የዶናልድ ትራምፕን ቀልብ ለማግኘት ሲባል ሎቢ የሚሰራ ሰው ይፈለግ ነበርና አንድ አሜሪካዊ ሰው (መለኮት) ለጉብኝት በአብይ አህመድ ግብዣ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በአዲስ አበባ ፕሮግራም ያዘጋጃል የተባለ ዜናን ነበር የሰማሁት። ይህን ከታች የተያያዘውን ፎቶ ስመለከት ግን ዛሬ በመስቀል አደባባይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምን መንፈሳዊ ዝግጅት ነበራት ብዬ ማህበራዊ ሚዲያውን እንድፈትሽ ሆንኩኝ። ያገኘሁት የአሜሪካዊው መለኮት ጉብኝትን ነበር። እናስ ታዲያ ዝግጅቱ ከኦርቶዶክስ ጋር በጋራ የተዘጋጀ ነው እንዴ ብዬ ዳግም ማህበራዊ ሚዲያውን ለመዳሰስ ሞከርኩ።
ወገኖቼ እነዚህ ፎቶዎች ኢዜማ የተሰኘውን የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲን አስታወሱኝ። አቋም የለሽና የስልጣን ጥመኛ የሆነው ይህ ፓርቲ አፉ ለወግ ያህል ስለተቃውሞ ቢያወራም ልቡ ግን ያለው ሙሉ በሙሉ ብልግና ፓርቲ ጋ ነው። እናም መቼስ ሚስጥር አይደበቅምና ይህን ጉዱን ጠንቅቆ የሚያውቀው አንዱ ወንድሜ የፓርቲው የወረቀት ስም ኢዜማ ቢሆንም መንፈሳዊ ስሙ ግን “ብልዜማ” ተሰኝቷል አለኝ። እናም ፎቶዎቹ ሰዎቹ እየታደሱ ወደ “ኦርቶጴንጤነት” እየተጓዙ ነው እንዴ እንድል አስገደዱኝ።

ጃል የምን ነካ ነካ ነው?። አንዴውኑ መቀላቀል አይበጅም ትላላቹ? ኦርቶዶክስ ቤት አልሳካ ያለው የተሀድሶ አብዮት ሌላኛውን ቤት እያደሰውና ወደ ኦርቶዶክስ እያመጣው ይሆን? ሶፊያ ሽባባው ይህን ነገር ከተዋቹ፣ አንዱ ተነስቶ ገድልና ድርሳን ካስወገዳቹ ኦርቶዶክስ እሆናለው ሲሉ ብዙ ጊዜ ይደመጣሉ። እኔ የምለው ግን ቤቱ አጥር ላይ ከማስቆም በዘለለ ማስቀመጥ የሚችል ወንበር የለውም እንዴ። በአጥር ላይ ቋሚውና ተመልካቹ በዛሳ።
አይን ያወጣ ሌብነት በፖለቲካ ሲሆን ያምራል። በኃይማኖት ሲሆን ግን መንፈስን ይረብሻል፣ ሞራልን ይሰብራል፣ ተስፋቢስም ያደርጋል። የሚያምረውና የሚያኮራው የራስ በሆነ ነገር ሲሆን ነው። ካይሶይ ሀኮ፣ ወርዶይ ሀኮ ይላል ጋሞው ወገኔ። ስርቆትና ውሸትን ሲፀየፍ ማለት ነው። መሠረት፣ ትሁፊት፣ ሀብትና የራስህ የሆነ አምልኮአዊ ስርዓት ከሌለህ ቀለዋጭነት (ከኦርቶዶክሱም፣ ቴዲ አፍሮ ለፍቅረኛው ከዘፈነውም፣ ከምሽት (ናይት) ክለቡም ወሰድ ወሰድ ማድረግ) ልማድህ ይሆናል። እኔ እስከማውቀው ድረስ ይህን ከተዋቹ የእናንተን ኃይማኖት እከተላለሁ የሚል ሰው ወይም ደግሞ ከሌላ ቤተእምነት ተኮርጆ የመጣ የአምልኮ ስርዓት የሚመፈፀምበትን ነገር ኦርቶዶክስ ቤት አይቼም ሰምቼም አለማወቄን ነው። እመኑኝ እንደ ፖለቲከኛነቴ ከሌላ የፖለቲካ ድርጅት ተኮርጆ የመጣ ነገር ከህዝብ ዘንድ ቅቡልነትን የሚያሰገኝ ከሆነ እቀበለው ይሆናል፤ እንደ ኦርቶዶክሳዊነቴ ከሌላ ቤተእምነት ተኮርጆ የመጣ አንዳች የሆነ ነገር ካለ እመኑኝ የዚያኔ ኃይማኖቴን እፀየፈዋለው። ወገን ኃይማኖት ወይም እምነት ከዚህም ከዚያም እያልክ ጠግነህ በማቆም የምትከተለው የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም። ጉዳዩ የህይወት ነው። ጉዳዩ የነፍስና የመዳን ነው!!!

ሽብሻቦው፣ መቋሚያው፣ ፀናፅሉና ከበሮው የአምልኮ ስርዓት ከሆነው ከአጠቃቀማቸው ጀምሮ የራሳቸው የሆነ ትርጉም አላቸው። ይህን ያህል ከኮረጃቹን እርቃን ሲኮን ለፈተና ይዳርጋልና ነጠላ ለብሳቹ ጧፍ እያበራቹ አንዴውኑ ለምን በደንብ አትመሳሰሉንም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች የኃይማኖታቸውን የአምልኮ ስርዓት መፈፀሚያ ሀብቶችን ማስከበር አንዱም ስራቸው ሊሆን ይገባል።
በነገራችን ላይ አገዛዙ የተለመደውን የዕለት አጀንዳ በማቀበል የእርስ በእርስ መራራቁን ለማስፋት ብሎ የቆመረውና ለፖለቲካው ትርፍ ሲል በኃይማኖት ጭምብል ያዘጋጀው ወጀብ ሆኖ ነው እንጂ የብዙዎቹ ጩኸት ጴንጤው ወገናችን ለምን አመለከ ወይም ለምን ጉባኤ አዘጋጀ አይደለም። ሆኖም አያውቅም። ይህን እውነተኞቹ ጴንጤዎች ያውቁታል። ጩኸቱ ከኃይማኖቶች አካባቢ እጅህን አርቅ፣ ኃይማኖተኛ የሚሰራውን ኃይማኖታዊ የሆነ ስራን አትስራ፣ የመንግስት ተቋማትንም ሆነ ሀብት ፍትሃዊነት በጎደለው መንገድ ኃይማኖታዊ ለሆነ ዓለማ አታውል ነው።

በዚህ መሰሉ ጉዞ ዛሬ ልትጨፍር ብትችልም ዛሬ ግን ፈፅሞ ነገን አንደማይሆን ልታውቅ ይገባል። የተዘራ የሚታጨድበት ቀን አለውና።
በተረፈ በቅን ልባቹ በየዋህነት ኃይማኖታዊ አገልግሎታችሁን ለፈፀማቹ ወገኖቼ ክብር አለኝ። Wondimagegn Anjulo Sisay