‘GTNA’ ለሚድያ መገንቢያ የተሰጠውን 5 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በ1 ቢልዮን ብር ሊሸጥ እያስማማ መሆኑ ታወቀ
– ቦታው ለጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ማስፋፊያ ተብሎ የተያዘ ነበር
(መሠረት ሚድያ)- ግሎባል ቴሌቭዥን ኔትዎርክ ኦፍ አፍሪካ (GTNA) በሚል ስያሜ የተቋቋመው እና በአፍሪካ ግዙፉ የሚድያ ተቋም ይሆናል የተባለለት ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሊዝ የተረከበውን 5ሺ ካሬ ሜትር ቦታ በደላሎች አማካኝነት ሊሸጥ መሆኑ ታውቋል።
GTNA መሬቱን ከተረከበ ሶስት አመት እንዳለፈው የጠቆሙት ምንጮቻችን አሁን ላይ ጋንዲ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው ቦታው ታጥሮ ለመኪና ፓርኪንግ አገልግሎት ብቻ እየዋለ መሆኑን ከምስሎች እና ቪድዮዎች ጋር አያይዘው ለመሠረት ሚድያ ልከዋል።

“በመጀመርያ በደላሎች አማካኝነት ለሽያጭ የቀረበው በ1.4 ቢልዮን ብር ነበር፣ ገዢ ስላልተገኘ አሁን ላይ እስከ 1 ቢልዮን ብር እየተጠራበት ነው” የሚሉት ምንጮች አፍሪካን ማዕከል አድርጎ የአፍሪካን እውነት ለአለም ያሳውቃል የተባለለት ተቋም መሬቱን ለምን እንደሚሸጥ እንደማያውቁ ተናግረዋል።
አንድ የከተማ አስተዳደሩ ባልደረባ ግን መሬቱ ለሽያጭ መቅረቡን እንደሚያውቁ ለሚድያችን ገልፀው “በዲዛይኑ ላይ የተቀመጠውን ግዙፍ መንትያ ህንፃዎች ለመገንባት አበዳሪ ባንክ አልተገኘም፣ ምናልባት ሀብት ለማሰባሰብ ይሆናል” ብለዋል።
ግሩም ጫላ በተባለ ግለሰብ አማካኝነት በአፍሪካ ትልቅ ሚዲያ ሊገነባ እንደሆነ በርካታ ሚድያዎች ከሶስት አመት በፊት መዘገባቸው ይታወሳል። ለሚድያው ዋና መስሪያ ቤት የሚውለው ቁልፍ ቦታ ከጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ይዞታ ጭምር ተወስዶ እንደተሰጠ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
“መንግሥት ለጋንዲ መታሠቢያ ሆስፒታል የማስፋፊያ ህንፃዎች ግንባታ የሚሆን ሰፊ ቦታ አዘጋጅቶ ነበር፣ ይሁንና ከሆስፒታሉ ይዞታ ላይ 5,000 ካሬ ሜትር የሚሆን ቦታ በቂርቆስ ወረዳ 07 የግንባታ ፈቃድ ከሚሰጡ ሰዎች ጋር በተደረገ ውል በሆስፒታሉ ካርታ ላይ ሌላ አዲስ ካርታ ተሰርቷል” የሚሉት እኚህ የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኛ በአንድ አጋጣሚ ለምን ብለው በጠየቁ የሆስፒታሉ ሰራተኞች ላይ ማስፈራራት ደርሶባቸው ነበርም ብለዋል።
ከጋንዲ ሆስፒታል ያገኘነው ተጨማሪ መረጃ እንደሚጠቁመው ሆስፒታሉ ለወላድ እናቶች አገልግሎት የሚውል የከርሰ ምድር ውሃ አስቆፍሮ የነበረ ሲሆን እሱም በGTNA ይዞታ ስር ሊሆን ይገባል የሚል አምባጓሮ ተነስቶ በመጨረሻም በ GTNA ይዞታ ስር እንደተጠቃለለ ታውቋል።