የኤርትራ መንግሥት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌትናንት ጀኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ የጦርነት ሰባቂነት አጀንዳ አቀንቃኝ ናቸው በማለት በቃል አቀባዩ የማነ ገብረመስቀል በኩል ከሷል። ጀኔራል ጻድቃን ሁለቱ አገሮች ጦርነት ውስጥ ለመግባት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል ማለታቸው፣ የጦርነት አጀንዳ አራማጅነታቸውን ያሳያል በማለት የማነ ወንጅለዋል። ጀኔራል ጻድቃን ኢትዮጵያ አሰብ ወደብን በኃይል መያዝ አለባት የሚል አቋም ከድሮ ጀምሮ በማንጸባረቅ ይታወቁ ነበር ያሉት የማነ፣ አኹን ግን የሰላም አቀንቃኝ መስለው መታየት ይፈልጋሉ በማለት ተችተዋል። የማነ ይህን ትችት የሠነዘሩት፣ ጀኔራል ጻድቃን በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ጦርነት መቀስቀሱ አይቀሬ መኾኑን ሰሞኑን በጻፉት ጽሁፍ ካስጠነቀቁ በኋላ ነው።