በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር ቱርካናና ዳሰነች አከባቢ በተከሰተዉ ግጭት እስካሁን 5 ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል

” በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር ቱርካናና ዳሰነች አከባቢ በተከሰተዉ ግጭት እስካሁን 5 ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል ” – የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር

⚫️ ” በአከባቢዉ ዛሬ ከማለዳዉ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 9 ሰዓት ከፍተኛ ተኩስ ነበር ! “

በጎረቤት ሀገር ኬንያ ቱርካና እና ኢትዮጵያ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች አከባቢ በአሳ ማጥመጃ ጀልባና መረብ ስርቆቶች እንደተነሳ በተገለጸ የአርብቶ አደሮች ግጭት ባለፉት ሶስት ቀናት 5 ኢትዮጵያዊያን መገደላቸውን የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስታውቋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ 28 ቀበሌዎች ከጎረቤት ሀገር ኬንያ ጋር ድንበር የሚጋሩ ሲሆን በአከባቢዉ በሁለቱ ሀገራት አዋሳኝ ላይ ከሚገኘው የቱርካና ሀይቅ አሳ በማስገር ስራ የአከባቢው አርብቶ አደሮች በጋራ ሲጠቀሙ የቆዩ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኦሞ ወንዝ መሙላቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ በኩል የአሳ ምርት መበራከቱንና የኬንያ አርብቶ አደሮች ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀዉ የመግባትና የአሳ ማስገሪያ መረብና ጀልባዎች (ዛተራ) የመስረቅ አዝማሚያዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የዳሰነች ወረዳ አስተዳዳር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስረድቷል።

ይህን ተከትሎም ባሳለፍነዉ ሳምንት በኬንያ ቱርካና ግዛት የአከባቢው አስተዳዳሪዎች ጋር በመነጋገር መግባባት ላይ በመድረስና ከሁለቱም አከባቢ አርብቶ አደሮች ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ተይዞ በነበረበት የኬንያ አርብቶ አደሮች ከትላንት በስቲያ ሁለት ኢትዮጵያዊያንን በትላንትናው ዕለት ደግሞ ሶስት የአንድ ቤተሰብ አባላትን መግደላቸዉን ተከትሎ የዳሰነች አርብቶ አደሮች አስከሬን ለመዉሰድና ለአፀፋ ተኩስ ከፍተዉ እንደነበር የወረዳዉ መንግስት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስታውቋል።

በዛሬዉ ዕለት በተለያዩ ተሽከርካሪዎች ታግዘዉ ከኬንያ በኩል በርከት ያሉ የታጠቁ ሃይሎች ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ እስከ ቀትር 9 ሰዓት ድረስ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብተዉ ሲታኮሱ መዋላቸዉን የገለፀው የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር የኬንያ ፓርላማ አባላት ወደ አከባቢው በመምጣት ተኩሱን ማስቆማቸዉንና ዜጎቻቸዉን ከኢትዮጵያ መሬት ማስወጣታቸውንና ከዳሰነች ወረዳና የዞን ፀጥታ መዋቅር ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ግጭቱ የተከሰተበት ቦታ ከደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ዋና ከተማ ኦሞ ራቴ 30 ኪሎሜትር ርቀት አከባቢ ሲሆን በተለይም በኬንያ ቱርካና ‘ ኮኮሮ ‘/ተብሎ በሚጠራዉ አከባቢና በኢትዮጵያ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ አሪኮ አከባቢ መሆኑም ተገልጿል።

የኬንያ አንዳንድ ሚዲያዎች ከ20 በላይ የሀገሪቱ አሳ አስጋሪዎች ” በቱርካና ሀይቅ ላይ ከኢትዮጵያ በኩል ሜሪሌ አከባቢ በገቡ ታጣቂዎች ተገድለዋል ” የሚል ዘገባ እየሰሩ ናቸው።