የዐማራን ተጋድሎ ከእንግዲህ ማንም ሊጠልፈው አይችልም!

የዐማራን ተጋድሎ ከእንግዲህ ማንም ሊጠልፈው አይችልም! Muluken Tesfaw

(ዐማራ የሚለውን ቃል የማይጠቀሙ በውስጣቸው የታመቀ ጥላቻ ያለባቸው ወይም የሚፈሩ ናቸው)

ስጋ በወደቀበት ቦታ ሁሉ ብዙ አሞራዎች ለመንጠቅ ይሮጣሉ፡፡ የዐማራውን ተጋድሎ ለመጥለፍ የሚሞክሩ ብዙ ግለሰቦች (ቡድኖች) ይኖራሉ፡፡ ይህን ማንም ያውቃል፡፡ ግን ከዚህ በኋላ አይደገምም፡፡ ማንኛውም አሁን ያለውን የአገራችን ሁኔታ የሚገነዘብ ዐማራ ትግሉን አያስጠልፍም፡፡

አንዳንዶች ከሌሎች የአገራችን ሕዝቦች ጋር ሊያጋጩን ይፈልጉ ይሆናል፤ እኛ ግን ከወያኔና ግበረ አበሮቹ ውጭ ጠላት የለንም፡፡ በራሳችን ቤት ስለራሳችን ብቻ እንመክራለን፡፡ ሌሎችም ስለራሳቸው እየመከሩ ነው፡፡ ያኔ እንደጋገፋለን፡፡ አሁን ግን የራሳችን በደል ከፍ አድርገን እንዲሰማ እንተጋለን፤ ለውጥ እስኪመጣ እንጋደላለን፡፡

ሁሉም ሰው እንዲገነዘበው የሚያስፈልገው ጉዳይ አለ፤ ይህን የዐማራ ሕዝብ ተጋድሎ እየመራው ያለው ራሱ ሕዝቡ ነው፡፡ ማንም የለበትም፡፡ የሕወሓትና ግበረ አበሮቹ ጭፍጨፋና ግድያ ከሕዝባችን ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስኪወገድ ድረስ የዐማራ ሕዝብ ተጋድሎውን ይቀጥላል፡፡ የዐማራ ሕዝብ ድምጽ ከኬፕ ቨርዲ እስከ ኬፕ ጋርዳፊ ከባብኤል መንደብ እስከ ስትሬት ኦፍ ጂብላርታር አፍሪካን ያነቃንቃል፡፡

በዚሁ ሁሉ የዐማራ ተጋድሎ ትግሉን የሚደግፉ አካላት አይነቀፉም፡፡ ግን ትግሉን ወደ ሌላ አቅጣጫ ወይም ደግሞ ‹‹አዛኝ ቅቤ አንጓች›› መሠል ሰዎችንና ቡድኖችን እኩል ከወያኔ እንዋጋቸዋለን፡፡ ምክንያቱም የዐማራ ተጋድሎ ባሕሪው ነውና፡፡ ዐማራ ይችላል፤ ትግስተኛ ነው፡፡ ዝም ይላል፤ እስኪማሩ ይጠብቃል፡፡ ግን ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው ያለው ማን መሰላችሁ? ዐማራ እኮ ነው!!

በዚህ ጽሑፍ ከዚያና ከዚህ አሁንም ሰማያዊ ፓርቲን ለመሳደብ የተዘጋጀ የሚመስላቸው ሰዎች ይኖራሉ፡፡ አያውቅንማ!! ሰማያዊ ፓርቲዎች የዐማራውን ሕዝብ ተጋድሎ አያኮላሹም፤ ያግዛሉ የሚል ጸኑ እምነት አለን፡፡ ምክንያቱም ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን በሚገባ አውቃቸዋለሁና፤ ሰማያዊዎቹ የዐማራ ሕዝብ ጠላት አይደሉምና፡፡

የዐማራ ሕዝብ ተጋድሎ የባለቤነት መብት ለመውሰድ ሽሚያ አይገባም፡፡ የዐማራ ሕዝብ ተጋድሎ ግብ በላያችን ላይ የተጫነውን መርገም፣ የመኖር ሕልውናችን የነጠቀንን ሥርዓት ማሽቀንጠር ነው፡፡ ይህንም የዐማራ ሕዝብ ያደርገዋል፡፡ ባለቤቱም ራሱ ሕዝቡ ነው፡፡

የዐማራ ሕዝብ ለምን በበላይ ዘለቀ ይምላል? እስኪ ጎጃም ሒዱ፡፡ ስንት አባት ልጁን ‹‹በላይ›› ብሎ እንደሚጠራ ታውቃላችሁ? በላይ የወንዶች ቁና!! አዎ ጎጃም ጣሊያንን ያረበደበደ፤ የወንዶች ቁና የሆነውን በላይ ዘለቀን ያበቀለ አገር ነው፡፡ ሸበል በርንታ ጫካው ይጣራል፡፡ የጮቄ ተራራ፤ የአዳማ ነፋስ፣ የጎንጅ ሰዋሰው፤ የዲማ ቅኔ የሚዘረፈው ስለነጻነት ነው እኮ!! አገው ምድር ጎጃም፣ የቻግኒና የመተከል ጫካዎች በዐማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደልና ጭፍጨፋ ያወግዛሉ፤ ለነጻነትም ይጋደላሉ፡፡ ከቡሬ እስከ ሽንዲ፣ ከቆላ ደጋ ደጋ ዳሞት እስከ ደንበጫና ፈረስ ቤት፣ ከመንቆረር ደብረ ማርቆስ እስከ ሉማሜና ደጅን አዎበል፣ ሞጣና እነሴዎች፣ (ስንቱን ዘርዝረን እንዘልቀዋል) የዓባይ ወንዝ ብቻ ሳይሆን የነጻነትም መፍለቂያ ምድር ነው፡፡

ዐማራውን ትግል ለማኮላሸት ለሚሞክሩ ሁሉ

የዐማራው ሕዝብ በራሱ መሬት በመተከል ሲታረድ፣ በወለጋ ሲቃጠል፣ የራስ ቅሉ ሲቆረጥ፣ በወልቃይት ከነነፍሱ ሲቀበር፣ የራያ ዐማሮች በግዴታ ትግሬ ሲሆኑ፣ በበደኖና አርባ ጉጉ ቆዳቸው ሲገፈፍ፣ በጉራ ፈርዳ ጫካዎች ቀባሪ አጥተው ሲቀሩ ማን ድምጹን አሰማ? ማንም ነው መልሱ፡፡ ያኔ ድምጻቸውን ያላሰሙ አሁን የዐማራውን ሕዝብ ትግል ለመጥለፍ ሲጥሩ ማየት በሕዝባችን ላይ የተደገሰው ጥፋት መጠኑ ምን ያክል እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግተንም፡፡

ስለዚህ እነዚህ አካላት በዐማራነታችን የሚደርስብንን ግድያና ዘር ማጥፋት ለመመከት የምናደርገውን ተጋድሎ ለመጥለፍ የሚያደርጉትን ሩጫ ሁሉ አብረን እኩል ከወያኔ እንታገላቸዋለን፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል እንዲሉ እስካሁን ለአገር አንድነት ስንል የታገስነውን ከሞኝነት ከቆጠሩት ዋጋቸውን እንሰጣለን፡፡

(በባሕር ዳር እና በሎሎች የዐማራ አካባቢዎች የሚደረጉ ሰልፎችን ዝግጅት በየጊዜው እናቀርባለን)

ይህ የመጨረሻው መጀመሪያ ነው!!

የዐማራ ሕዝብ ትግል ያሸንፋል!!


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE