በጠራራ ፀሐይ የሚፈፀም አስገዳጅ የፓርቲ ዝርፊያ በቸልታ የሚታለፍ አይደለም፤ በግልጽ እምቢ ሊባልም ይገባል!
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የመንግሥት እና ፓርቲ አለመለያየት ለሀገራችን ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዋንኛው እንቅፋት መሆኑን ደጋግሞ ለማስረዳት ሞክሯል፤ በተግባርም ድርጅቱን ሲያዋቅር ይህን ታሳቢ በማድረግ የድርጅት እና የመንግሥት ክንፎችን ለይቶ እምነቱን በተግባር ማሳየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በተቃራኒው ብልፅግና ፓርቲ በተደጋጋሚ መንግሥት እና ፓርቲ መለየት ሲሳነው ባስተዋልንባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ደጋግመን አሳስበናል፡፡ ነገር ግን ፓርቲው ከዚህ ስህተቱ ከመታረም ይልቅ ከጊዜ ወደጊዜ እየባሰበት መሆኑን ስናይ ሆነ ተብሎና ታስቦበት በማወቅ የሚፈፀም ታቅዶ የሚከናወን ሥራ ነው እንድንል አድርጎናል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ባለፈው ጥር ወር ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው ካሳለፋቸው ውሣኔዎች አንዱ “ፓርቲውን ማጠናከር” የሚል ውሳኔ ይገኝበታል፡፡ ይህንኑ ውሳኔ መሠረት በማድረግ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጉዳያቸውን ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ ዜጎቸ በውድም ሆነ በግድ የፓርቲ ማጠናከሪያ ገንዘብ እንዲያዋጡ እየተደረገ እንደሆነ ካሰባሰብናቸው ማስረጃዎች ለማወቅ ችለናል፡፡ ከፓርቲ አባላት ውጭ ያሉ ዜጎች ብልፅግናን ፓርቲ ጨምሮ ለየትኛውም ድርጅት በፈቃደኝነት የፈለጉትን ድጋፍ ማድረግ መብታቸው እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ እንዲሁም ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ዜጎች ሃሳባችንን ይወክሉልናል ለሚሏቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለምንም ፍርሃት መደገፍ እንዳለባቸውም እምነታችን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዜጎች አገልግሎት ለማግኘት በሚሄዱባቸው የመንግሥታዊ ተቋማት ይህን ተግባር መፈፀም በፍፁም ሕገወጥ ተግባር ነው፡፡
በመሠረቱ ብልፅግና ፓርቲ 17 ሚሊዮን በላይ አባላት አሉኝ” ሲል በአደባባይ ቢሰማም ለፓርቲው ማጠናከሪያ አሉኝ ክሚላቸው አባላት ማሰባሰብ ሲገባው አባል ካልሆኑ ዜጎች በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ጋር አያይዞ መዋጮ ማሰባሰብ ምንም ዓይነት የሕግም ሆነ የሞራል መሠረት የለውም። ብልጽግና ይህንን ዓይነት አሳፋሪ ተግባር የሚፈፅሙ አባላቱንም ቆጥሮ ከሆነ “በአባላት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ሁለተኛ ሆኛለሁ” የሚለው መዋቅሩን በድጋሚ ሊያጤነው ይገባል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ዋና ዋና የሚባሉት የፓርቲው አባላት በመንግሥት መዋቅር በሹመት ግፋ ሲል ደግሞ በዴሞክራሲ ተቋማት ማስተባበሪያ በሚል የሙሉ ጊዜ የአንድን ፓርቲ የፖለቲካ ሥራ የሚሠሩት ሁሉ ከሕዝብ ከሚሰበሰብ ታክስ ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም የሚተዳደሩ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር በሆነበት ሀገር አሁን ደግሞ አባል ያልሆኑ ዜጎችን ጭምር ለአገልግሎት ወደ ማንኛውም መንግሥታዊ ተቋማት ሲሄዱ የፓርቲ መዋጮ መሰብሰብ የመንግሥት መዋቅርን ለአንድ ፓርቲ አገልግሎት መጠቀም መሆኑን አለመረዳት ሳይሆን የማናለብኝነት ስሜቱ የት እንደደረሰ እንደማሳያ የምንወስደው ነው፡፡
በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ይኑር የሚል ቁርጠኛ አቋም አለኝ የሚል ፓርቲ እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ ተግባር ውስጥ መገኘቱ ዓይን ያወጣ አድልኦ እየሠራ መሆኑ ሊያወቀው ይገባል፡፡ ገዢው ፓርቲም አሁን አለኝ ከሚለው ግዝፈት በላይ ለመለጠጥ የሚሄድበት መንገድ ቅጥ ያጣ እራስ ወዳድነት እና አልጠግብ ባይነትን የሚያሳይ እንደሆነ ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ በዚህ መንገድ የምንጓዝ ከሆነ በሀገራችን ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫም ይደረጋል ብሎ ማሰብ ዘበት ይሆናል፡፡ ዜጎች በኑሮ ውድነት፣ በሙስና እና በመልካም አስተደዳደር እጦት መንገላታተቸው ሳያንስ ይህን ዓይነት በጠራራ ፀሐይ በፓርቲ መዋጮ ስም የሚፈፀም ዝርፊያ በቸልታ የሚታለፍ አይደለም፤ ዜጎችም በግልፅ እምቢ እንዲሉ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም መንግሥት በማንኛውም ደረጃ እና ተቋም ይህ ሕገወጥ ተግባር እንዳይፈፀም አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ እና ሥርዓት እንደዲያስከብር እየጠየቅን ይህን ድርጊት የሚፈፅሙ የብልፅግና ፓርቲ አባላትም ይህን ዓይነት አቅጣጫ ከየትኛውም አካል ቢወርድ ህገወጥ መሆኑን በመረዳት ለሀገራችን ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ግንባታም ጸር መሆኑን በመገንዘብ ከዚህ ሥራቸው እንደዲታቀቡ እናሳስባለን፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ይህን ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ በማጣራት በመንግሥት ተቋማት ከአገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚሰበሰብ የብልፅግና ፓርቲ ማጠናከሪያ ገንዘብ ማሰባሰብ በአስቸኳይ እንዲያስቆም እና ፓርቲው ላይ የወሰደውን የእርምት እርምጃ ለሕዝብ በግልጽ እንዲያሳውቅ እንጠይቃለን፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
መጋቢት 02/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ