱት አስተዳዳሪው “እስካሁን ባለኝ መረጃ በአርሷደሮቹ አካውንት እስከ 6 ሚሊየን ብር ገደማ ገቢ ተደርጓል፣ ነገር ግን ለአከፋፈል ስላልተመቸን አልተሰጣቸውም ” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለው፥ “በተደጋጋሚ ወረዳውን ጠይቀናል እስካሁን ግን ከቀጠሮ የዘለለ የለም። በመሆኑም በቀበሌው መሰብሰብ የነበረብንን ግብር መሰብሰብ አልቻልንም፣ ገበሬዎችም ማዳበራሪያ መግዣቸው በመሆኑ ችግር ላይ ናቸው” ሲሉ ተናግረው ይህም በቀበሌው ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥሮብናል ብለዋል።
የጉመር ወረዳ አመራር ምላሽ
ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉትን የጉመር ወረዳ አመራሮችን በስልክ አግኝተን በጉዳዩ ዙሪያ ለማናገር በተደጋጋሚ ብንሞክርም “ጉዳዩ ላይ እኔን አይመለከትም” በሚል ተደጋጋሚ ምክንያት ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም።
በመሆኑም ከወረዳው የሚመለከተውን አካል ለማናገር ያደረግነው ጥረትም ሳይሳካ በመቅረቱ ምላሻቸውን ሳይካተት ቀርቷል።