በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ግቢ ውስጥ ውሀ በአቆረ ጉድጓድ (ኩሬ) ዉስጥ ዋና ለመዋኘት የገቡ ሦስት ታዳጊዋች ህይወታቸዉ ማለፉ ተገልጿል።
ታዳጊዎቹ ትላንት እሁድ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ኳስ ሲጫወቱ ቆይተዉ በዕጽዋት ማዕከሉ ጊቢ ዉስጥ ባለው ውሀ በአቆረ ጉድጓድ ዉስጥ ዋና ለመዋኘት በገቡበት ወቅት አደጋው ማጋጠሙን የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ የታደጊዎቹ ዕድሜ ሁለቱ የ13 ዓመት እድሜ ያላቸው ሲሆኑ አንደኛዉ ደግሞ 16 ዓመቱ መሆኑን በመግለጽ የኮሚሽን መሥሪያ ቤቱ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችና ጠላቂ ዋናተኞች የታዳጊዎቹን አስከሬን አዉጥተዉ ለፖሊስ ማስረከባቸውን ተናግረዋል።
በዚሁ በጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ዉስጥ ጥቅምት 02 ቀን 2017 ዓ.ም ዕድሜዉ 16 ዓመት የተገመተ ወጣት በተመሳሳይ ሁኔታ በጉድጓዱ ውስጥ ዋና ለመዋኘት ገብቶ ህይወቱ ማለፉን የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አስታውሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ክበበ ጸሀይ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ውሀ ባቆረ ጉድጓድ ዉስጥ ዋና ለመዋኘት የገባ የ14 ዓመት ታዳጊ ህይወቱ ማለፉንም ገልጸዋል፡፡ የኮሚሽኑ ጠላቂ ዋናተኞችም የታዳጊዉን አስከሬን አውጥተው ለፖሊስ አስረክበዋል ነው ያሉት።
በአዲስ አበባ በአንዳንድ አካባቢዎች ውሀ ባቆሩ ጉድጓዶች ውስጥ ዋና ለመዋኘትና ለመታጠብ በሚል በተለይ ታዳጊዎችና ወጣቶች እየገቡ ህይወታቸዉ እያለፈ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።
ጉድጓዱን የቆፈሩና በዉሀ የሚጠቀሙ አካላት ተገቢዉን የአደጋ መከላከል ስራ የማከናወን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እና የአካባቢዉ ማኅበረሰብም ለታዳጊዋች አስፈላጊዉን ጥበቃ እንዲያደርግ ኮሚሽን መሥሪያ ቤቱ አሳስቧል።
ዘገባው የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ነው።