ከባለስልጣናት ጋር የተሻረኩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አስመጪዎች ችግር እየፈጠሩ ሲል ሚኒስትሩ አማረረ

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር፣ ከባለስልጣናት ጋር የተሻረኩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አስመጪዎች ከመነሻ አገራት የቅድመ ጭነት ኢንስፔክሽን ሳያከናውኑና የሦስተኛ ወገን የጥራት ፍተሻ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሳይዙ ጉሙሩክ ጣቢያ ከደረሱ በኋላ የጥራት ፍተሻ ወረቀት ተሠጥቷቸው እንዲያስገቡ በመጠየቅ ችግር እየፈጠሩ እንደኾነ አስታውቋል።

ከደረጃ በታች የኾኑ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሲባል የመንግሥትን አገልግሎት “በገንዘብ ለመግዛት መሞከር ፈጽሞ አይቻልም” ያለው ሚንስቴሩ፣ ማንኛውም አስመጪ ሕጋዊውን የአሠራር ሥርዓት ብቻ ተከትሎ እንዲሠራ አሳስቧል።

በሕጋዊ አሠራሩ መሠረት፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ 13 ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት በመነሻ አገራት በዓለማቀፍ የኢንስፔክሽን ተቋማት የቅድመ ምርት ጭነት ፍተሻ ምስክር ወረቀት ማቅረብ እንዳለባቸው ሚንስቴሩ ገልጧል።

ሚንስቴሩ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከመነሻ አገር ሳይኾን ከጅቡቲ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መሞከር የሕዝቡን ደኅንነትና ጥቅም እንዲኹም የአገርን ኢኮኖሚ ይጎዳል ብሏል። ከባለስልጣናት ጋር የተሻረኩ አስመጪዎች ኝ በሕገወጥ አሰራራር የተተበተበውን ስራቸውን ካለምንም ፍርሃት ቀጥለዋል።