13 ኢትዮጵያውያንና 38 ኬንያውያን በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ እስካኹን የደረሱበት አልታወቀም

በኢትዮጵያው ዳሰነችና የኬንያ ቱርካና ጎሳዎች መካከል በየካቲት አጋማሽ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ 13 የዳሰነች ጎሳ አባላትና 38 የኬንያ ቱርካና ጎሳ አባላት እስካኹን የደረሱበት እንዳልታወቀ የኬንያ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

የኬንያ ቀይ መስቀል የፍለጋ ቡድን እስካኹን የሦስት የቱርካና ጎሳ አስከሬኖችን ብቻ ያገኘ ሲኾን፣ 66 ሰዎች ደሞ ከተሸሸጉበት መታደግ እንደቻለ ዘገባዎቹ አመልክተዋል።

የፍለጋ ቡድኑ፣ 140 የአሳ ማስገሪያዎችንና ዘጠኝ ጀልባዎችን ጭምር እንዳስመለሰም ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። የኬንያ የፍለጋ ቡድን በዳሰነች ወረዳ ውስጥ ፍለጋ እንዲያካሂድ ቀደም ሲል ፍቃድ መስጠቱ ይታወሳል።

በተያይዘ፣ በኢትዮጵያው ኦሮሞና በቱርካና ጎሳዎች መካከል የሚካሄዱ ግጭቶችን ለመግታት የኬንያ መንግሥት ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል ባካባቢው አሠማርቷል ተብሏል።