USAID በዓለም ዙሪያ በወባ፣ በኤች አይ ቪ ኤድስና በሳንባ ነቀርሳ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች እንደገና ሥራቸውን እንዲቀጥሉ መመሪያ ሰጠ

በአሜሪካው ዓለማቀፍ ተራድዖ ድርጅት ሥር በዓለም ዙሪያ በወባ፣ በኤች አይ ቪ ኤድስና በሳንባ ነቀርሳ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች እንደገና ሥራቸውን እንዲቀጥሉ በዚህ ሳምንት አዲስ መመሪያ እንደደረሳቸው የአሜሪካ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር፣ በተራድዖ ድርጅቱ ሥር የሚገኙ የዕርዳታ ፕሮግራሞች ምን ምን ሥራዎችን ሲሠሩ እንደነበርና የአሜሪካን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ያላቸውን አስፈላጊነት በደረጃ እንዲያስቀምጡ መጠይቆችን እንደላከላቸው ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

መጠየቁ ከደረሳቸው መካከል፣ በጤና፣ በምግብ ዋስትና፣ በመብትና ዲሞክራሲ ዙሪያ ይሠሩ የነበሩ የድርጅቱ ዘርፎች እንደሚገኙበት ዘገባው ጠቅሷል። በጤናው ዘርፍ መጠይቁ ከደረሳቸው መካከል፣ ባስቸኳይ የምግብ ዕርዳታና በወባና የሳንባ ነቀርሳ በሽታ ዙሪያ የሚሠሩ ፕሮግራሞች ይገኙበታል ተብሏል።

የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር፣ የገንዘብ ዕርዳታ የተቋረጠባቸውን የአብዛኞቹን ፕሮግራሞች ግምገማ እንዳጠናቀቀ ገልጧል።