የኤርትራ መንግሥት ያገቡና የልጆች እናት የሆኑ ሴቶችን ጨምሮ እድሜአቸው ከ60 አመት በታች የሆኑ ዜጎቹ እንዲዘመገቡና ወደ ካምፕ እንዲገቡ ትዕዛዝ አስተላለፈ።
ወታደራዊ ግዳጁ ከዚህ በፊት በውትድርና ላይ የነበሩ ዜጎችን የሚጨምር ሲሆን፤ ስልጠናውን የወሰዱ አካላትም በተጠባባቂነት እንዲቆዩ ይደረጋል ተብሏል።
በተጨማሪም ያገቡ እና ልጆች ያሏቸው ሴት ወታደሮች ወደ ቀድሞ ወታደራዊ ክፍላቸው እንዲመለሱ ታዝዘዋል።
በወታደራዊ ግዳጁ መመሪያ መሰረት ዕድሜያቸው ከ50 አመት በታች የሆኑ ግለሰቦች ከሀገር እንዳይወጡ የተከለከሉ ሲሆን፤ ይህም የግዳጅ ምልመላው ጥብቅ መሆኑን የሚያመላክት ነው ተብሏል።
የወታደራዊ ግዳጁን መመሪያ ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደቦች ተጥለዋል።
የክልል አስተዳደሮች ለወታደራዊ ግዳጅ የሚመለምሏቸውን ዜጎች የማሰባሰብ፣ የመመዝገብ እና የማሳወቅ ስራ መጀመራቸውንም ዘገባዎች አመላክተዋል።
ለወታደራዊ ግዳጅ ምልመላው ድንገተኛ እና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ቅስቀሳ እየተደረገ ሲሆን፤ ይህም በኤርትራ ህዝብ ዘንድ ድንጋጤ ፈጥሯል።
የኤርትራ መንግሥት ለሌላ ዙር የትጥቅ ግጭት እየተዘጋጀ ነው የሚል ስጋትም እየጨመረ መምጣቱ ተጠቅሷል።
ቀደም ሲል ከወታደራዊ አገልግሎት በተለያየ ምክንያት የወጡትን ጨምሮ የሲቪል ዜጎችን በግዳጅ መልሶ ማሰባሰብ የመንግስትን የማያቋርጥ ወታደራዊ ፖሊሲ እና መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶችን ችላ ባይነት እንደሚያሳይ በውጭ የሚገኙ የኤርትራ ሕዝብ ተቆርቋሪ ሚዲያዎች ዘግበዋል።