በራያ አላማጣ ጥሙጋ በቤተክርስቲያን ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት አምስት ሰዎች ተገደሉ

በራያ አላማጣ ወረዳ ጥሙጋ ከተማ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከትናንት ወዲያ ሌሊት በተፈጸመ ጥቃት አንድ የቤተክርስቲያኗ መምህርና አራት የቆሎ ተማሪዎች እንደተገደሉ የአካባቢው ነዋሪዎች መናገራቸውን ዶቸቨለ ዘግቧል።

በጥቃቱ ቢያንስ አምስት ሰዎች እንደቆሰሉ መስማቱን ዘገባው ጠቅሷል። ጥቃቱን የፈጸሙት የመከላከያ ሠራዊት መለዮ የለበሱ የታጠቁ ኃይሎች መኾናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል ተብሏል።

አንዳንድ እማኞች፣ ግድያው የተፈጸመው በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የፋኖ ታጣቂዎች አሉ የሚል የተሳሳተ መረጃ ባካባቢው ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በመድረሱ ሳይኾን እንዳልቀረ ግምታቸውን እንደሠጡም የዜና ምንጩ አመልክቷል።