እናት መሬት!

ከደምስ በለጠ

እናት መሬት ሆይ! በምድርሽ ላይ ደም እንደውኃ ፈሰሰ ። ጨቋኞች የሰው ስጋ መተሩብሽ ። ወጣቶችሽ እንደዱር አውሬ እየታደኑብሽ ነው ። አዳኞቹ ደግሞ ከሰው የተፈጠሩ አይመስሉም ። ወይ አንቺ እናት መሬት ! እስከመቼ ? እኮ እስከመቼ ? የደም አበላ ይከፈልሽ ! መቼ ይሆን የደም ግብርሽ የሚቆመው ? መቼ ይሆን ለዘንዶው ግብር የሚሰጡ የህጻናት መስዋትነት የሚገታው ? ሴቶችሽ ሃፍረታቸው ተገለበ ! ባልቴት እናቶች ቀሚሶቻቸው በልጆጃቸው ደም ጨቀዬ ። አዝውንቶችሽ የዘመን ክብር ሽበታቸው በወራዶች ተነጨ ፤ ሪዛቸው ተጎተተ ። የአብያተ ክርስቲያናቱ መጋረጃዎች ለጋጠ-ወጦች መከናነቢያ ተሰጡ ። የመስጊዶችን ቅዱስ ቦታዎችን በተበከለ ቆሻሻ እግሮቻቸው አጎደፏቸው ።

ታዲያ የዛሬው ዘመን ወጣት ምን እያለ ይሆን ?

ዘመን የሚያመጣቸው ወይም የሚወስዳቸው ሁነቶች በታሪክ ውስጥ ያጋጥማሉ ። የትላንቷ ኢትዮጵያ ወጣት ለሃገራችን ህዝብ መልካም ዘመን እናመጣለን ከሚል ህሳቤ ፤ በአንድ የፖለቲካ መርሕ ፤ ሆኖም ግን በተለያየ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ በመሰለፍ ፤ ጠመንጃ አንስቶ የአገሪቷን ማእከላዊ መንግስት ተፋልሟል ። የዚህ ትግል ውጤት ዛሬ አገሪቷ ለደረሰችበት ሁኔታ መሰረት ጥሏል ፤ ወይም መንስኤ ሆኦኗል ፤ የሚል ክርክር ውስጥ መግባት አልፈልግም ። ከዚያ አንድ ዘመን ቀደም ብሎ የነበረው ትውልድ ግን ፤ ጊዜው ጎትቶ ከቀየው ድረስ ያመጣበትን የፀረ- ቅኝ ገዢዎች ትግል በታላቅ አርበኝነት ተወጥቷል ። የሃገሪቷንም አንድነት ጠብቆ ለመጪው ትውልድ አስተላልፏል ።

የዛሬው የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ደግሞ ፤ ራሱን ካልጠበቀው ሁኔታ ውስጥ ገብቶ አግኝቶታል ። ይህ ዘመን ፤ የዚህ የአዲሱ ዘመን ወጣት ዘመን ቢሆንም ፤ ራሱ ሳይፈልገው በግድ የተጫነበት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግር ውስጥ ገብቷል ። ፈለገውም አልፈለገውም የዘመናችን ወጣት ፤ የአገሪቱን አንድነት የመጠበቅ ፤ ብሎም ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፍትህ ይመጣ ዘንድ መታገሉ አይቀሬ ይሆናል ። ታዲያ ይህ የዛሬው የኢትዮጵያ ወጣት ለዚህ ይበቃ ይሆን ? ወይስ የቀደሙት የፈፀሙትን አይነት ስህተት ፈጽሞ የሱም ዘመን አገሪቱን ሌላ የችግር አዙሪት ውስጥ ከቷት ያልፍ ይሆን ?

ላለፉት ዘጠኝ ወራት በረዕሰ-ከተማችን በአዲስ አበባ ዙሪያ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና ገጠሮች በመስፋፋት ፤ እስካሁንም እዚህም እዚያም እሳቱ እየነደደ ይገኛል ። ለዚህም የኦሮሞ ወጣቶች የደምና የህይወት መስዋእትነት ከፍለዋል ። አሁንም እየከፈሉ ናቸው ። ዛሬ በጎጃም ደብረ-ማርቆስና ባህር ዳርም የደም ዋጋ እየተከፈለ ነው ። ሌሎችም አካባቢዎች ፤ የመስዋእትነቱ ዋጋ ለመክፈል በዝግጅት ላይ ናቸው ። ይህ ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ፤ ትልቁን ሚና የተጫወተውና አሁንም በመጫወት ላይ ያለው ፤ ስርአቱ ራሱና የስርአቱ ባህርይ ነው ።

በጎንደር የተነሳው ሕዝባዊ እንቢተኝነትና አመፅ በጎንደር ወጣቶች የተመራ ነው ። ይህን አመጽ ለየት የሚያደርገው ደግሞ ያለውን ስርአት ከፍ ያለ ፈተና ውስጥ የከተተ መሆኑ ነው ። የጎንደር ሰው ከመሞት አልፎ ለመግደልም ብረት አንስቷል ። የስርአቱን ገዳይ አግአዚ የተባለውን ጦርም ፈትኖታል ። አግአዚ ጦር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተላከ ያልታጠቁ ሰዎችን ፤ ሴቶችንና ህጻናትን በመግደል ተወዳዳሪ አልተገኘለትም ። ሴት ገዳይ ነው ። ህፃናትን አራጅ ነው ። አግአዚ ፤ በዚህ ጦር ሜዳ ላይ ውሎ ፤ የሃገሪቷን ድንበር አስከበረ ሲባል ታይቶም ተሰምቶ አይታውቅም ። ታዲያ ይህን የአገዛዙን ማስፈራሪያ ዱላ ፤ የጎንደር ሰዎች ፈትነውታል ፤ ዘርጥጠውም ጥለውታልም ።

ከአገራችን ታሪክ ፤ የዛሬ አራት መቶ አመት ወደ ኋላ ተመልሼ አንድ ማጣቀሻ ዋቤ ላደርግ ወደድኩ ። ግራኝ አህመድ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ያደረጋቸው መስፋፋቶች ላይ የተፈጠረ ታሪክ ነው ። “የግራኝ አባት ቄስ የነበረ ሰው መሆኑንና ከግራኝ እናት ጋር አድሮ በጠዋት ለቅዳሴ ሲወጣ ፤ በጥምጥሙ ፈንታ የእስላሟን የግራኝን እናት መቀነት ራሱ ላይ ጠምጥሞ ወደመቅደስ ሊገባ ሲል ፤ ከእስላሟ ጋር ማደሩን ያወቁት ቄሶች ፤ ተሰብስበው በመቋሚያቸው ቀጥቅጠው ገደሉት ። በዚህ ምክንያት አብያተ ክርስቲያናትን ያቃጥል ነበር ።” የሚል ተረት ተረት የኔ ዘመን ትውልድ በልጅነታችን ከካህናት ስንሰማ ቆይተናል ። ለዚህ ተረት ደግሞ አንድም የታሪክ ማጣቀሻ አልተገኘለትም ።

ልክ እንደዚሁ አይነት ሌላ ተረት ተረት ፤ በካህናት ስለግራኝ አህመድ ይነገሩ የነበሩ ፤ ጦር በታኝ የሆኑ ወሬዎች በንጉሱ በአፄ ልብነድንግል ጦር ውስጥ በሰፊው ይወራ ረበር ። ጎንደር ብትሄዱ በአንድ እጁ ግራኝ የተከለው እየተባለ የሚወራለት ቋጥኝ ይኖራል ። ወሎ ላይ ደግሞ የግራኝ ፈረስ በአንድ እግሩ ረግጦ የናደው የተራራ ክፋይ እስካሁን ድረስ ይወሳለታል ። ጎጃም ላይ ወይም ትግራይ ብሎም ሸዋ ላይ ተመሳሳይነት ያላቸው የግራኝ አፈ-ታሪኮች ከዚያ ዘመን ጀምረው እየተወሩ ዛሬ ላይ ደርሰው ሰምተናቸው ይሆናል ። ግራኝ ለአስራ አምስት አመታት ፤ በአንድ የጦር ሜዳ ላይ ሳይሸነፍ ጥቃቱን በንጉሱ ጦር ላይ አዝንቧል ። “ግራኝን እንዴት ማሸነፍ አቃተን ?” ተብሎ በንጉሱ ሰራዊት በኩል ፤ በጊዜው ይነሳ ለነበረው ጥያቄ ፤ የጊዜው ምሁራን የነበሩትና ሁሉን አዋቂ የሚባሉት ካህናት በንጉሱ ጦር ውስጥ የሚነዙት ወሬ ነበራቸው ። ግራኝ ከተራ የሰው ልጅ ውሱን አቅም በላይ ኃይል ያለው ፤ ተራራ የሚንድ ፤ የሚቀመጥበት ፈረስ ራሱ እንደግራኝ ሁሉ የታሰረበትን ዋርካ ነቅሎ የሚሄድ ፤ ልክ እንደ ዛሬው የአሜሪካን የፊልም ኢንዱስትሪ ፈጠራ “ሱፐር ማን” አይነት ባህርይ ይሰጡት ነበር ።

ስለዚህ የግራኝ ጦር መጥቶ ለውጊያ ከንጉሱ ጦር ፊት ሲቆም ፤ የሁሉም የንጉሱ ወታደር ጥያቄ ፤ ይህን የእስላሞቹን ጦር እየመራ ያለው ማነው የሚል ይሆናል ። የጦሩ አዝማች ግራኝ መሆኑን ያወቀ የንጉሱ ወታደር የአቅሙን ያህል ከመዋጋቱ በፊት ፤ ቀድሞ በሰማው መሰረት ፤ በምናቡ የፈጠረውን የግራኝ ሃያልነትን ሲያስብ ፤ አስቀድሞ ወኔው ከድቶታል ። ያን በምናቡ ካህናቱ የሳሉበትን ፤ በአካል የማያውቀውን ጎልያድ እንደማይችለው በማሰብ ለሽሽት ይዘጋጃል ። እንደዚያ ዘመን ሰው አስተሳሰብ ፤ ይህን አስፈሪ የሰይጣን ቁራጭ ጎልያድ ፤ አንድ የፖርቱጋል ወታደር በአንድ ጥይት በጌምድር ላይ ሲያጋድመው ፤ የአበሻ ወታደር ተመልክቶ “ግራኝ ማለት ይህ ነው እንዴ ?” ብሎ በእጅጉ ሳይገረም አልቀረም ።

እንደዚሁ ሁሉ ፤ ይህን ህፃናትና ሴቶች ገዳይ የሆነውን ጦር ጎንደሮች እንደ ግራኝ ሁሉ ሞክረው አጋድመውታል ። ጎንደር የተበላሸውን ሲያስተካክል የተጣመመውን ሲያቃና ይህ የመጀመሪያው አይደለም ። ሱስንዮስ የሻረውን ፋሲለ-ደስ አቅንቶታል አገሩንም አረጋግቶ ሰላምን መልሷል ። ይህ የሆነው ጎንደር ላይ ነው ።ስሁል ሚካኤል ንጉሱን በሻሽ አስንቆ ገድሎ ፤ ያፈረሰውን ማዕከላዊ መንግስት ፤ ጎንደር (ጎን እደር) ግንባሩን ለሃሩር እግሩን ለጠጠር ሰጥቶ ፤ የአዲሲቱን ኢትዮጵያ መሰረት እንደገና ከቴዎድሮስ ጋር ጥሏል ። ዛሬም እንደ ጥንቱ የአባቶቹን ሰንደቅ በክብር ወደቦታው መልሷል ። ታሳሪዎች ለጅብ እንዳይሰጡ ከጎናቸው ቆሟል ። በአድማ ምክንያት ድሆች እንዳይራቡ ያለውን አካፍሎ አብሮ በልቷል ። ይህን የመሰለ ማሕበራዊ ፍትህ ደግሞ የነገ ብሩህ ተስፋነት ጠቋሚ ምልክት ነው ። ለጎንደር ምን ይህ ብቻ ! ስንት የሚወሳ ታሪክ አለው መሰላችሁ ። የጨለማው ዘመን በሚባልበት ዘመን እንኳ ፤ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በእውነተኛ ዲሞክራሲ በምርጫ ስልጣን የሰጠ ህዝብ ጎንደር ነው ። ይህን ታሪክ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ ።

ዛሬ ታዲያ ፤ ኦሮሞዎችም አማራዎችም የደም ግብር እየከፈሉ ነው ። ወደ አንድነትም በመምጣት ፤ የነፃነታቸው መአዛ ፤ የት ላይ እንደሚገኝ ቀምሰው አውቀውታል ። ከእንግዲህ ይህ ትውልድ ጠመንጃ ያነሳ ዘንድ ተገዷል ። ጠመንጃ ካነሳ ደግሞ ፤ ለሴቶች ገዳዩ አጋዚ ፤ ህዝባዊ አጋዚ ይሆንበታል ፤ ያለርህራሄም እየጣለ ይወድቃል ። ህዝባዊ አመፁ በመላዋ ሃገሪቱ ተቀጣጥሎአል ። የተንበረከከ ፈሪ ነው ፤ የቆመ ደግሞ ለመተናነቅ ዝግጁ ነው ።ተንበርክኮ የነበረው ዛሬ ተነስቶ ቆሟል ።

እዚህ ላይ ለሚዲያዎች የማስተላልፈው አንድ መልእክት አለ ። ዜና ተገኘ ተብሎ ዝም ብሎ አይረጭም ። “ከትግራይ የተነሳ በሰላሳ ኡራል መኪና የተጫነ ወታደር ወደ ጎንደር እየተጓዘ ነው ። ወደ ባህርዳር የሚጓዝ ፤ ታንክና መትረየስ የጫኑ ወታደራዊ መኪናዎች በሸራ ተሸፍነው በጎሃ ፅዮን በኩል ታዩ ፤” ወዘተርፈ…… እየተባሉ የሚለቀቁ ዜናዎች ፤ የተነቃቃው ህዝባዊ እንቢተኝነት ላይ ቀዝቃዛ ሽብር መቸለስና ፤እንደግራኝ ዘመን ካህናት ትጥቅ አስፈቺና ጦር በታኝ ወሬ ስለሚሆን ፤ እየታሰበበት ቢለቀቅ መልካም ነው ። ሰዎች በዘመናት በራሳቸው ውስጥ ያዳበሩትንና ያሳደጉትን ፍርኃት አላቸው ። ዛሬ ከጨቋኞች መትረየስ ፊት ፤ ያለ ምንም ፍርኃት ፤ ለመብቱና ለነፃነቱ ሊተናነቅ ቀጥ ብሎ የቆመ ወጣት ተፈጥሯል ።

በዚህ ለነጻነቱና ለክብሩ በቆመ ነፃ ወጣት ስነልቡና ውስጥ ፤ በዜና ስም የራስን የፍርኃት ቆፈን እየሰነቀሩ ሊተናነቅ የቆመውን እንደገና እንዲምበረከክ ግፊት ማድረግ ፤ ተገቢ አይደለም ። ይህ አይነቱን የዜና አቀራረብ ወገን ነኝ በሚል ሚዲያ ማስተላለፍ ፤ ለጠላት ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ መሆንን ያመጣል ። ጦርነቱ የጠመንጃ ብቻ ሳይሆን የፕሮፓጋንዳ ጭምር ነውና።

እየኖረ በየቀኑ ከመሞት ፤ ዛሬ ጥሎ መውደቅን የመረጠ ወጣት አለ ። ይህ ወጣት ደግሞ ፤ ጎረቤት አገሮችን አስጠልሉኝ ብሎ የሙጥኝ ተጠግቶ ሳይሆን ፤ በራሱ አገር በራሱ ምድር ላይ ፤ ቀጥ ብሎ ቆሟል ። በዚህ ቆራጥ በሆነ ፤ የዚህ ዘመን ትውልድ ላይ ፤ በልማድ የተገኘ ፍርኃት ቆፈን ማልበስ የማይሰረይ ሃጢያት ይሆናል ። በዚህ ለነፃነት ሲባል ፤ እየጣሉ የመውደቅ ዘመን ላይ ፤ ነጻነት ናፋቂ ሁሉ ፤ ስለ ነፃነት እንጂ ስለ ግል ግብና ስለድርጅት ፕሮፓጋንዳ ማሰብ ግምኛ ነው ።

ለዚህ ደግሞ ጎንደሮች የተከተሉት ፤ የትግል አቅጣጫ ፤ ጎንበስ ተብሎ እጅ ሊነሳው የሚገባ ታላቅ ተግባር ነው ። ትግሉ ገና “ሀ” ብሎ መሰረት ሲጥል ፤ አገዛዙ ሊለጥፍባቸው ከሚችለው ውንጀላዋች ፈውስ ይሆን ዘንድ ፤ ትግሉ ህዝባዊ ነው እዚሁ ተወልዶ እዚሁ ያደገ ነው ፤ ማንም ውጪ ያለ ድርጅት በኛ ስም መግለጫ እንዳያወጣ ፤ ሲሉ የባይረስ ማርከሻውን ፔኒሲለን ወግተው ነው ትግሉን የጀመሩት ። ቀጥለውም በአገሩ ምድር ላይ ቆሞ የሚሞተው ኦሮሞ ወጣት ደም የኛም ደም ነው አሉ ። ኦሮሞውም አፀፋውን በመመለስ ከአዳማ አስከ ነቀምቴ አልፎም እስከ ባሌ ሮቤ ድረስ የሚፈሰው የአማራ ደም የኔ ደም ነው አለ ። ዛሬ ሁሉም በተጠንቀቅ ዘብ ቆሟል ።

የጎንደር ወጣቶች ፤ ከእስረኞች ይፈቱ እስከ ስራ ማቆም አድማ የዘለቀ ትግላቸውን እየመሩ ያሉት ከነመፍትሄው ፤ ከነመድሃኒቱ እዚያው ጎንደር ውስጥ ነው ። ሁሉም ደግሞ ትግሉን እንደ ጎንደሮች ቢያቀናጅ የበለጠ ውጤት ሊገኝ ይችላል ። የጎንደር ወጣቶች ዛሬ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ነው ። ትግሉ የተናጠል እንዳይሆንም የኦሮሞና የአማራ ወጣቶች የግንኙነት መስመራቸውን ባስፈላጊው መንገድ ሁሉ ከትልቁ ፤ እስከትንሹ ዘዴ በመጠቀም አብሮ የመስራት ባህላቸውን ሊያዳብሩ ጊዜው የግድ ይላል ። ወጣቶች ይህ ቀረሽ የማይባል የፈጠራ ችሎታ እንዳላችሁ አሌ አይባልም ፤ ዘመኑ የናንተ ነውና ። ይህን ድንቅ የሆነ ዘመናችሁን በአንድነት በእጃችሁ አስገብታችሁ ራሳችሁ ተቆጣጠሩት ። አለበለዚያ የናንተ ወርቃማ ዘመን ለሌሎች ቁማር መጫወቻ ይሆናል ። ከፊታችሁ ታላቅ ሃላፊነት ተደግኗል ። ( በዚህ አጋጣሚ ፤የራሱን ዘመን በራሱ መንገድ ተቆጣጥሮ በትግራይ ተራሮች ታልቅ ገድል ስለፈፀመው ስለ አስራሰባት አመቱ ወጣት ስለአብቹ ታሪክ ደግሞ በሚቀጥለው ፅሁፌ አቀርብላችኋለሁ ። “አብቹ ነጋ ነጋ” ።)

መግቢያዬ ላይ ያስቀመጥኳቸው ጥያቄዎች አሉ ። ልድገማቸው ። ወጣቱ በራሱ ዘመን ፤ ሳይፈልገው በግድ የተጫነበት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግር ውስጥ ገብቷል ። ፈለገውም አልፈለገውም የዘመናችን ወጣት ፤ የአገሪቱን አንድነት የመጠበቅ ፤ ብሎም ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፍትህ ይመጣ ዘንድ መታገሉ አይቀሬ ይሆናል ። ታዲያ ይህ የዛሬው የኢትዮጵያ ወጣት ለዚህ ይበቃ ይሆን ? ወይስ የቀደሙት የዚያ ዘመን ወጣቶች የፈፀሙትን አይነት ስህተት ፈጽሞ ፤ የሱም ዘመን አገሪቱን ሌላ የችግር አዙሪት ውስጥ ከቷት ያልፍ ይሆን ?

የዛሬውን ወጣት ከትላንትናዎቹ ለየት የሚያደርገው የርእዮተ-አለም ቃልኪዳን እስረኛ አለመሆኑ ነው ። የዛሬው ወጣት ግብ አንድና አንድ ብቻ ነው ። ለራሱና ለህዝቡ ነጻነትና ፍትህን ማስፈን ብቻ ። እንዳያያዙ ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፍትህ ያሰፍናል የሚል ግምት አለኝ ። ትግሉ የነፃነት ነው ሲል ወጣቱ ፤ የነፃነት ብቻ ነው ። ነፃነት በራሱ ፍትህ ነው ። ነፃነት ሰላም ነው ። ነፃነት ፍቅር ነው ። ስለዚህም በአማራና በኦሮሞ ወጣቶች መካከል ፤ አገዛዙ አስፍኖት የነበረው የጥላቻ መጋረጃ ተቀዷል ። እንደገና የታደሰው የወጣቶቹ አንድነት በሃገራችን ላይ ፍትህ ሰላምና ፍቅር ያሰፍናል ። የሰው ልጆች ታሪክ እንደሚያሳየው ፤ ነጻነት ከምንም ነገር በላይ ጣፋጭ ናት ። ሆኖም ግን ዋጋ ታስከፍላለች ። የኦሮሞ ወጣት ላለፉት ዘጠኝ ወራት ለነጻነት ህይወቱን እየከፈለ ነው ። ጎንደር ከነብረቱ እምቢ ለነፃነቴ ብሎ ደሙን እየከፈለ ነው ። ጎጃም ከነድፍረቱ በባዶ እጁ ህይወቱን እየባጀ ነው ። ይህ የነጻነት ተጋድሎ በመላ አገሪቱ እየተቀጣተለ ነው ። እሳቱም ጨቋኞችን እየለበለበ ፤ እስከወዲያኛው ይዟቸው ይሄዳል ። እናት መሬትም ታብባለች ። ወጣቱ ለነጻነት የሚያደርገው ትግል ፤ ለወደፊቱ ትውልድ ፍንትው ብላ የምትታይ ከዘረኝነትና ከትምክህት የፀዳች ብሩህ ፤ መሪ ኮከብ ትሆንለታለች የሚል ተስፋ ሰንቄ ፤ የዛሬውን ፅሁፌን አበቃለሁ ።

በፅሁፉ ላይ አስተያየትም ሆነ ፤ ትችት ካላችሁ ፤ እነሆ የኢሜል አድራሻዬ [email protected] .

ላስ ቬጋስ ኒቫዳ
ኦገስት 20/2016 እ.ኤ. አ.


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE