የአእላፍ ቅዱሳን ሀገር ኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌ ዐጣችን?
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
(ቁም ነገር መጽሔት፤ 15ኛ ዓመት ቅጽ 15 ቄጥር 264፤ መስከረም 2008 ዓ.ም.)
/ተክለ ኪዳን አምባዬ/
በቅርቡ ለአራተኛ ጊዜ የበጎ ሰው ሽልማት መካሔዱ ይታወሳል፡፡ ከሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ቀደም ብሎ ስለዝግጅቱ በተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ ለፕሮግራሙ አዘጋጆች ከጋዜጠኞች የቀረበ አንድ ጥያቄ ነበር፡፡ የበጎ ሰው ሽልማት ከሚሸልምባቸው ዘርፎች መካከል፣ ‹‹የዓመቱ የሰላም ሰው›› የሚል ነበር፤ ነገር ግን ዘንድሮ የለም፤ ለምንድን ነው? የሚል ነበር፡፡ ከፕሮግራሙ አዘጋጆች አንዱ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ‹‹ለዘንድሮ ብቻ ሳይኾን ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የዓመቱን የሰላም ሰው ለመሸለም ዝርዝራችን ውስጥ ነበር፤ ነገር ግን የሰላም ሰው ብለን የምንሸልመው መስፈርቱን የሚያሟላ ሰው ባለማግኘታችን ልንሸልም አልቻልንም፡፡›› ከአገራችን 90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ውስጥ ለተከታታይ ዓመታት አንድም የሰላም ሰው መፍጠር አለመቻላችን፣ ማኅበረሰባችን ሕመም ላይ መኾኑን አመላካች ነው፡፡
መነሻ ኹለት
ባለፈው ሳምንት እሑድ በተከበረው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ማግሥት፣ አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣ ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ‹‹የወቅቱን የሀገሪቱን ችግር በውል ተገንዝቦ ሀገር የሚያስማማ ሰው ጠፍቷል፤ የሀገር ሽማግሌ የሚባል የለም፤ የሃይማኖት መሪዎቹም ትኩረታቸው ሌላ ነገር ላይ ኾኗል፤ ሀገሪቱ የጎረምሳ ሀገር ኾናለች፤›› ብለው ነበር፡፡
ርግጥ ነው፤ አገራችን ታማለች፤ በሕዝቦች መካከል ከዚኽ በፊት ያልታየ ቅራኔ ተፈጥሯል፡፡ ዜጎች ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ጉዳዩ በመንግሥት እና በሕዝብ በኩል በተለያየ መነጽር እየታየ ገመዱ እየተጎተተ ነው፡፡
በአንድ አገር የዚኽ ዓይነት ውጥረት ሲከሠትና የሰላም አየር ሲበከል፣ ‹አለን› ማለት ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ዝምታ አነጋጋሪ ነው፡፡ የአገራችን መረበሽም ኾነ መፍረስ አንድ ወገንን ብቻ በመጉዳት እንደማይቆም ግልጽ ነው፡፡ በእሳት ዳር ያሉ ማናቸውንም ግለሰቦች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ እሳቱ መብላቱ አይቀርም፡፡ ባይበላ እንኳ መጥፎ ጠባሳውን ትቶ እንደሚያልፍ በሌሎች አህጉር የታየው እውነታ ምስክር ነው፡፡
አገር በታመመችበት ወቅት፣ ‹‹አንተም ተው! አንተም ተው!›› ማለት ያለባቸው አካላት እና ዜጎች ጉዳዩን በቸልታ መመልከታቸውና ግድየለሽነታቸው ሊፈጥር የሚችለው አደጋ፣ እንደ ሩዋንዳ ያሉ አገሮች ያለፉበትን የእርስ በርስ እልቂት የልጆች ጫዋታ ሊያስመስል ይችላል፡፡
አገር በፖሊቲካ ብቻ አትመራም፡፡ በሃይማኖት፣ በሞራል እና በዕውቀት ጭምር እንጂ፡፡ ይህን ማኅበረሰባዊ ሓላፊነት የተሸከሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ፖሊቲካውን ወደ ጎን ትተው ስለ አገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመምከር ሊሰበሰቡ ይገባል፤ ከውጥረቱም ኾነ ሊነድ ካለው እሳተ መዓት ለመዳን ሐሳብ ሊያዋጡ፣ ምክር ሊለግሡ በሚገባቸው ሰዓት ላይ ያለን ቢኾንም፤ ዳር ቆመው የመመልከታቸው አመክንዮ ግልጽ አይደለም፡፡
ጉዳዩ የኹሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጉዳይ ቢኾንም፣ ተደማጭ የሚባሉ አካላት አጀንዳ አዘጋጅተው ኅብረተሰቡ ተቀራርቦ ሊነጋገር የሚችልበትን መድረክ ሲያፈላልጉ አይታይም፡፡ ከዚኽ ነፃ እና ገለልተኛ ውይይት የሚፈልቀው ሐሳብ፣ ኹሉንም ወገኖች የሚገሥጽና ተግባራዊ መረጋጋት እንዲመጣ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ የውይይት መድረክ የአገሪቱን ሕዝቦችንም ኾነ የፖሊቲካ ኃይሎች ወደ ብሔራዊ ዕርቅ እና ወደ ብሔራዊ መግባባት ጠረጴዛ ሊያመጣቸው ይችላል፡፡
የሃይማኖት አባቶች ሚና
ባለፉት ኃምሳ ዓመታት፣ በኢትዮጵያ ያሉ የሃይማኖት አባቶች ከፖሊቲካ ሥርዓቱ ተነጥለው ለመቆም ያደረጉት ጥረት አነስተኛ በመኾኑ ሳቢያ፣ የወቅቱ ዓይነት ችግር ሲከሠት ኅብረተሰቡ ከሃይማኖት አባቶች ተስፋ የሚያደርገው የአስታራቂነት ሚና ጠባብ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ እንዲያውም ግልጽ በኾኑ መድረኮች ሳይቀር፣ ሕዝቡ ለሃይማኖት አባቶቹ ያለው ግምት እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ፣ አገራችን የዚኽ ዓይነቱ ችግር ሲገጥማት ዓይኑን ወደ ሌሎች ማማተር ጀምሯል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ሚና ላልቶ መታየቱም፣ ሊሰጣቸው ይገባ የነበረውን የአስታራቂነት ሚና አላሳጣቸውም ማለት አይቻልም፡፡
የሃይማኖት አባቶች ወደ አመራር የሚመጡበት መንገድ ፍጹም መንፈሳዊ ኾን ሲገባው፣ በአንድም ኾነ በሌላ መንገድ የመንግሥታት እጅ መኖሩ ለተቀመጡበት ወንበርና ለተሠየሙበት መንፈሳዊ ሕይወት ታማኝ እንዳይኾኑ ጋሬጣ ኾኖባቸው ቆይቷል፡፡ አገራችን በሕገ መንግሥት ደረጃ፣ መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ መኾናቸውን፣ አንዱ በሌላው ጣልቃ እንደማይገባ በግልጽና በማያሻማ ኹኔታ የተደነገገ ቢኾንም፤ አብያተ ክርስቲያንና አብያተ መስጊዶች፣ የመንግሥት ካድሬዎች መፈንጫ መኾናቸው የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡
በአገራችን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለታየው አለመረጋጋትና ረብሻ፣ የሃይማኖት አባቶች ሊጫወቱ ይገባ የነበረውን ሐቀኛ ሚና ሳይወጡ በመቅረታቸው ሳቢያ ውጥረቱ ከሯል፡፡ በሰባት የእምነት ተቋማት ከአምስት ዓመታት በፊት፣ ‹‹የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ›› የተሰኘ ማኅበር መመሥረቱ ይታወቃል፡፡ በአኹኑ ወቅት የሚመራው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ነው፡፡
‹‹በመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር ዕሴታችንን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ›› በሚል መርሕ በ2003 ዓ.ም. የተመሠረተው ይህ የእምነት ተቋማት ጉባኤ ዋና ዓላማው፣ በእምነቶች መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት እንጂ በትውልዱ መካከል ስለሚነሡ ልዩ ልዩ ቅራኔዎች መፍትሔ ለማበጀት የሚችል አያስመስለውም፡፡ ጉባኤው የተመሠረተው በምእመናን ፍላጎትና ይኹንታ ሳይኾን በመሥራች የእምነት ተቋማቱ ዋና ዋና መሪዎች ፍላጎት መኾኑ ደግሞ፣ ወደ መንበሩ ከመጡበት መንገድ ፍትሐዊነት ጋር የተያያዘ ያደርገዋል፡፡ ችግር ሲደርስ ብቻ ወደ ብዙኃን መገናኛ ብቅ እያሉ መንግሥት ለወሰደው ርምጃ ቡራኬ የመስጠት አካሔድ፣ የጉባኤውንና የተቋማቱን ተኣማኒነትና መንፈሳዊነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ የከተተው ኾኖ ይገኛል፡፡
ባለፈው ዓመት በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልሎች ከአዲስ አበባ የማስተር ፕላን ማስፋፊያ ጋር በተያያዘ ረብሻ በተቀሰቀሰበትና ብዙዎች ሕይወታቸውን ባጡበት ወቅት፣ በየካቲት ወር የተሰበሰበው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው፣ ‹‹ለደረሰው የሰው ሞት አዝነናል›› ከማለት ውጭ፣ ግድያውንና ደም መፋሰሱን ሊያወግዝ አለመቻሉ የተጠበቀ ነገር ኾኗል፡፡
የሃይማኖት አባቶች፣ ኢ-ሰብአዊ እና ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸም፣ ለምን ብለው መጠየቅ ባይችሉ እንኳ፣ ለድርጊቱ ቡራኬ መስጠት በሚመስል አኳኋን መግለጫ ማውጣታቸው፣ በተኣማኒነታቸው ላይ ጥላ አላጠላም ማለት አይቻልም፡፡ ከዚኽ አለፍ ሲልም፣ የሰዎች ሕይወት አላግባብ ሲያልፍ መነሻ አንድ
በቅርቡ ለአራተኛ ጊዜ የበጎ ሰው ሽልማት መካሔዱ ይታወሳል፡፡ ከሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ቀደም ብሎ ስለዝግጅቱ በተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ ለፕሮግራሙ አዘጋጆች ከጋዜጠኞች የቀረበ አንድ ጥያቄ ነበር፡፡ የበጎ ሰው ሽልማት ከሚሸልምባቸው ዘርፎች መካከል፣ ‹‹የዓመቱ የሰላም ሰው›› የሚል ነበር፤ ነገር ግን ዘንድሮ የለም፤ ለምንድን ነው? የሚል ነበር፡፡ ከፕሮግራሙ አዘጋጆች አንዱ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ‹‹ለዘንድሮ ብቻ ሳይኾን ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የዓመቱን የሰላም ሰው ለመሸለም ዝርዝራችን ውስጥ ነበር፤ ነገር ግን የሰላም ሰው ብለን የምንሸልመው መስፈርቱን የሚያሟላ ሰው ባለማግኘታችን ልንሸልም አልቻልንም፡፡›› ከአገራችን 90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ውስጥ ለተከታታይ ዓመታት አንድም የሰላም ሰው መፍጠር አለመቻላችን፣ ማኅበረሰባችን ሕመም ላይ መኾኑን አመላካች ነው፡፡
መነሻ ኹለት
ባለፈው ሳምንት እሑድ በተከበረው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ማግሥት፣ አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣ ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ‹‹የወቅቱን የሀገሪቱን ችግር በውል ተገንዝቦ ሀገር የሚያስማማ ሰው ጠፍቷል፤ የሀገር ሽማግሌ የሚባል የለም፤ የሃይማኖት መሪዎቹም ትኩረታቸው ሌላ ነገር ላይ ኾኗል፤ ሀገሪቱ የጎረምሳ ሀገር ኾናለች፤›› ብለው ነበር፡፡
ርግጥ ነው፤ አገራችን ታማለች፤ በሕዝቦች መካከል ከዚኽ በፊት ያልታየ ቅራኔ ተፈጥሯል፡፡ ዜጎች ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ጉዳዩ በመንግሥት እና በሕዝብ በኩል በተለያየ መነጽር እየታየ ገመዱ እየተጎተተ ነው፡፡ በአንድ አገር የዚኽ ዓይነት ውጥረት ሲከሠትና የሰላም አየር ሲበከል፣ ‹አለን› ማለት ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ዝምታ አነጋጋሪ ነው፡፡ የአገራችን መረበሽም ኾነ መፍረስ አንድ ወገንን ብቻ በመጉዳት እንደማይቆም ግልጽ ነው፡፡ በእሳት ዳር ያሉ ማናቸውንም ግለሰቦች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ እሳቱ መብላቱ አይቀርም፡፡ ባይበላ እንኳ መጥፎ ጠባሳውን ትቶ እንደሚያልፍ በሌሎች አህጉር የታየው እውነታ ምስክር ነው፡፡
አገር በታመመችበት ወቅት፣ ‹‹አንተም ተው! አንተም ተው!›› ማለት ያለባቸው አካላት እና ዜጎች ጉዳዩን በቸልታ መመልከታቸውና ግድየለሽነታቸው ሊፈጥር የሚችለው አደጋ፣ እንደ ሩዋንዳ ያሉ አገሮች ያለፉበትን የእርስ በርስ እልቂት የልጆች ጫዋታ ሊያስመስል ይችላል፡፡
አገር በፖሊቲካ ብቻ አትመራም፡፡ በሃይማኖት፣ በሞራል እና በዕውቀት ጭምር እንጂ፡፡ ይህን ማኅበረሰባዊ ሓላፊነት የተሸከሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ፖሊቲካውን ወደ ጎን ትተው ስለ አገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመምከር ሊሰበሰቡ ይገባል፤ ከውጥረቱም ኾነ ሊነድ ካለው እሳተ መዓት ለመዳን ሐሳብ ሊያዋጡ፣ ምክር ሊለግሡ በሚገባቸው ሰዓት ላይ ያለን ቢኾንም፤ ዳር ቆመው የመመልከታቸው አመክንዮ ግልጽ አይደለም፡፡
ጉዳዩ የኹሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጉዳይ ቢኾንም፣ ተደማጭ የሚባሉ አካላት አጀንዳ አዘጋጅተው ኅብረተሰቡ ተቀራርቦ ሊነጋገር የሚችልበትን መድረክ ሲያፈላልጉ አይታይም፡፡ ከዚኽ ነፃ እና ገለልተኛ ውይይት የሚፈልቀው ሐሳብ፣ ኹሉንም ወገኖች የሚገሥጽና ተግባራዊ መረጋጋት እንዲመጣ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ የውይይት መድረክ የአገሪቱን ሕዝቦችንም ኾነ የፖሊቲካ ኃይሎች ወደ ብሔራዊ ዕርቅ እና ወደ ብሔራዊ መግባባት ጠረጴዛ ሊያመጣቸው ይችላል፡፡
የሃይማኖት አባቶች ሚና
ባለፉት ኃምሳ ዓመታት፣ በኢትዮጵያ ያሉ የሃይማኖት አባቶች ከፖሊቲካ ሥርዓቱ ተነጥለው ለመቆም ያደረጉት ጥረት አነስተኛ በመኾኑ ሳቢያ፣ የወቅቱ ዓይነት ችግር ሲከሠት ኅብረተሰቡ ከሃይማኖት አባቶች ተስፋ የሚያደርገው የአስታራቂነት ሚና ጠባብ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ እንዲያውም ግልጽ በኾኑ መድረኮች ሳይቀር፣ ሕዝቡ ለሃይማኖት አባቶቹ ያለው ግምት እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ፣ አገራችን የዚኽ ዓይነቱ ችግር ሲገጥማት ዓይኑን ወደ ሌሎች ማማተር ጀምሯል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ሚና ላልቶ መታየቱም፣ ሊሰጣቸው ይገባ የነበረውን የአስታራቂነት ሚና አላሳጣቸውም ማለት አይቻልም፡፡
የሃይማኖት አባቶች ወደ አመራር የሚመጡበት መንገድ ፍጹም መንፈሳዊ ኾን ሲገባው፣ በአንድም ኾነ በሌላ መንገድ የመንግሥታት እጅ መኖሩ ለተቀመጡበት ወንበርና ለተሠየሙበት መንፈሳዊ ሕይወት ታማኝ እንዳይኾኑ ጋሬጣ ኾኖባቸው ቆይቷል፡፡ አገራችን በሕገ መንግሥት ደረጃ፣ መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ መኾናቸውን፣ አንዱ በሌላው ጣልቃ እንደማይገባ በግልጽና በማያሻማ ኹኔታ የተደነገገ ቢኾንም፤ አብያተ ክርስቲያንና አብያተ መስጊዶች፣ የመንግሥት ካድሬዎች መፈንጫ መኾናቸው የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡
በአገራችን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለታየው አለመረጋጋትና ረብሻ፣ የሃይማኖት አባቶች ሊጫወቱ ይገባ የነበረውን ሐቀኛ ሚና ሳይወጡ በመቅረታቸው ሳቢያ ውጥረቱ ከሯል፡፡ በሰባት የእምነት ተቋማት ከአምስት ዓመታት በፊት፣ ‹‹የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ›› የተሰኘ ማኅበር መመሥረቱ ይታወቃል፡፡ በአኹኑ ወቅት የሚመራው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ነው፡፡
‹‹በመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር ዕሴታችንን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ›› በሚል መርሕ በ2003 ዓ.ም. የተመሠረተው ይህ የእምነት ተቋማት ጉባኤ ዋና ዓላማው፣ በእምነቶች መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት እንጂ በትውልዱ መካከል ስለሚነሡ ልዩ ልዩ ቅራኔዎች መፍትሔ ለማበጀት የሚችል አያስመስለውም፡፡ ጉባኤው የተመሠረተው በምእመናን ፍላጎትና ይኹንታ ሳይኾን በመሥራች የእምነት ተቋማቱ ዋና ዋና መሪዎች ፍላጎት መኾኑ ደግሞ፣ ወደ መንበሩ ከመጡበት መንገድ ፍትሐዊነት ጋር የተያያዘ ያደርገዋል፡፡ ችግር ሲደርስ ብቻ ወደ ብዙኃን መገናኛ ብቅ እያሉ መንግሥት ለወሰደው ርምጃ ቡራኬ የመስጠት አካሔድ፣ የጉባኤውንና የተቋማቱን ተኣማኒነትና መንፈሳዊነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ የከተተው ኾኖ ይገኛል፡፡
ባለፈው ዓመት በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልሎች ከአዲስ አበባ የማስተር ፕላን ማስፋፊያ ጋር በተያያዘ ረብሻ በተቀሰቀሰበትና ብዙዎች ሕይወታቸውን ባጡበት ወቅት፣ በየካቲት ወር የተሰበሰበው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው፣ ‹‹ለደረሰው የሰው ሞት አዝነናል›› ከማለት ውጭ፣ ግድያውንና ደም መፋሰሱን ሊያወግዝ አለመቻሉ የተጠበቀ ነገር ኾኗል፡፡
የሃይማኖት አባቶች፣ ኢ-ሰብአዊ እና ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸም፣ ለምን ብለው መጠየቅ ባይችሉ እንኳ፣ ለድርጊቱ ቡራኬ መስጠት በሚመስል አኳኋን መግለጫ ማውጣታቸው፣ በተኣማኒነታቸው ላይ ጥላ አላጠላም ማለት አይቻልም፡፡ ከዚኽ አለፍ ሲልም፣ የሰዎች ሕይወት አላግባብ ሲያልፍ
እንደየእምነታቸው ጸሎት አለማወጃቸው፣ መንፈሳዊ ተልእኳቸውን መዘንጋታቸውን እንደሚያሳይ ነው ብዙዎች የሚምኑት፡፡
የሃይማኖት መሪዎቹ በግለሰቦች የሚጠየቁበት አካሔድ ባይኖርም፣ በሚያምኑበት ፈጣሪ እንደሚጠየቁ መዘንጋታቸውን ማሳያዎች አሉ፡፡ በተለይም በየጊዜው በሚወጧቸው መግለጫዎች፣ የአማናዊ ፍርድና ፍትሕ የፈጣሪ ሥራ መኾኑን በመርሳት ወይም በመካድ፣ ‹‹አጥፊዎች ለፍርድ ይቅረቡልን›› ማለታቸው፣ ሃይማኖታዊ ትእዛዝን እንደ መጣስ ይቆጠርባቸዋል፡፡ አስቀድመው ያጠፉ ወገኖችን ገሥጸው ወደ ቀናውና ትክክለኛው መንገድ ከመመለስ ይልቅ፣ ለበለጠ ችግርና መከራ እንዲዳረጉ መማለድ በአመራር ደረጃ ከተቀመጡ አባቶች የሚጠበቅ ነውን? ፈሪሃ እግዚአብሔር በምእመኑ ላይ እንዲያድር ከመሥራት ይልቅ፣ አምስት ዓመታትን እየጠበቀ የሚመጣውን ምርጫ ለመታዘብ በየምርጫ ጣቢያው መዞራቸው አነጋጋሪ ነው፡፡
የምሁራን ሚና
አገራችን ደክማ ያስተማረቻቸው ምሁራን፣ የዚኽ ዓይነት ችግርና ውጥረት ሲከሠት ዳር ቆመው የመመልከታቸው ልምድ አዲስ አይደለም፡፡ በርግጥ በደርግ መንግሥት ውድቀት ዋዜማ ላይ እየመጣ ከነበረው አስፈሪ የእርስ በርስ እልቂት ለመዳን፣ ‹‹የራሳችንን አስተዋፅኦ ማድረግ አለብን›› ያሉ ምሁራን፣ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ሐሳባቸው፣ በደርግም ይኹን በኢሕአዴግ ዘንድ ተቀባይነት ባያገኝም እኒኽን ምሁራን ታሪክ ያስታውሳቸዋል፡፡
በምሁራኑ የመፍትሔ ሐሳብ የቀረበለት የደርግ መንግሥት፣ በ11ኛው ሰዓት ላይ እንኳ ራሱን ለመመርመር ሳይችል የቀረ ቢኾንም፣ ምሁራኑ በጊዜው የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ሓላፊነት ተወጥተዋል፡፡ አገራዊ ውጥረት በሰፈነበት ጊዜ ኹሉ የምሁራን አስተዋኦ አስፈላጊ መኾኑን ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲኽ ግን ምሁራን ራሳቸውን በልዩ ልዩ ምክንያት እየጀቦኑ፣ ከፖሊቲካም ኾነ ከማኅበራዊ ተሳትፎ መራቃቸው እየታየ ነው፡፡ የውይይትና የንግግር መድረኩን የመክፈት፣ ችግሩን የመተንተንና የመፍትሔ አቅጣጫውን የማመላከት ሞራላዊና ሞያዊ ድርሻ የምሁራን ነው፡፡
ከዚኽ በአንፃሩ አንዳንዶቹ፣ የመንግሥት ካድሬ መኾናቸው አፍ አውጥተው ሲናገሩ፣ ሌሎች ደግሞ ራሳቸውን በጽፈኝነት መድበው ይታያሉ፡፡ ሕዝብ በተለያዩ ግፊቶች ወደ ፍጅት ሲያመራ፣ በጎራ እንዲፈራረጁም ኾነ በዝምታ እንዲሸበቡ የቀሰሙት ዕውቀትና ምሁራዊ ሚናቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ አንዱን ደግፈው ሌላውን ማውገዝ አይኖርባቸውም፡፡ በርግጥ እየተስፋፋ ያለው ሁከት በጊዜ መፍትሔ ካልተበጀለት የሚናገሩ ጥቂት ምሁራን አሉ፤ በድምፃቸው ማነስ፣ የተንሰራፋው ምሁራንን የማግለል ዘመቻ ሰለባ ኾኑ እንጂ፣ በየጊዜው ከሚፈጠሩ ውጥረቶች አንዱ መውጫ መንገድ ከምሁራን ጋር ግልጽ ውይይት ማድረግ ነው፡፡
የብሔራዊ ዕርቅ እና መግባባት አስፈላጊነትና ጥቅም
ብሔራዊ መግባባት እና ዕርቅ፣ እጅግ ተፈላጊ ማኅበራዊ እሴቶች እንደኾኑ ግልጽ ነው፤ ሀገርን ከውድቀት ለማዳን ዓይነተኛ መፍትሔዎች ናቸውና፡፡ ሰላምን ለመመሥረትና ለማጽናት ወሳኙ መሣርያ በግልጽ መነጋገርና መወያየት እንደኾነ በጉዳዩ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ያስገነዝባሉ፡፡ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት፣ ከሌሎች የትግል ስልቶች አግባብነትና አተገባበር ጋር የሚወዳደር አለመኾኑ ቢታወቅም፣ በተለይም ሥልጣን ላይ ያሉ መንግሥታት በቀላሉ እጃቸውን የሚሰጡለት ስልት እንዳልኾነም የጥናቱ ተግዳሮቶች ያሳያሉ፡፡
ብሔራዊ ዕርቅ እና መግባባት፣ ከሌሎች ሰላምን የማስፈኛ መንገዶች ጋር/ለምሳሌ፡- በጦርነት ከማሸነፍ ጋር/ ፈጽሞ የሚወዳደርና የሚነፃፀር አይደለም፡፡ በተለይም አገራችን አኹን ካለችበት ወቅታዊ ኹኔታ አንፃር፣ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት የሚያስፈልገው፣ ኢትዮጵያችን ያለችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ተባብሶ ወደ ከባድ ቀውስ እንዳትገባ ስለሚያደርግ እንደኾነ ግልጽ ሊኾን ይገባል፡፡ ችግሮችን፣ በሕዝባዊ ዓመፅም ኾነ በጦርነት ለመፍታት መሞከሩ የሚያስከትለው ቀውስ፣ በቶሎ ማቆሚያ እንደማይኖረው፣ የበርካታ አገሮችን ተሞክሮ በመጥቀስ የሚያስጠነቅቁ ብዙዎች ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ፣ “Democracy and Its’ Trade-off: Ethiopia’s Path to National Reconciliation” በሚል ርእስ እ.አ.አ በ2014 ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳመለከቱት፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ለውጥ በምርጫ፤ ካልኾነ በጦርነት፤ ካልተቻለ በሕዝባዊ ዐመፅ ማምጣት አደጋ ካለው በብሔራዊ መግባት የትብብር መንግሥት ከመመሥረት ውጭ ሌላ ምንም አማራጭ የለም›› ሲሉ የሰላም ማስፈኛ መንገዶችን ያመላክታሉ፡፡
ብሔራዊ መግባባትን ለማስፈን የየአገሮቹ ነባራዊ ኹኔታም ሊተኮርባቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል ዋናው እንደኾነም ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ፡- ሙሉ በሙሉ ወደ ውድመት እያመሩ ባሉ እንደ እነሶሪያ እና ሊቢያ ዓይነት አገሮች ውስጥ ብሐየራዊ መግባባትን ለመፍጠር ጊዜው ረፍዷል ለማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ግጭቱ ከቃላት አልፎ ወደለየለት ደም መፋሰስና አውዳሚነት ስለገባ ብሔራዊ መግባባትን ለማስፈን ተጨማሪ ጊዜ ይጠይቃል፡፡
ብሔራዊ መግባባት በኹሉም ወገኖች እስከሚታመንበት ጊዜ ድረስ፣ ለማፈንገጥ የሚሞክሩ ወገኖች መኖራቸው ነባራዊ ሐቅ ነው፡፡ ያም ኾኖ ቅራኔና ቁርሾ ባለበት ሀገር መንግሥት ባለጠመንጃ በመኾኑ፣ ብሔራዊ መግባባቱን በተፈለገው ፍነት ለማምጣት ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ይህን በተመለከተ፣ ተክሉ አባተ የተባሉ ጸሐፊ፣ “Reconciliation: the way out” በተሰኘ ጽሑፋቸው፣ ‹‹የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ስለሚፈልጉት፣ ብሔራዊ መግባባትንና ዕርቅን ለመተግበር የማይቻል አይደለም፤›› ሲሉ በሰላም የመኖር ፍላጎት የኹሉም ግለሰቦች ፍላጎት መኾኑን በመጥቀስ ይሞግታሉ፡፡
ብሔራዊ ዕርቅ በሚገባ ከተያዘና ከተጠናቀቀ ዓምባገነኖችን ሳይቀር ነፃ የሚያወጣ ነው፡፡ ኹሉም ተሳታፊ ስለሚኾን ጦርና የጦር ወሬዎች ታሪክ እየኾኑ ይሔዳሉ፤ ይህ መንገድ የሰው ሕይወትም ኾነ ንብረትና ሀብት አያጠፋም፡፡ በመኾኑም፣ ይህ የፖሊቲካ መሥመር ጭስ አልባ ሊባል ይችላል፡፡ በሚያስፈራ ዝምታ ውስጥ ያለውን የሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀልብ ሊስብ ይችላል፡፡ ለመግባባትና ለዕርቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ፣ በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ስላለው፣ አስፈላጊው ድጋፍና ማበረታቻ ለማግኘት አይከብድም፡፡ በመጨረሻም ይህ የትግል ስልት ቀጣይነት ያለው ሰላምና ዕድገት እንዲመጣ ፈር ይቀዳል፡፡/ተክሉ አባተ፤ 2013/2014/
ርግጥ ነው፣ ቀጣይነት ዘላቂ ሰላምና ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር፣ መግባባትና ዕርቅ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ዳዊት ተሾመ፣ “On the question of national reconciliation” በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፣ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት፥ በቋንቋ፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖሊቲካ ምክንያት ጥላቻ ያደረባቸውን አካላት ለማገናኘት እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡
ምን ማድረግ ይቻላል?
ቀዳሚው ነገር፣ የችግሩ አሳሳቢነት ላይ ግልጽ አቋም መያዝ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ በግልጽ መነጋገር የሚችሉ ዜጎች ኹሉ ሐሳባቸው ተደራሽ ሊኾን በሚችልበት መንገድ ሐሳብ ማዋጣት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ፣ በመምህርነት ያሳለፉ፣ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በግልጽ አውጥተው በመናገር የሚታወቁ፤ በማንኛውም የፖሊቲካ ፓርቲ ውስጥ ተሳትፎ ያላደረጉና በድጋፍም ይኹን በተቃውሞ ሐሳብ ሰጪነታቸው የማይታወቁ ግለሰቦች፤ ኹሌም የትውልዱና የአገራችን ትኩሳት የሚያሳስባቸውና ባገኙት አጋጣሚ ኹሉ ተቆርቋሪነታቸውን የሚያሳዩ የብዙኃን መገናኛና የኪነ ጥበብ ሰዎች እንዲኹም ሀገር ወዳድ ዜጎች ኹሉ ሊሳተፉበት ይችላሉ፡፡
በሀገራችን የተፈጠረውንና እያቆጠቆጠ የመጣውን ጎሳ ተኮር መጤ ጠልነት፣ ከሥር መሠረቱ ችግሩን አጥንቶ ለመንቀል፣ የጠፉት የሀገር ሽማግሌዎች ከያሉበት ብቅ ብለው ትውልዱን ሊታደጉት ይገባል፡፡ ሽማግሌነት በዕድሜ ብቻ የሚመጣ የሓላፊነት መንበር ሳይኾን፣ በዕውቀትና በአስተሳሰብ መረጋጋት ጭምር ነውና፣ ኹሉ የሚሳተፍበት መድረክ መኾን ይገባዋል፡፡ ለዚኽም፣ ኹሉም ዜጎች ወደ ሰላሙ ሜዳ በመግባት የበኩላቸውን አስተዋኦ ሊያበረክቱ ይገባል፡፡
አገሬው የሚያከብራቸውና የሚከተላቸው ‹‹ሽማግሌ›› ዜጎች፣ በአንድ ዓላማ ሥር ተሰባስበው ሕዝብን፣ መንግሥትንና የተለያዩ ኃይሎችን ለማግባባት በሚያደርጉት ጥረት፣ ሕዝብም እንደ ሕዝብ፣ ሀገርም እንደ ሀገር ከጥፋት የሚድኑ ይኾናል፡፡
የማጠቃለያ ሐሳቦች
ለሀገር የጸና ሰላምና ጤናማ ዕድገት ወሳኝ የኾነው ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት እንዲመጣ፣ በዋናነት ግንባር ቀደም ሚና ሊጫዎት የሚገባው፣ መንግሥት ስለመኾኑ አያከራክርም፡፡ ኾኖም ይህንኑ የመግባባት አስፈላጊነት ተንትነው ሊያቀርቡ የሚገባቸው፣ በገለልተኝነት የተደራጁ የሀገር ሽማግሌዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት ተቋማት ይኹን ከምሁራን ሊውጣጡ ይችላሉ፡፡ ከኹሉም የኅብረተሰብ ክፍል መውጣጣታቸውና መደራጀታቸው እንደተጠበቀ ኾኖ፣ ከዚኽ በፊት በታየ ፖሊቲካዊ ሒደት ተሳትፈው በኅብረተሰቡ ጥቁር ነጥብ ያልተሰጣቸው መኾን ይገባቸዋል፡፡
በመኾኑም ገለልተኛና አንፃራዊ በኾነ የዘረኝነትና የጎሰኝነት በሽታ ያልተያዙ ወይም የአንደኛውን ወገን የመደገፍም ኾነ የመቃወም ዝንባሌ ያላሳዩ፣ ንጹሕ ኢትዮጵያውያን የተሰባሰቡበት ብሔራዊ ሸምጋይ አካል መመሥረት ተገቢ ነው፡፡ ይህን አካል የሚያቋቁመው ስብስብ፣ የሚቋቋምበት መስፈርት፤ የሚኖረው ዝርዝር የሥራ ድርሻ፣ የሚጠቀማቸው ዘዴዎች… ወዘተ ጥርት አድርገው በማዘጋጀት ለውይይት ቢያቀርቡ መልካም ይኾናል፡፡ ይህ ቀላል ሥራ ስላልኾነ፣ የስብስቡ አባላት ስሜታቸውን የሚቆጣጠሩና ሞራላዊ ብስለት ያላቸው፤ ዐዋቂዎችና አስተዋዮች እንዲኹም የመግባባትና ጫናን የመቋቋም አቅም ያላቸው ሊኾኑ ይገባል፡፡
ከዚኽ አንፃር የሚከተሉት ኢትዮጵያውያን፣ ብሔራዊ የመግባባት ሥራውን ለመጀመር ይችላሉ ብዬ አምናለኹ፡፡ ምናልባት ፖሊቲካዊ ፍላጎት ወይም አንዳች የፖሊቲካ ፍላጎት ያላቸው ከኾኑ በቅንነት ራሳቸውን ከስብስቡ ሊያገሉ እንደሚችሉ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል እላለኹ፡፡ በጥቆማው የቀሩ ወይም መካተት ያለባቸው ካሉ አንባብያን ሐሳብ ሊሰጡበት ይችላሉ፡፡
- አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ
- አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ
- ወ/ሮ አበበች ጎበና
- አቶ ይመስገን ሞላ
- አቶ ብንያም በለጠ(መቄዶንያ)
- ፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታ
- ተ/ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው
- ዶ/ር ምሕረት ደበበ
- ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኤ
- ደራሲና ሠዓሊ አሰፋ ጉያ
- ማኅደር ገብረ መድኅን
- ወ/ሮ ቤተ ልሔም ጥላሁን
- ኢ/ር ሰውነት ቢሻው
- አትሌት ቀነኒሳ በቀለ
- ገነነ መኩሪያ
- መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ
- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
- ዑስታዝ ሐሰን ታጁ
- ዶ/ር ወዳጄነህ መሐሪ
- አዜብ ወርቁ
- አርቲስት ፈቃዱ ተክለ ማርያም
- አርቲስት ሰሎሞን ቦጋለ
- ጋሽ አበራ ሞላ
- አርቲስት ፀሐዬ ዮሐንስ
- አርቲስት ቻቺ ታደሰ
- አርቲስት ሚካኤል በላይነህ
- ሠርጸ ፍሬ ስብሐት