የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአልሸባብ ዒላማዎች ላይ ጥቃት ፈጸመ

የሱማሊያ መከላከያ ሚንስትር አሕመድ ኑር፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአልሸባብ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን መናገራቸውን የአገሪቱ መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጥቃቱን የፈጸመው፣ በመካከለኛው ሸበሌ አውራጃ እንደኾነ ዘገባው ጠቅሷል። ኾኖም በጥቃቱ በአልሸባብ ላይ ስለደረሰው ጉዳት ሚንስትሩ አልገለጡም ተብሏል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጥቃቱን መፈጸሙ የተነገረው፣ የኢትዮጵያና ሱማሊያ ወታደራዊ አዛዦች ሱማሊያ ውስጥ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋትና የኢትዮጵያ ወታደሮች በአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ ሰጪና ማረጋጊያ ተልዕኮ ሥር የሚሠማሩበትን ስምምነት ከተፈራረሙ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአልሸባብ ላይ የአየር ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ያለው ነገር የለም።