ብሪታንያ፣ ኤርትራ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ራፖርተር መሐመድ ባቢከር ጋር በመተባበር ወይም የሰብዓዊ መብት ይዞታዋን በማሻሻል ረገድ አንዳችም አዎንታዊ ለውጥ አላሳየችም በማለት በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የምክክር መድረክ ላይ ከሳለች።
ብሪታንያ፣ ኤርትራ በወታደራዊ አገልግሎት ሕጓ ላይ ባስቸኳይ ማሻሻያ እንድታደርግና ዜጎች የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት እንዲሠጡ የሚገደዱበትን ጊዜ እንድትወስን ጠይቃለች። ብሪታንያ፣ መንግሥት ይህን ማሻሻያ ካደረገ፣ ወጣቶች የወደፊት የሕይወት እጣ ፈንታቸውን ለመወሰን እንደሚያስችላቸውና በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት እንዲጨምር እንደሚያግዝም ጠቁማለች።
በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ የኤርትራ መንግሥት የሚፈጽማቸው “ማስፈራሪያዎች” እና “ዛቻዎች” ተቀባይነት እንደሌላቸው ብሪታንያ ገልጣለች። የምክር ቤቱ አባል የኾነችው ኤርትራ፣ የምክር ቤቱ አባል አገራት ያቀረቡባትን ውንጀላዎች “ያረጁና ያፈጁ” ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጋለች።