“እናቴም አርጅታለች እስካሁን ከመታገቷ ውጭ በእህቴ ላይ የሚደርስባትን ድብደባ አሳይቻት አላቅም ምክንያቱም ካየች ትሞትብናለች” የታጋች እህት

“እናቴም አርጅታለች እስካሁን ከመታገቷ ውጭ በእህቴ ላይ የሚደርስባትን ድብደባ አሳይቻት አላቅም ምክንያቱም ካየች ትሞትብናለች” የታጋች እህት

አዜብ ሽሙየ ትባላለች። በወልቃይት ጠገዴ ቃፍታ ሁመራ ዓዲ ሕርዲ ከተማ ተወልዳ ያደገች የ17 ወጣት እና የ9ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች።

ያልፍልኛል ብላ በመስከረም ወር 2017ዓ/ም በሱዳን በረሀ በሊብያ አቋርጣ ስትሰደድ ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም አብሮዋት ከተጓዙ ሁለት የአከባቢዋ ሴት ልጆች ጋር በአጋቾች ስር ትወድቃለች።

የታጋች እህት መሆኗን ጠቅሳ መረጃውን ያደረሰችን ወይዘሮ ናፈቁሽ ሙሉ ስለ ጉዳዩ ስታስረዳ “እኛ ምንም አይነት ገንዘብ የለንም። አባታችን ጥበቃ ነበር የሚሰራው አሁን ጡረታ ወጥቷል። እናቴም አርጅታለች እስካሁን ከመታገቷ ውጭ በእህቴ ላይ የሚደርስባትን ድብደባ አሳይቻት አላቅም ምክንያቱም ካየች ትሞትብናለች” ስትል ትገልጻለች።

“በየቀኑ እየደበደቡ በኢሞ እና በዋትሳብ (Whatsapp) ቪዲዮ ይልኩልናል። በየቀኑ ገንዘቤን ትልኩ እንደሆነ ላኩ ካላካችሁ እህትሽ እንደሞተች ቁጠሪያት ይሉኛል ” ስትል በእንባ ጭምር ያለችበትን ሁኔታ ታስረዳለች።

አጋቾቹ 750 ሺሕ ብር መጠየቋቸውን  በመጥቀስ “ገንዘቡን መላክ አልቻልኩም፤ ወላጆቻችን አዛውንቶች ናቸው ፣ ያለሽን ላኪ እና እንልቀቅልሽ ሲሉኝ ጥር 21/2017 ዓ.ም 250 ሺህ ብር  በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቁጥር ልኬላቸው ነበር። ነገር ግን እንኳን ሊለቋት ይቅር እና የሚፈፅሙባትን ጥቃት መናገርም መስማትም ይሰቀጥጣል ” ስትል ታስረዳለች።

በወልቃይት ጠገዴ ቃፍታ ሁመራ ወረዳ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥረው እንደሚሰሩ ገልፀው  አሁን ባላቸው አነስተኛ ደመወዝ የተጠየቁትን ገንዘብ ማሟላት  እንደማትችል አስረድታለች።

የ17 ዓመት ታዳጊዋ አዜብ ላይ እገታው ሲፈፀም አብረዋት ሁለት ኢትዮጵያን ቢኖሩም ሁለቱም ቤተሰቦቻቸው የተጠየቁትን ገንዘብ በመክፈላቸው መለቀቃቸውን ጭምር ገልጻለች።

“የኔ እህት ግን ለአምስት ወራት በአረመኔዎች እጅ ናት፣ ሁሌም የሚልኩልኝን ቪዲዮ እያየሁ ለእህቴም ሳልደርስላት መሞቴ ነው” ስትል ሀዘኗን ገልጻለች።

በመሆኑም ቤተሰቦቻችን የገጠር ነዋሪ ከመሆናቸውም በላይ  በእድሜ የገፉ እና የተጠየቁትን ገንዘብ ለመክፈል ይቅርና ለራሳቸውም እየተጦሩ ነው የሚኖሩት በማለት የቤተሰቦቻቸውን ሁኔታም አስረድተዋል።

“ለቤተሰቦቻችን መታገቷን እንጂ የሚደርስባትን ሲቃይ ነግሬያቸው አላቅም ያም ሆኖ ግን ሁሌም እያለቀሱ ነው። እኔም መኖሬ ትርጉም አልባ ሆኖብኛል” ስትል የታጋች እህት ወይዘሮ ናፈቁሽ ሙሉ ነግረውናል።

የታጋቿ እህት ፣ ታጋቿ  አዜብ በአጋቾች እየደረሰባት ያለውን ስቃይ የሚያሳይ ቪዲዮ የላኩ ሲሆን፣ አጋቾችዋ ኢትዮጵያውያን ወይም ኤርትራውያን መሆናቸው በደብደባ ወቅት ከሚናገሩት የትግርኛ ቃላት መረዳት ይቻላል።

በተጨማሪም እህቷ 250 ሺ ብር የላከችበትን የባንክ መረጃም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አጋርታለች።

መርዳት ለምትሹ 1000456940041 የወይዘሮ ናፈቁሽ ሙሉ የንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር ነው። ወይዘሮ ናፈቁሽን በዚህ ስልክ 0938602801 ማግኘት ይቻላል።