ያንዣበበው የሥጋት ደመና ይገፈፍ!
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ መረጃዎች እየተንሸራሸሩ ነው፡፡ በቅርቡ በቀድሞው የኤፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በአልጄዚራ ላይ የኤርትራን መንግሥት የጦረኝነት አባዜ የሚተርክ ጽሑፍ ከወጣ በኋላ፣ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ጠንካራ ምላሽ መስጠታቸውና ሌሎችም በሁለቱ አገሮች የሻከረ ግንኙነት ላይ ተመሥርተው እየሰጧቸው ያሉ አስተያየቶች የጦርነት የሥጋት ደመና ማንዣበቡን እያመላከቱ ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድን ወደ ለየለት ቀውስ ሊከት የሚችል የጦርነት ወሬ አየሩን ሲሞላው ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች ጎረቤቶቿ የሚያዋጣቸው ልዩነቶቻቸውን በሰከነ መንገድ በማለዘብ ልማት ላይ ቢያተኩሩ ይሻላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራም በሰጥቶ መቀበል መርህ የጋራ ልማት ላይ ማተኮር ሲገባቸው፣ ለዘመናት ሲዳክሩበት ኖረው ከውድመት በስተቀር ትርፍ ያላገኙበት ጦርነት ውስጥ እንደገና ሊዘፈቁ አይገባም፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን በባድመ ጦርነት በመሰዋት ለሃያ ዓመታት በፍጥጫ ቆይተው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከያዙ በኋላ ፍጥጫው ረግቦ መልካም ግንኙነት መጀመራቸው በታላቅ ደስታ አቀባበል እንደተደረገለት ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ጦርነት በገታው የፕሪቶሪያ ስምምነት ሳቢያ ቢቀዛቀዝም፣ ከመነሻውም ግንኙነቱ ተቋማዊ ሆኖ በሥርዓት ባለመመራቱ የዘላቂነቱ ጉዳይ ያጠራጠራቸው ሥጋታቸውን በወቅቱ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ የኤርትራ ሠራዊት ትግራይ ውስጥ የፈጸመውን የጦር ወንጀል ጨምሮ ሌሎች ምክንያቶች ተደራርበው ግንኙነቱ ሲቀዛቀዝ፣ በሁለቱም ወገኖች በኩል ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ እንጂ በይፋ የሚነገር ተቃርኖ አልተደመጠም፡፡ ነገር ግን ሁለቱም አገሮች ብዙዎችን በደስታ ካስፈነጠዘው ግንኙነት ማፈንገጣቸው ለማንም የተሰወረ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ልዩነቱ አፍጥጦ በመደበኛና በኢመደበኛ ሚዲያዎች እየተሰጣ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ በቅርብ ርቀት ከሚገኘው ቀይ ባህር ተጋሪ መሆን ይኖርባታል ብሎ አቋሙን ሲያስታውቅ፣ የመጀመሪያው ቁጣና ተቃውሞ የተሰማው ከኤርትራውያን በኩል ነበር፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን በኃይል ለመያዝ ፈልጋ ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 1 ቀን 2024 የባህር በር መግባቢያ ስምምነት በመሪዎቻቸው አማካይነት ሲፈራረሙ፣ ሶማሊያ በንዴት ተነስታ ሉዓላዊነቴና የግዛት አንድነቴ ተጣሰ ስትል የመጀመሪያው አጋርና ወዳጅ ሆኖ የቀረበው የኤርትራ መንግሥት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተደጋጋሚ ከሶማሊያና ከግብፅ ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ በተፃራሪ መቆሙ ይታወሳል፡፡ ለልማትና ለዕድገት መተባበር የሚገባቸው የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በረባ ባልረባው ጦር ለመማዘዝ በጣም ቅርብ መሆናቸው ከማስገረም አልፎ፣ ለመጪው ትውልድ ቂም የሚያወርስ አሳዛኝ ድርጊትን ሙጥኝ ማለታቸው ያሳዝናል፡፡
ኤርትራ ከኢትዮጵያ በይፋ በ1983 ዓ.ም. ስትለያይ ሥርዓት ባለው መንገድ አልነበረም ይሉ የነበሩ ወገኖች ድምፅ በአግባቡ አለመደመጡ፣ በባድመ ምክንያት ለተከሰተው ጦርነትና ላስከተለው ዕልቂትና ውድመት ሰበብ መሆኑ ይነገራል፡፡ አውዳሚው ጦርነት በአልጀርስ ስምምነት ቆሞ ዘ ሄግ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የድንበር ኮሚሽን አማካይነት ክርክር ተደርጎ ውሳኔ ላይ ቢደረስም፣ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ባለመቻሉ ምክንያት ነው ለሃያ ዓመታት ሁለቱ አገሮች አንዱ የሌላውን ተቃዋሚ እያደራጁ ተፋጠው የኖሩት፡፡ የዛሬ ስድስት ዓመት ፍጥጫውን በመግታት አዲስ ግንኙነት ቢጀመርም፣ የጋራ ልማት ላይ በማተኮር ሁለቱን አገሮች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች አልተከናወኑም፡፡ ከኢትዮጵያ በኩል ወደ አሰብ ወደብ የሚሄደው መንገድ ቢገነባም፣ በኤርትራ በኩል ግን ተመሳሳይ ዕርምጃ አልተወሰደም፡፡ ከልማት ዕሳቤ ይልቅ የተለመደው ሴረኝነት ውስጥ እየተገባ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ እየተሰማ ነው፡፡
ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰሙ ሥጋቶች ቢኖሩም በዚህ ጊዜ ሰተት ብሎ ጦርነት ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡ ድንበር ተጋሪ የሆኑት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ኬንያ እርስ በርስ እየተገበያዩና በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተሳሰሩ መደጋገፍ ነው የሚያዋጣቸው፡፡ እነዚህ ድንበር ተጋሪ አገሮች ከበፊት ጀምሮ የውክልና ጦርነት ማስተናገጃ ሆነው ከመደህየታቸው በተጨማሪ፣ ለልማትና ለዕድገት መዋል የነበረበትን የሰው ኃይል ሲያስፈጁና ንብረት ሲያስወድሙ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ አንዳቸው የሌላቸውን ከሌላው እየተዋሱ በጋራ ማደግ ሲኖርባቸው የውክልና ጦርነት ሰለባ ሆነው ሲጎዳዱ ኖረዋል፡፡ የሰው ኃይላቸውንና በተፈጥሮ የተቸሩዋቸውን ፀጋዎች በማቀናጀት ከድህነት ማጥ ውስጥ መውጣት ሲኖርባቸው፣ አሁንም ከዚያ አዙሪት ውስጥ ለመውጣት አለመቻላቸው ያስቆጫል፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ከጦረኝነት አባዜ ውስጥ አለመውጣትም ሆነ፣ የመጪውን ትውልድ ዕጣ ፈንታ ማበላሸት ተገቢ አይደለም፡፡
ባለፈው ሳምንት ኤርትራ ውስጥ ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ኤርትራውያን ከአገር እንዳይወጡና የሠራዊት ተጠባባቂዎች ወደ ካምፕ እንዲገቡ ክተት ሲታወጅ፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የአስተዳደር እርከኖች ወደ ካምፕ መግባት ያለባቸውን መዝግበው እንዲያሳውቁ ትዕዛዝ መተላለፉ ተሰምቷል፡፡ በተጨማሪም የኤርትራ መንግሥት አዲስ አበባ የሚገኘው ኤምባሲውን እየዘጋ መሆኑም ሌላው መረጃ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ነገር እየተሰማ ያለው በኢትዮጵያ በኩል የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሳንካ እንዳልገጠመው በተነገረ ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ምንም እንኳ ከኢትዮጵያ መንግሥት የሰሞኑን የኤርትራ ሁኔታ በተመለከተ ይፋዊ መግለጫ ባይሰማም፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከመቀዛቀዝ አልፎ ወደ ፍጥጫ ሊያስገቡ የሚችሉ ምልክቶች ግን እየታዩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል መደረግ የሚኖርበት ችግሮች በሰላም የሚፈቱበትን መንገድ ማፈላለግ ነው፡፡ በጦርነት የሚገኝ አንዳችም ትርፍ ስለማይኖር ለሰላም ሲባል ትዕግሥት ይኑር፡፡ ያንዣበበው የሥጋት ደመናም ይገፈፍ!