በየመን ባህር ዳርቻ በደረሰ አደጋ 181 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ጠፍተዋል።

በየመን ባህር ዳርቻ በደረሰ አደጋ 181 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ጠፍተዋል።

በየመን እና በጅቡቲ የባህር ዳርቻ ስደተኞችን አሳፍረው ሲሄዱ የነበሩ 4 ጀልባዎች በነበረው ከፍተኛ ንፋስ ምክንያት መስጠማቸውንና ቢያንስ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉንና 186 ሰዎች በፍለጋ ላይ እንደሚገኙ የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ገልጿል።

ጀልባዎቹ ከጅቡቲ ወደ የመን ስደተኞችን ጭነው ሲጓዙ የነበረ ሲሆን እንደ አሶሼትድ ፕረስ ዘገባ አብዛኞቹ ተጓዥ ስደተኞች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ይገልጻል።

ከአራቱ መርከቦች ሁለቱ በየመን ባህር ዳርቻ አከባቢ የሰመጡ መርከቦች ሲሆኑ ከዚህም ውስጥ 181 ስደተኞች እና 5 የየመን መርከበኞች የት እንደገቡ አልታወቀም። ከዚህ አደጋ ሁለት የየመን መርከበኞች መትረፋቸውን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ቃል አቀባይ ታሚም ኤሊያን ለኤፒ ገልጸዋል።

ሌሎች ሁለት ጀልባዎች በተመሳሳይ በጅቡቲ ባህር ዳርቻ የሰጠሙ ሲሆን የሁለት ስደተኞች ሲሞቱ ሌሎች ስደተኞችን ማትረፍ ተችሏል ተብሏል።

በየመን ባህር ዳርቻ ከሰመጡት ከሁለቱ ጀልባዎች በአንደኛው ጀልባ 31 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እና ሶስት የመን መርከበኞች ተሳፍረው የነበረ ሲሆን በሌላኛው መርከብ ደግሞ በተመሳሳይ150 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችና 4 የየመን መርከበኞችን ጭኖ ነበር።

እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጃ ከሆነ ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን በሚደረገው የስደተኞች ጉዞ እ.ኤ.አ በ2024 ብቻ 558 ሰዎች ህይወት ቀጥፏል።