የትግራይ ወታደራዊ አዛዦች በመቀሌና አዲጉዶም ከተሞች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በመተኮስ በርካቶች ላይ ጉዳት አድርሰዋል – ጌታቸው ረዳ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ ከሕገወጡ የሕወሓት አንጃ ጋር የወገኑ የትግራይ ወታደራዊ አዛዦች በመቀሌና አዲጉዶም ከተሞች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በመተኮስ በርካቶች ላይ ጉዳት አድርሰዋል በማለት ትናንት ምሽት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ከሰዋል።

ጌታቸው፣ ወታደራዊ አዛዦቹ የጊዜያዊ አስተዳደሩን መዋቅሮች ለማፈራረስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የተቃወሙ ሰላማዊ ሰዎችን ስብስበው በማሠር ተጠምደዋል በማለትም ወንጅለዋል።

የወታደራዊ አዛዦቹ ዓላማ ሕገወጡን ቡድን ወደ ሥልጣን ማምጣት መኾኑን የጠቀሱት ጌታቸው፣ ድርጊቱ ትግራይን ወደ ከባድ አረንቋ እያስገባት ይገኛል ብለዋል።

የውጭ ኃይሎች ተጨማሪ ግጭት ለመፍጠር ቀውሱን እየተጠቀሙበት እንደኾነም ጌታቸው ጠቅሰዋል።