የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ ላይ የእግድ ደብዳቤ ፅፈዋል።
የእግድ ደብዳቤው ዘላቂና ጥቅማ ጥቅም እስከማስቀረት የዘለቀ እንደሆነ በፃፉት ደብዳቤ ለሚመለከታቸው አካላት በግልባጭ አስታውቀዋል።
ፕሬዜዳንቱ ትናንት በሦስት ከፍተኛ የሰራዊት አመራሮች ላይ ጊዚያዊ የእግድ ደብዳቤ መፃፋቸው ይታወሳል።
ዛሬ ” ኋላፊነታቸው በአግባቡ አልተወጡም ” ያሉዋቸውን የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ ላይ ሙሉ የእግድ ደብዳቤ ፅፈዋል።
የእግድ ደብዳቤው የተፃፈላቸው ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ ከዛሬ መጋቢት 2/2017 ዓ.ም ጀምሮ ከማንኛውም መንግስታዊ ጥቅም በመራቅ ማንኛውም የፀጥታ አካል እንዳያዙ እግድ ተላልፎባቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መጋቢት 1/2017 ዓ.ም ህግና ስርዓት እንዲጣስ ውሳነ በመስጠትና በማሰማራት ተሳትፈዋል በተባሉ ሦስት ከፍተኛ የሰራዊት አመራሮች ከተወሰደው ጊዚያዊ የእግድ ትእዛዝ በኋላ በዓዲግራት እና በዓዲጉዲም ከተሞች በታጠቁ ኃይሎች የታገዘ መፈንቀለ ስልጣን ተካሂደዋል። መቐለም ሙከራዎች ነበሩ።
በዓዲግራት የተካሄደው በሰራዊት የታገዘ መፈንቅለ ስልጣን ያለ ግጭት የተካሄደ ሲሆን በዓዲጉዲም ከተማ ታጣቂዎች በወሰዱት እርምጃ የከተማው በርካታ ሰዎች የአካል ጥቃት ሰለባ እንደሆኑ ተነግሯል።
በዓዲጉዲም ከተማ የአካል ጉዳት የደረሰ ቢሆንም የሞተ ሰው ስለመኖሩ ማረጋገጥ አልተቻለም።
አንዳንድ መረጃዎች የዓዲጉዶም ከንቲባ የሚገኙባቸው 9 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ ቢያመላክቱም ከሚመለከታቸው አካላት በኩል ማረጋገጫ ማግኘት አልተቻለም።
የዓዲግራት ከተማ አስተዳደር ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ ፤ የደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ህወሓት ባሰማራቸው የሰራዊት አባላት የከንቲባ ፅህፈት ቤት በመስበር መፈንቅለ ስልጣን ተካሂዷል ብሏል።
” በጠበንጃ የሚፀና ስልጣን የለም ” በማለት ወጣቱ መብቱ ለማስከበር እንዲታገል አሳስቧል።
በመቐለ ፣ በዓዲጉዶምና በዓዲግራት ከተሞች ” የሰራዊት ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ” ደብረፅዮ (ዶ/ር) የሚመሩትን የህወሓት ቡድን የሚኮንኑ ሰላማዊ ሰልፎች ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው።