መጨረሻው ያለየለት የUSAID እግድ

አንድ ወር ያስቆጠረውና መጨረሻው ያለየለት የUSAID እግድ

የትራምፕ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የUSAID እንቅስቃሴ ላይ የ90 ቀን እቅድ መጣል ሲሆን ይህ እግድ ከተጣለ 35 ቀናት አልፈዋል።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ በUSAID በኩል የምታገኘው ድጋፍ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ትልቁ ነው። በድርቅና በርስ በርስ ግጭት ውጥ ላሉ ዜጎች የአሜሪካ መንግስት በ2023 1.77 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ አድርጓል።

USAID በኢትዮጵያ ከምግብ እርዳታ ቀጥሎ ሁለተኛው ትልቁ ቅድሚያ የሚሰጠው ዘርፍ ጤና ሲሆን በዓመት 200 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ ይደረግበታል።

USAID በዓመት 200 ሚሊዮን ዶላር ለጤናው ዘርፍ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ፈሰስ ያያደርጋል። ጤና ሚኒስቴር ይህንን ለክልሎች የማከፋፈሉን ሥራ ይሰራል። በተጨማሪም ተላላፊ በሽታዎችና የተመጣጠነ ምግብ ላይ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችንም ይደግፋል። ይህ አሁን ላይ ቆሟል።

በኢትዮጵያ በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና የገንዘብ እጥረት ምክንያት የወባ ተጠቂዎች በ2019 ከነበረው 900 ሺ በ2024 ወደ 7.3 ሚሊዮን ተጠቂዎች ከፍ ብሏል። የኩፍኝ በሽታም ከ2021 ከ 1,941 ተጠቂዎች ወደ በ2024 ወደ 28,129 ከፍ ብሏል።

ሌላው ትልቁ ጉዳይ ደግሞ የኤችአይቪ ኤድስ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች ላይ ያለው ድርሻ ነው። ለዚህ ተግባር በ2023 ብቻ 3 ቢሊዮን ዶላር ከአሜሪካ መንግስት ፈሰስ ተደርጓል።

በተጨማሪም በUSAID የሚደገፉ ፕሮግራሞች ለኤች አይ ቪ፣ ለሳንባ ነቀርሳ እና ለወባ መድኃኒቶችን ወደ ገጠር ክሊኒኮች ማድረስም ቆመዋል።

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በአሜሪካ እርዳታ የተቀጠሩ ከ 5,000 በላይ ሰራተኞችን ለማባረር ሊገደድ እንደሚችልም መገለጹ ይታወሳል።

በሰብዓዊ እርዳታው በኩልም በተመሳሳይ አሁን ባለው ተጨባጭ ኹኔታ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምግብ አቅርቦቶቹን ከጨረሰ፣ ተጨማሪ የዕርዳታ ምግብ መግዛት እንደማይችል ገልጿል።

ዘጋርዲያን ይዞት በወጣው ዘገባ ማሽላና የምግብ ዘይትን ጨምሮ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን ለአንድ ወር መመገብ የሚችል 34 ሺሕ 800 ሜትሪክ ቶን እህል፣ ወደ አገር ውስጥ ለሚያስገቡ አካላት የሚከፈል ገንዘብ ባለመኖሩ ጅቡቲ ወደብ ላይ መቆሙን ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የስደተኞች ቁጥር የምታስተናግድ ሀገር እንደመሆኗ ነገሮችን ከባድ ያደርጉታል።

USAID ለኢትዮጵያ በ2023 የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሲያደርግ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ 1.4 ቢሊዮን ዶላር የእዳ ክፍያ ፈጽማለች። የUSAID ድጋፍ መቆም ኢትዮጵያ በጀመረችሁ ኢኮኖሚክ ሪፎርም ላይ የሚኖረው ተጽዕኖም ቀላል አይደለም።

በኢትዮጵያ ከ5 ሺ በላይ የሲቪክ ማኅበራት በUSAID ድጋፍ የጀመሯቸው ፕሮጀክቶች ጭምር በመቆማቸው በእነዚህ ተቋማት እና በየፕሮጀክቱ የሚሰሩ ሰራተኞች ላይ ከፍተኛ ጫናም የፈጠረ ነው።

ሀገራት ለአሜሪካ ድንገተኛ ውሳኔ አማራጭ እቅዶችን መንደፍ ግድ ይላቸዋል። ኢትዮጵያም ከዲፕሎማሲያዊ እስከ ሀገር ውስጥ ገቢን እስከማሳደግ እንዲሁም ወጪ ቅነሳ እና የበጀት ዝውውር እቅዶችን እንደ አማራጭ ልትመለከት ትችላለች።

እውን ይህ ክስተት እንደ የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ሃካይንዴ ሂቺሌማ አገላለጽ “የማንቂያ ደውል” ይሆን ?

የትራምፕ አስተዳደር የ90 ቀኑን እግድ ሲጠናቀቅ የመጨረሻ ውሳኔው ምን ይሆን ? የኢትዮጵያ መንግስትስ መፍትሔ?