በሰንዳፋ ያሉ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች የአዲስ አበባ ቆሻሻ ከዚህ በኋላ እንዳይመጣብን ሲሉ ከለከሉ።

በአዲስ አበባ ካለፈው ሣምንት ጀምሮ ለ7 ቀናት በዋና ዋና የከተማዋ አውራ ጎዳናዎች፣ መንደሮች እንዲሁም ገንዳዎች ቆሻሻ ተከማችቶ ሰንብቷል…

የቆሻሻ ማንሻ መኪኖች የተሸከሙትን ቆሻሻ የሚያራግፉበት አጥተው ቆመዋል፡፡

ለወትሮው የከተማዋን ደረቅ ቆሻሻ ሸክፈው ሰንዳፋ ወደሚገኘው ዘመናዊ የቆሻሻ መጣያ ቦታ መሄድ የነበረባቸው እነዚሁ መኪኖች ወደ ሰንዳፋ ማቅናት አልሆነላቸውም፡፡

ሸገር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ ዳዊት አየለ ጋር ስለ ሰሞኑ የፅዳት ችግር ተነጋግሯል፡፡

አቶ ዳዊት ከመኖሪያ ቤትና ድርጅቶች ከሌሎችም ተቋማት የተሰበሰበው ቆሻሻ በወጉ ሊወገድ አለመቻሉን ተናግረው የቆሻሻ ክምር ወደ ሰንዳፋ ወስዶ ለመጣል ጊዜያዊ የተባለ ችግር ተፈጥሯል፡፡

SHEGER FM 102.1 RADIO's photo.

በሰንዳፋ ያሉ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች የአዲስ አበባ ቆሻሻ ከዚህ በኋላ እንዳይመጣብን ሲሉ መከልከላቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ የየዕለት ደረቅ ቆሻሻ እየተረከበ በዘመናዊ መንገድ ለማስወገድ እንዲረዳ ተብሎ በሰንዳፋ የተገነባው የቆሻሻ መረከቢያ ማዕከል በዚህ ሰሞን አገልግሎቱን አቋርጧል፡፡

ከ7 ዓመት በፊት ይህ ማዕከል ስለሚሰጠው አገልግሎት መንግሥት ግልፅ ውይይት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ማድረጉንና ተቀባይነትንም እንዳገኘ የሚያስታውሱት አቶ ዳዊት የፅዳት አስተዳዳር ሥራ አስኪያጅ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ ቆሻሻው ሸቶናል መሠረተ ልማት ይሟላልንና ሌሎች ጥያቄዎች ማንሣት ጀምሯል ይላሉ፡፡

በሰንዳፋ ያለው ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ማዕከል ሥራ ከጀመረ መንፈቅ አልፎታል፡፡ በዚህ ሣምንት ግን ቆሻሻውን መረከብ በማቆሙ ምክንያት ከተማዋ ቆሽሻ ሰንብታለች፡፡

የአዲስ አበባን ቆሻሻ ለረዥም ዘመናት ሲቀበል የከረመው ረጲ ተመልሶ እንዳይከፈት ሆኖ ተዘግቷል የሚሉት አቶ ዳዊት የከተማዋን ቆሻሻ በማስተናገድ በኩል የ50 እና የ60 ዓመት አገልግሎት እንዲሰጥ የተዘጋጀው የሰንዳፋ ማዕከል አሁን የተፈጠረበትን ጊዜያዊ ችግር ለመፍታት ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው ትናንት ከሰንዳፋ አካባቢ ቅሬታ አቅራቢዎች ጋር ድርድር ማካሄዱንና የድርድሩ ውጤት ለጊዜው እንዳልሰመረ ሰምተናል፡፡

(ሕይወት ፍሬስብሃት)

 
 

► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE