ሙሉጌታ ሉሌ ሲሞትልዎ በሐሰን ዑመር አብደላ ላይ መዝመትዎን ቀጠሉ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ሆህተብርሃን ጌጡ | ጀርመን

ይድረስ ለዕዝራ ደመላሽ (አበራ ለማ) “የምግታር ለትርቡሌዉ ልጅ” ፅሁፍ አቅራቢ (ኖርዌይ) ካሉበት

ምግታር ለትርምቡሌዉ ልጅ… ቃሉ ምግታር የሚለዉ ከሟቹ ከኀይሉ ገሞራዉ የተሰረቀም ቢሆን በዚህ ርዕስ በዕዝራ ደመላሽ ሥም ከፍራንከፈርት ብለዉ ሰሞኑን ለድረ ገፆች ለንባብ ያበቁትን አርቲክል ተመለከትኩት። አነሳስዎ ከእርስዎ ፅሁፍ ከጥቂት ቀናት በፊት በተለያዩ ድረ ገፆች ለንባብ ለበቃዉ… በመዘዘኛዋ ኤርትራ ጦስ-ዛሬም ስንተራመስ…,, የሚለዉ ፅሁፍ በይሄይስ ተዓምኖ ሳይሆን በእኔ ይሄይስ ተአምኖ በተሰኘ ብዕር ሥም ፍራንክፈርት አብሬዎ በምኖረዉ (ነጭ ዉሸት አይዋሹ፣ አርስዎ ኖርዌይ ነዉ የሚኖሩት) እንደተዘጋጀ በመገመት፣ በእኔ ሥም ግን እንዳልወጣ አድርገዉ በማመን ፀሐፊዉን ወይንም እኔን ለመሄስ የተነሱ ይመስላል። የትችትዎ ምክንያትም ደግሞ እኔ ወይም ጸሓፊዉ ከጠቀሰዉ ሰዉ ጋር ያለዎት አለመግባባት (ጠብ) እንጂ የመጣጥፉ ይዘት እንዳልሆነ፣ ገና ከጅምሩ ያስታዉቃል። ያን ሁሉ ጎዳና ያስኬደዎና ያንድን ክፍለ ሀገር ሕዝብም በጅምላ ለመሳደብ ያነሳሳዎ ምክንያቱ ይኸው ነዉ። ዉስጣዊ ዓላማዎ ደግሞ በዚያ ፅሁፍ በበጎም ሆነ በክፉ ሥማቸዉ የተጠቀሱ ግለሰቦች ካሉ ዕገሌ ነዉ የሚል ጥቆማ ለማካሄድ ወይም የማሳበቅ ሥራ ለመሥራት የተዘጋጁ እንደሆነ ያስታዉቅበዎታል። ባጭሩ የፅሁፍዎ ጭብጥ የሚያጠነጥነዉ ይህን ፅሁፍ ሊጽፍ ይችላል ብለዉ ግምት የሰጡት ሰዉ፤ እርስዎ ከሚጠሉት ዩሱፍ ያሲን ጋር የእርስዎን አባባል ልዋስና የሆድ ወዳጅ ስለሆነ እሱንም፣ የተወለደበትንም ክፍለሃገር ሳይቀር ሥማቸዉን ላጥፋ ነዉ መልዕክቱ። ሌላ ምክንያት ባፈላልግ የተወለድኩበትን ክፍለሃገር ሕዝብ ጭምር የሚያሰድብ ድርጊት ባወጣ ባወርደዉ ላገኝ አልቻልኩም፤ ምናልባት ጎንደር የአማርኛ አስተማሪ ሆነዉ በሰሩበት ወቅት በግል ያስቀየመዎት ተማሪ ከሌለ በቀር? እኔን በሚመለክት ወደፊት የሚያካሂዱት ሪሰርች ካለ የፕሮጄክትዎ ጥናት የተሳካ እንዲሆን መጀመሪያ ሥሜን ላስተካክልዎ። እርስዎ አበራ ለማ ገደፋ ገዳ በመባል እንደሚታወቁት ሁሉ እኔንም ሲገልጹኝ ሆህተጥበብ እንዳሉት ሳይሆን፣ ሙሉ ሥም ከነአያት ሆህተብርሃን ጌጡ ተሰማ ነዉ። በብርሃንና በጥበብ መካከል ያለዉን ልዩነት መቼም ሳይረዱት አይቀሩም። በሰዋስዎ ቀመር ሕግ በዘርፍ ተናባቢዎች መካከል ባሉ የቃላት መለያየት ከፍተኛ የትርጉም ልዩነትም አለ።።እርስዎ ለመግለፅ እንደሞከሩት በካድሬነትም ባይሆን ለተወስኑ ዓመታት በደርግ ሥርዓት በጋዜጠኝነት ተግባር ተሰማርቼ ለሀገሬ ሠርቻለሁ። ይህንንም በሆነ አጋጣሚ ራይን-ማይን የኢትዮጵያዉን ኮምዩኒቲ በአንድ ወቅት ፍርንክፈርት ከተማ በተደረገ ስብስባ፣ በሆነ ምክንያት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዉ ስለነበር፣ ስለእኔ ማንነት ገልጫለሁ። እርስዎ የፍራንክፈርት ኗሪ ቢሆኑ ኑሮና የኮሚኒቴያችንም አባል ቢሆኑ ኖሮ፣ ሆህተ እንደዚህ ነዉ የሚል ያረጀ ኢንፎርሜሽን/መረጃ እንደ አዲስ አያቀርቡም ነበር። ለብዙ ጊዜያትም በዚሁ ኮሚኒቲ በምክትል ሊቀ መንበርነትና በፀሐፊነት አገልግያለሁ። በየደረስኩበት ባላቅራራም ኢትዮጵያዊ ጎንደሬነቴንም ደብቄ አላዉቅም። አስጎንብሶ የሚያስኬድ ተግባር በሕይወቴ ፈፅሜ ስለማላዉቅ ባለፈ ሥራዬ ባልኩራራም አፍሬበት ግን አላዉቅም። ደግሞስ ለአንድ ሰዉ ፅሁፍ መልስ ለመስጠት ወደዚያ ሰዉ ክፍለ ሀገር ትዉልድ መሄድስ ምን አስፈለገ? ኢትዮጵዊነታችን አልበቃ አለ? የፅሁፍዎ ይዘት ግን የሚያስተላልፈዉ መልዕክት ከዚያ የተለዬ ነዉ። እኔ በዕዉነት አንባቢ እንዲረዳልኝ የምፈልገዉና ይቅርታም የምጠይቀዉ ሳልወድ በግድ ወደዚህ አተካራ ተራ ነገር ውስጥ እንድገባ በመገደዴ እንጂ የመወራረፍና የመጠላለፍ ሱስ ኑሮብኝ እንዳልሆነ፣ነዉ። ይኸዉም እኔን እንደግለሰብ በመሰላቸዉ መንገድ መሳደብ ሲችሉ፣ ተውልጄ ያደኩበትን ክፍለ ሃገር ሥም በማንሳት የጎንደርን ሕዝብ ባጠቃላይ ,,የጎንደሮቹ ትርምቡሌ ልጅ,, ስለትርምቡሌዎች ጋባዥነትና አልባሽነት ታሪክ ሊተርቱ ሞክረዋል። በዕዉነት የጎንደር ክፍለ ሀገር ሕዝብስ እርስዎ እንዳቀረቡት፣ እንዲያ ዓይነት ታሪክ ነዉ ያለዉ? ባለፈ ታሪኩም የሚያኮራ ጀብዱ የፈጸሙ ጀግኖችን ያፈራ፣ በአሁኑም ፀረ ወያኔ እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥም ሆነ፣ በዉጭ አገር በገንዘባቸዉ፣ በጊዜያቸዉ ሁለ አቀፍ የሆነ መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚገኙ ልጆችን ያፈራ ክፍለ ሀገር ነዉ። ሌላዉ ሁሉ ቢቀር እነታማኝ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ሊረሱት አይገባም ነበር? ብዙዎችም ይታዘቡዎታል!

አንድ ሥሙን የማላስታዉሰዉ ገጣሚ፤

በራስ ጎጆ ጣሪያ ሥር፣
ተደብቆ በምሥጢር፤
ከበድን ኮምፒዩተር ጋር ይዞ ንግግር፤
በኤሌክትሮኒክ ዓለም ከልካይ በሌለበት፤
የስድብ ዉርጅብኝ የምታወርድ መዓት፤
ያልተገራ አንደበት ምላስ ባለሐብቶች፤
የነገር፣ የተንኮል፣ የሸር ቱጃሮች፤
ወደ ጠላት ሳይሆን ወደ ወገን ግንባር አነጣጣሪዎች፤
እንዴት ከረማችሁ እናንት ዋልጌዎች

እንዳለዉ መሬት ላይ ካለዉ ዕዉነት ርቀን፣ የምንወደዉን አለአግባብ ለማወደስና የምንጠላዉን ለማዉገዝ ስንል አንዳንዶቻችን የዘመኑን ቴክኖሎጂ እየተጠቀምንበት እንገኛለን። ባጭሩ ዕሁፍዎ እንደገባኝ ከሆነ የእኔ ወንጀል ሆኖ የተገኘዉ፣ እርስዎ ከሚጠሉት ሰዉ (ዩሱፍ ያሲን) ጋር ለምን የልብ ወዳጅ ሆንክ የሚል ነዉ። ያም በመሆኑ ሌላዉ ሁሉ አንባቢ በወቅቱም ሆነ ዛሬ እጅግ የወደደዉን እርስዎ ግን የተጸየፉትን (,,…ኢትዮጵያና ኤርትራ-ያልተጠናቀቀ ፍቺ፣ ያልተሳካ ጉርብትና…,,) ከሚለዉ አርቲክል የእርሱን ፅሁፍ ያን በእኔ ሥም የጻፈ ሰዉ ለምን ጠቀሰ ነዉ፣ ያንጨረጨረዎት። ጸሃፊዉ ራዕይ መጽሄትን ምንጭ አድርጎ መጥቀሱ ከሆነ ወደ ጥርጣሬ ዓለም ያስገባዎ፣ በወቅቱ የራዕይ ደንበኞች የነበሩ አንባብያን መፅሄቱ በየቤታቸዉ እንደሚኖር እርግጠኛ ነኝ። ደግሞስ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ግንኙነት አስመልክቶ በተፈጠረ ችግር የሐሰን ዑመር አብደላ (የዩሱፍ ያሲን) ፅሁፍ ያልተጠቀሰ የማንስ ይጠቀሳል? መሬት ይቅለለዉና አቶ ሙሉጌታ ሉሌ በአንድ ወቅት እሱን፣ ሟቹን ተፈራ አሥማረን፣ ገሞራዉ ካሳን፣ (ዳዊ ኢብራሂም በወቅቱ ተጋብዞ ኬንያ ስለነበር በቪዛ ምክንያት ሳይሳካ አልተገኘም) በኮሚኒቲዉ መድረክነት ፍራንክፈርት ጋብዘን በነበረበት ወቅት በዚያ አጋጣሚ ያጫወተኝን ሳልጠቅስ ማለፍ ይከብደኛል። ጋሽ ሙሉጌታ፡ ተፈራ አስማረ እኔ ሆነን፣ እኔ ቤት እስከ ሌሊቱ አሥር ሰዓት ሳንተኛ ያልተነሳ ነጥብ አልነበረም። ያችን ሌሊት ሁልጊዜ አስታዉሳታለሁ። ከእነኝህም አንደኛዉ በወቅቱ ለድምፅ አልባዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ድምፅ ሆና ታገለግል ስለነበረችው የጦቢያ ዓምደኛ ፀሃፊዎች ነበር። ሳልጨምር ሳልቀንስ ሙሉጌታ በወቅቱ ያጫወተን፣ ,,..ጦቢያ መፅሄትን ደረጃዋን ጠብቃ እንድትቀጥል ያስቻላት ,,… ጸጋዬ ገብረ መድኅን አርያ ወይንም ስንሻው ተገኘም አይደለም፣ ሐሰን ዑመር አብደላ እንጅ ነዉ ያለን። እንዲያዉም መጽሄቱ ታትሞ ሲወጣ አንዳንዶች በቅድሚያ ማውጫዉን ዓይተዉ የእሱ ፅሁፍ ካለበት (በተለይም በምሁሩ አካባቢ) ነዉ የሚገዙት፣ለሚያደርገዉም ያልተቆጠበ አስተዋጽኦ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለዘመድ ዉክልና ስጥና መጠነኛ ክፍያ እናድርግልህ ብለን ብንጠይቀዉ፣ እናንተ በርትታችሁ ቀጥሉ እንጅ ከእናንተ ምንም ሳንቲም አልፈልግም …,, የሚል መልስ ነዉ የሰጠን ብሎ ያጫወተንን እስካሁን አልረሳዉም። እታዲያ ስለ ዩሱፍ ያሲን ምንንነት ምስክርነት ሙሉጌታ ሉሌን እንመን ወይንስ አበራ ለማን? ሰዉ ዕምነት እንዲጥልብዎ ከፈለጉ፣ ከአሉባልታ ይራቁና አመኔታ አንዲጣልብዎ የሚያስችል ተግባር ይፈጽሙና እንይዎ! አሁን ባሉበት ሁኔታ ግን ያን! ሎጋ ቁመትዎን የአስተሳሰብ ድንክነትዎ ተክቶት ተቸግረዉ ይታዩኛል።

ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስና በመሠረቱ እኔ፣ የዚያ ፅሁፍ አቅራቢ ባለመሆኔ ያን ፅሁፍ በተመለክተ እንደዚያ ሰዉ ሆኜ ልሞግትዎ አልሻም። ለነገሩ እኮ እርስዎ ያንን ፅሁፍ መነሻ አደረጉ እንጂ፣ ፅሁፍዎ የሚያስተላልፈዉ መልዕክት ሊሂሱት ከሞከሩት ፅሁፍ ጋር በይዘቱ በጣም የተለያየ ነዉ። ግን አንድ ሰዉ አንድ ፅሁፍ ሲያዘጋጅ፣ ከዝግጅቱ ጋር የሚጎዳኝ ሆኖ ካገኘዉ፣ የማንኛዉንም ጸሃፊ ሰዉ በዋቢነት መጥቀስ የማንኛዉም ሰዉ መብትም ነዉ። እኔ የምጠላው ሰዉ ስለሆነ ሥሙ አይነሳ ከሆነ ችግርዎ፣ ጠቡ ከራስዎ ጋር ነዉና ሳይመሽና ይችን የኮንትራት ዓለም ሳንሰናበታት ከራስዎ ጋር ይታረቁ። መፍትሄዉ እሱ ብቻ ነዉ። በመጀመሪያ ደረጃ እኔ የማን የልብ ወዳጅ ልሁን የማን ጠላት እርስዎ ሊወስኑልኝ አይገባም፣ አይችሉምም። የትኛዉን ሰዉ ለመቅረብም ሆነ፣ ለመራቅ የሚያስችል መጠነኛ አዕምሮ ያለኝ ይመስለኛል። እንዲያዉም እርስዎ በጽሁፍዎ የሆድ /የልብ ወዳጅ ያሉት ዓይነት አባባል የእኛን ግንኙነት በትክክል አይገልጸዉም። ሁለት የእናት ልጅ ወንድሞች አሉኝ። ሦስተኛዉ ወንድሜ ደግሞ ዩሱፍ ነዉ። እርሱ ደግሞ እኔን ከሰዉ ጋር ሲያስተዋዉቀኝ ,,ልጄ,, ነዉ በማለት ነዉ። በእርግጥ እሱ ማቅረቡን ለመግለፅ ቢጠቀምበትም ከዚህ አባባሉ ጋር ባለቤቱ አትስማም። ምሥጢሩ ሌላ ሳይሆን የሆህተ አባት መሆን ከቻለ ያረጅብኛል ነዉ ፍራቻዋ። መቼም ይችን እርጅና ሁሉም ዓይንሽ ላፈር ነዉ የሚላት። አይደል? ግን አትቀር! ይህን ዓይነቱን ግንኙነታችንንም የሚያቑርጠዉ ወሪደ-መቃብር ብቻ ነዉ። አራት ነጥብ። እኔ ከሠላሳ ዓመት በላይ ሳዉቀዉ በኢትዮጵያዊነቱ እንጂ ኤርትራዊ ነዉ የሚለዉን አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ ገና ከእርስዎ መስማቴ ነዉ። እርስዎ ብዙ ስለቀባጠሩባቸዉ አባቱ ስለማላዉቃቸዉ እምብዛም የምለዉ የለኝም። በመጽሃፉ የምረቃ ዕለት ስለሳቸዉ በፎቶና በተለያዩ መረጃዎች በእርስዎ አገቡኞች በሆኑ የኮሚቴዉ አባላት የተነገረን ታሪክ ግን እርስዎ ከሚተርቱልን የባንዳነት ተረት በእጅጉ የተራራቀ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይህ ብቻም አይደለም። አንዳንድ የሀገር ዉስጥና የዉጭ ጸሃፊዎች ስለእሱ አባትና (ፊታዉራሪ ያሲን ሙሃመዳ) ቤተሰብ ከጻፏቸዉም፣ የእርስዎ አቀራረብ በእጅጉ ስለተራራቀብኝ፣ እነዚያን መጻሕፍት በዋቢነት ቢመለከቷቸዉ ኖሮ አቀራረብዎ ሚዛን የደፋ ሊሆን ይችል ነበር ብዬ እገምታለሁ። አሁንም ስለማይመሽ (Dr. Abdalla Adu ,,..Afar… a nation of trial 1988) swedeen, Dr. Jamal Abdulkadir Redoo (Macamooda yassini 2015, Samara and Encycolopedia Athiopiaca (Volume 5 page) Jhon Markarkis የተሰኙትን መጻሕፍት ከቻሉ ይመልከቷቸዉ። የኦስሎ ኗሪ ኢትዮጵያዊ ይጠየቅ? የእርስዎ ዘመዶች ይጠየቁ? ዩሱፍ ጢዮ እሚባል ቦታ መወለዱንም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በኦስሎ የመጽሃፍ ምረቃ ወቅት ላይ ነበር። ይህ ሁሉ ብዙ የሚነገርለት መዘዝ በቀይ ባሕር ባለቤትነት ምክንያት መሰለኝ። በቅርቡም ከአቶ ያሬድ ጥበቡ ጋር ያደረገዉን ቃለ ምልልስም አዳመጥኩት። የትዉልድ መንደሩንም ,,ጢዮን,, ሦስተኛ ወደብ ናት ሲል ይገልጻታል እንጂ የሚያፍርባት አይመስለኝም። እኛ ከተዋወቅንበት ከዛሬ ሠላሳ ዓመት በፊት ጀምሮ እስካሁን፣ የእኛ የጋራ ,,ፓስ-ወርድ,, ኢትዮጵያዊነት እንጂ ዘርና አካባቢ አይደለም። ደርግ ደግሞ የወደቀ ግንድ ምሳር ካልበዛበት በስተቀር በዘር የሚታማ መንግሥትም አልነበረም። እስካሁንም ድረስ ከኢትዮጵያዊነት ዉጭ ዘሩ አይታወቅም። ደግሞስ ለእርስዎ አንዱን ኤርትራዊ ሌላዉን ኢትዮጵያዊ የሚል ዜግነት ለመስጠትና ለመንሳት ማነዉ ሥልጣኑን የሰጠዎ! ላንድ ምስኪን ስደተኛ እንዲህ ዓይነት ሥልጣን የሚሰጥ ሀገር ከሆነማ ሁላችንም ጉዟችንን ወደ ኖርዌይ እናድርጋ? ደግሞስ እርስዎ በፅሁፍዎ እንደጠቀሱት በኤርትራ መገንጠል ፈፅመዉ የማይስማሙ ከሆነ፣ ለምንድነዉ እታዲያ ዩሱፍን ወደ ኤርትራ ለመሸኘት የተቻኮሉት? ለክፉም ለደጉም መጀመሪያ የነበረከት ስምኦን መመለስ ይጠናቀቅና የዩስፍን ጉዳይ ደግሞ ለወደፊቱ እናስብበታለን። ለሀገር የሚያስብ የእርስዎ ዓይነቱ ሰዉ ጥቆማ እንዲህ በቀላሉ መታለፍ የለበትም።

ወንድማችን ሙሉጌታ ሉሌ መሬት ይቅለለዉና ወደማይቀረዉ ዓለም ሂዷል። ቀደም ብለዉም እርስዎ በዚህ ታዋቂ ብዕረኛ ሰዉ ላይ ጥላሸት ለመቀባት ሲሉ የበዓሉ ግርማ አስገዳይና ገዳይ እንደሆነ አድርገዉ፣ በዓሉ ግርማን የበሉ ጅቦች ብለዉ በአቶ ሙሉጌታ ብቻ ሳይወሰኑ ጎጃሜዎችን በሙሉ ተሳደቡ። ጋሽ ሙሉጌታ ተራ ሰዉ ስላልነበር፣ መልስ ሳይሰጥዎ ወደ ማይቀረዉ ዓለም ተሰናበተ። ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ እግዜር ይስጣቸዉና በቅርቡ ባሳተሙት ,,አብዮቱና ትዝታዬ,, በተሰኘዉ መፅሐፍ ምክንያትነት ስለበዓሉ ግርማ አሟሟት ተጠይቀዉ፣ በዓሉን የገደለዉ የደሕንነት መሥሪያ ቤቱ እንደሆነ፣ ከራሱ ከወቅቱ የደሕንነት ኀላፊ ባለሥልጣን ከነበሩት ከኮሌኔል ተስፋዬ ወልዴሥላሴ አንደበት መስማታቸዉን አረጋገጡልን። በዚህም የአርስዎ ዋሾነት ይፋ ሆነ። እንግዲህ ከምድር ተነስተዉ አፋሮችን፣ ጎጃሞችን፣ ጎንደሮችን ተራ በተራ እየተሳደቡ ነዉ።ምን ቀረዎ? መቼም ጎንደር ከደረሱ ተከዜን መሻገርዎ የማይቀር ነዉ። ክልል አንድ ይድረሱና ሱሪ መታጠቅዎን ያስመስክሩ። ሥም ከሚያጠፉበት ከኢንተርኔትና ከፌስቡክ የጀግንነት ሜዳ ወጣ ይበሉና እስኪ በራስዎ ሥም ለሃያ አምስት ዓመትያህል በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ስላለዉ ግፍ ይተነፍሱ። ወንድ ይውጣዎ! መጨፈር የሚችሉት ያዉ ጊዜ ባጋደለበት አካባቢ እንጂ ወደዚያ ተሻግረዉ ቃል አይተነፍሱም። እንደዚያ ቢያደርጉ ደግሞ አዲስ አበባ በወያኔ የቀበሌ አዳራሽ እየተያዘልዎ መፅሃፍዎን ማስመረቅና መቸብቸብ ሊያቆሙ ነዉ። የነ ጋሼ ዩሱፍ መጽሃፍ አዲስ አበባ ለመመረቅ ዕድል የለዉም። እርስዎ እንደሚሉት ኤርትራዊ ስለሆነ አይደለም ግን ምክንያቱ። በማይንበረከክ ፀረ ወያኔ አቑሙ እንጂ።

እያስረዘምኩ አንባቢን እንዳላሰለች እንጅ፣ ስለ ዩሱፍ መጽሃፍም በጽሁፍዎ ለማዉሳት ሞክረዋል። እንዲህም ይነበባል፤ ,,… ዩሱፍ ያሲን ኢትዮጵያዉያንን በዘርና በጎሳ ለመበታተን አዉጥቶና አዉርዶ የጻፈዉን ርካሽ መጽሃፍ የተንኮል ጭብጥ ተረድቶ,,…የኢሳቱ ሲሳይ አጌና ቃለ መጠይቅ አድርጎለት ባያጋልጠዉ ኖሮ፣ ስንቱ የዋህ ኢትዮጵያዊ በራሱ ገንዘብ እራሱ የተሰደበበትን ርካሽ ዝባዝንኬ ሸምቶ ያንጀት በሽተኛ በሆነ ነበር…,, ይላል። ባጭሩ የመልዕከቱ ጭብጥ የዩስፍን መጽሃፍ አትግዙ ለማለት ነዉ እንጅ፣ የኢሳትን ቃለ መጠይቅ ለተከታተለ ሰዉ እንዲህ ዓይነት መልዕክት ሲተላለፍ አልተደመጠም። ወይንስ አርስዎ የሚያዳምጡት የኢሳት ጣቢያ ለዬት ይላል? (በነገራችን ላይ በአካባቢዬ መጽሃፉን ለሚፈልጉ ሰዎች ያከፋፈልኩት ከለንደን የኢሳት ቡክ ስቶር) ተልኮልኝ ነዉ። ወንድሜ ዩሱፍ ያሲን ለማቴሪያል የሚጨነቅና የሚጠበበብ ሰዉ፣ ለንግድ ብሎ ያዘጋጀዉማ ቢሆን ኖሮ፣ ኪሣራ በኪሣራ አድርገዉት ነበር። ግን ብዙዎቻችን በቅርብ የምናዉቀዉ ዩሱፍ ስለ ዕለት ምግቡና ስለሚለብሰዉም ልብስ አስቦ የሚያዉቅ ሰዉ አይደለም። ግን በእግዜኣብሔር ዕዉነት ,,…አሰባሳቢ ማንነት ባንድ ሀገር ልጅነት-የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ…,, የተሰኘዉ መፅሃፍ እኛን በዘርና በጎሳ ለመከፋፈል የተፃፈ ዝባዝንኬ ነዉ? ደግሞስ ለኢትዮጵያ አለመበታተን አሳቢ ነኝ ካሉና ይህም ካንጀት ከሆነ፣ በጎሳና በዘር እየከፋፈሉን ያሉትን ባለጊዜዎች ለምን ፈሯቸዉ? በወግ ተረታችን ,,አህያዉን ፈርቶ ዳዉላዉን,, የሚለዉ አባባል እዚህ ላይ በትክክል የሚገልጽዎት ይመስለኛል። መጽሃፉን ያነበቡ ሰዎችም ,,…ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት…,, የተሰኘዉን መጽሃፍ ዝባዝንኬ ነዉ ሲሉ፣ በጣም ይታዘቡዎታል። ከልባቸዉም ያዝኑበዎታል። አንድን ሰዉ ስንጠላ በጎ ተግባራቱን ሁሉ አፈርድሜ ለማስጋጥ መሞከርና ብርሃኑን ጨለማ፣ ጨለማዉን ብርሃን ነዉ ብሎ አጣሞ ማቅረብ በስድስተኛ ሕዋስ ከማሰብ በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል ትላላችሁ? ,,..ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት…,, የተሰኘዉ መጽሃፍ ተራ የተረት ተረት ልብ ወለድ ሳይሆን፣ በቂ ጥናቶች ተደርገዉበት የቀረበ፣ የማኅበራዊ ሳይንስ ግኝትና ወደፊትም በከፍተኛ የትምህርት ተቑማት ለማስተማሪያነት እንደሚገለግል ሆኖ፣ በመረጃዎችና በጥልቅ ትንተናዎች ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀ ሰነድ ነዉ። በመጽሃፉ ምረቃ ዕለትም ከታዳሚዎችና ከመጽሃፉ ገምጋሚዎች የተንጸባረቀዉ የፅንሰ ሀሳብ መልዕክት ይኸዉ ነበር። አለመታደል ሆኖ ነዉ እንጅ፣ ኖርዌይ መፅሃፍ ሲመረቅማ መገምገም የነበረበት ደራሲ አበራ ለማ ነበር። እኔ ለእርስዎ ያለኝ አመለካከት እንዲዚያ ነዉ። ግን ምን ያደርጋል? የመለያየትና የመከፋፈል ዛር በሁላችን ላይ ሰፍሮብን በየቦታዉ ያስጎራናል አልፈርድበዎትም። የስደት ኑሮ ከሌላዉ ሰዉ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራስ ጥላም፣ ከቤተስብም ጋር ያጋጫል።
በቅርቡ እርስዎ የጻፉትንና ለንባብ ያበቁትንም ,,…ጥሎ ማለፍ…,, ታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሃፍዎን አንብቤ ወድጄለዎታለሁ። የሥነጽሁፍ ችሎታዎንም አደንቃለሁ። ሳነበዉም በጣም እየጣመኝ ነዉ የጨረስኩት። ግን እንዲያም ሆኖ ከጋሼ ዩሱፍ መፅሃፍ ጋር በይዘት ደረጃ ሲመዘኑ ክብደታቸዉ አይመጣጠንም። ልዩነታቸዉም የት እየለሌ ነዉ። እንዲያም ስልዎ እርስዎ እንዳሉት የሆድ ወዳጄ ስለሆነም አድልዎ በማድረግ አይደለም። እንደዚያ ዓይነት አስተሳሰብ ያለኝ ሰዉ ብሆንማ ኖሮ ገና ከመጀመሪያዉኑ መጽሃፍዎንም አልገዛዉ ነበር። ,,…ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት…,, የሚለዉን ርዕስ ይዞ የወጣዉ የጋሼ ዩሱፍ መጽሃፍ ግን ገና የዉጭ ሽፋኑን ሲመለከቱት መላ ኢትዮጵያ ከነሁለመናዋ ትታያለች። የእርስዎ ደግሞ የቃላት ዉበቱና አቀራረቡ ቢማርክም፣ በይዘቱ በሞቱ እሬሳዎች ላይ የሚፎክር ስለሆነ፣ ሕይወት አልዘራበትም። በሞተ ሬሳ ላይ የሚፎክሩትና አልቃሹን ደረት እያስመቱ ሚሾ እንዲያስወርዱ የተቀጠሩ፣ ከሟቹ ጋር ምንም ዓይነት የሥጋ ዝምድና የሌላቸዉና ሆድ ያልባሳቸዉ አስለቃሾች ብቻ ናቸዉ። የታሪካዊ ልቦለዱ ባለታሪክ ሆኖ በገፀ ባሕርይነት የቀረበዉ ግለሰብ ዳኛቸዉ ወረደ (ፒቲ ኦፎሰር ታምራት ፈረደ) በዕውኑ ሳይሞት በቁም ከሞተ የቆየ ግለሰብ ነዉ። ገና ያንጊዜ የኢኮኖሚ ዘመቻ መምሪያ ስብሰባ ላይ ከሻለቃ እንዳለ ተሰማ ጋር ለመቧከስ ቃጥቷቸዉ ,,ይቺን የሂስ ክኒን ዋጡ…,, ተብለዉ በተግሳጽ በትምህርት ሥም እንዲታረሙ ተብሎ ወደ ቼኮዝሎቫኪያና ቡልጋሪያ ሲላኩ ከሥልጣን ዓለም ተሰናብተዉ ያን ጊዜ ነዉ ሁለቱም በቁም የሞቱትና ከሥልጣንም እየተገለሉ የሄዱት። ያውም እነሱ ዕድለኛ ሆነዉ፣ ጊዜዉ ተቀይሮ ነዉ እንጅ፣ ድሮ የነበረዉ እርምጃማ ለትምህርት ወደ ዉጭ ሳይሆን ,,አመሉ ከከፋ ላከዉ ጋሞጎፋ,, ነበር አሉ የሚባለዉ። የፅሁፍዎ ፈርጠ-ተምሳሌት ሆኖ የቀረበዉ ፒ.ቲ. ኦፊሰር ታምራት ፈረደ (ዳኛቸዉ ወረደ) ሁሉም ነገር ሳይሳካ ሲቀር ተስፋ ቆርጦ እራሱን ከፎቅ ወርዉሮ የሞተ ሰዉ ነዉ። ከመጨረሻዋ ሚስቱ ከወ/ሮ ፀሐይ ዶክሜንቶቹ ተዘርፈዉ ወይም ተሰርቀዉ በእጄዎ ገብተዉ ሊሆኑ ስለሚችሉም ያሰባሰቧቸዉ መረጃዎች መጽሃፉን አጠናክረዉት ቢታይም፣ ስለእነዚህ ስለሞቱ ሰዎች ከሚያቅራሩ ግን፣ እንደ ቆራጧ አርቲስት አስቴር በዳኔ ባለ አራት ነጥብ ኮከቡን የወያኔዉን ጀኔራል ሳሞራ የኑስን ደደቢት ላይ ,,ያን ያደረጋችሁትን ተጋድሎ ሁሉ እናደንቃለን፣ ግን በዕዉነት እናንተ አሁን ሥልጣናችሁን በሰላም ትለቃላችህ? የአንድ አገር ልጆች ሆነንስ ለምን ከተቃዋሚዎች ጋርስ እንደ ጠላት ትተያያላችሁ..ወዘተ በማለት በጥያቄ እንዳፈጠጠችዉ፤ (ያዉም አገር ውስጥ እየኖረች) ወይንም ደግሞ እስኪ እንደነ ኤርምያስ ለገሰ ሀገሪቱን ባለቤት አልባ ስላደረጟት ባለጊዜዎች ደፈር ብለዉ፣ አንድ ይበሉና እርስዎንም እንደነ ሙሉጌታ ሉሌ እንደነ ሐስን ዑመር አብደላ እናክብርዎት እናድንቅዎትም። እርግጠኛ ነኝ ይህን ቢያደርጉ ደግሞ ኖሮዌዎች እንደ ጋሼ ዩሱፍ መጽሃፍ የተዋጣለት ምርቃን እንደሚያደርጉልዎት አልጠራጠርም።

ባጭሩ ጽሁፌን ወደ ማጠቃለሉ ሳመራ እኔ በደባልነት የልብ ወዳጅ ነህ ከሚል ዕምነት በመነሳት ከነክፍለ ሀገሬ ተሰደብኩ እንጂ፣ጽሁፍዎ በዋናነት ያነጣጠረዉ፣ ከዩሱፍ ጋር ባለዎ የግል ጥላቻ በመነሳት፣ እሱ የሚለዉን ሁሉ አትስሙት፣ በተለይ እርስዎን ለሚከተሉ ደቀ መዛሙርትዎ ደግሞ እሱን ከተከተላችሁና የሚጽፈዉንም በእርስዎ አገላለጽ ዝባዝዝንኬ ካነባበችሁ ,,ዉጉዝ ከመ አርዮስ,, ብያችሁዋለሁ ብለዉ የዉግዘት ቡራኬ ለማስተላለፍና ለቡድንዎ ተከታዮች መመሪያ ለመስጠት ነዉ፣ ያን ሁሉ ዙሪያ ጥምጥም የተጟዙትና ያንድ ክፍለ ሀገር ሕዝብ ጭምር የተሳደቡት። ላስተላልፍልዎ የምፈልገዉ መልዕክት ግን ማንኛዉንም ዓይነት የጥላቻ መርዝ ቢረጩ፣ የየሱፍን ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ዉስጥ የሚያስገባ አንድም አምክንዮ ማግኘት እንደማይቻል ላረጋግጥልዎ እንደምወድ ነዉ። እንዲያዉም በልጅነቴ ከደገምኩት መልካጊዮርጊስ አንድ ነገር ልመርቅልዎ!

,,…አፅራርዬ እለ ተንስኡ በነገረ ከንቱ ወበክ፣ ሀመደ ለይኩኑ በፅባሕ ወሰርክ…,, (ያለ ምንም አመክንዮ በከንቱ የሚነሱ ጠላቶች፣ አምድ ዱቄት ይሆናሉ) እንደሚለዉ አባባል፣ መጨረሻዎ የሚያመራዉ ወደዚያ ነዉ። አባቴ በልጅነቴ ካጫወቱኝ ትዝታዎች አሁን እያወራን ካለዉ ርዕስ ጋር ስለሚጎዳኝ ላዉሳና ሃሳቤን ላጠቃል። እርሳችዉ ሲበዛ የአፄ ኀይለ ሥላሴ አምላኪ ስለነበሩ፣ አሁን ይሄ የእናንተ መንግሥት (ደርግን ማለታቸዉ ነዉ) ምን ሥነ ሥርዓት አለዉ? ለመሆኑ ቤተክርስቲያንስ ይሄዳል? አስቀድሶስ ያዉቃል? ይሄ ሊቀመንበር የምትሉትስ ጧት ጧት ሥራ ሲገባ እንደ ንጉሳችን ባለሥልጣናቱ እጅ እየነሱ በፊቱ ያልፋሉ፣ ወይንስ ዝምብለዉ መንጦልጡል ነዉ? ሲሉኝ ግራ ስለገባኝ ምን ማለታቸዉ እንደሆነ ጠየኩኣቸዉ። አየህ፣ በአፄ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ ሁሉም ሥርዓት ነበረዉ። ለምሳሌ ጧት ጧት ተማሪዎች ትምሕርት ቤት ሲገቡ የሀገራችን ብሔራዊ መዝሙር እተዘመረ፣ ለሰንደቅ ዓላማችንና ለብሔራዊ ክብራችን ክብር እየተሰጠ፣ እርሳቸዉም ጧት ሥራ ከመጀመራቸ በፊት ቤተመንግሥት መንበረ ዙፋናቸዉ ላይ ይቀመጡና ባለሥልጣኖቻቸዉም በፊታቸዉ እጅ እየነሱ ያልፋሉ፣ እታዲያ በዚህ ጊዜም በእሳቸዉ ላይ ነገር የሚጎነጉን፣ ተኝቶ የማያድር ባለሥልጣን ካለ፣ ዘወትር አጠገባቸዉ የማትለያቸዉ ዉሻቸዉ በጃንሆይ ላይ ነገር የሚያስብባቸዉ ባለሥልጣን ካለ እሱ በፊታቸዉ ሲያልፍ አምርራ ትጮሃለች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ባለ ሥልጣኑ ጥርስ ዉስጥ ይገባል። በዚህም መሠረት ባንደኛዉ የእጅ መንሻ ቀን ባለሥልጣን ይልማ ደሬሳ የሚባሉ ሰዉ እጅ ነስተዉ ሲያልፉ ዉሻዋ ትጮሃለች አሉ። እታዲያ ምን መሰለህ ቁምነገሩ ዉሻዋ መጮሃ ላይ አይደለም፣ የተጮኸበት ባለሥልጣን የሰጠዉ መልስ ነዉ። አዳምጠኝ ልጄ! ተይ አንች ዉሻ ይልማ ደሬሳ ያላሰበዉን አታሳስቢኝ፣ አሉ መባሉ ነዉ። የየሱፍን ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት መሞከርም እራስን አለማመንና ከዉሻዋ አስተሳሰብም ተነጥሎ የማይታይ ይሆናል።

በእርስዎ አገላለጽ የእኔን የደርግ ካድሬነትም ሆነ ወጭት ሰባሪነቴንም (እንዲያዉም ከዚህ የዘቀጠና ወደታች በጣም የወረደ ስድብም በተለያዩ የራስዎ የብዕር ሥሞች በፌስ ቡክም የለቀቁትን ሳልጨምር ማለቴ ነዉ) በፀጋ ልቀበለዉና አንባቢን እንዳላሰለች አንድ ጥያቄ ልወርውርና ሀሳቤን ልዝጋ። በጽሁፍዎ የመጨረሻ አንቀጽ/ፓራግራፍ ላይ ,,..ሲጀመር ጀምሮ ኤርትራ የምትባል አገር በሕገ ተአምኖ አልነበረችም፣ ወደፊትም አትኖርም። አራት ነጥብ።…, የምትል አረፍተ ነገር አስቀምጠዋል። ይህ አባባል ከልብዎ ከሆነ፣ ማነዉ ከሻዕቢያ ጋር አብሮ ተሰልፎና ተዋግቶ፣ ኢትዮጵያ ትንሽ አገር ትሁንልኝ ብሎ፣ ፀረ ኢትዮጵያ አቑም ወስዶ ለዩናትድ ኔሽን ማመልከቻ ፅፎ ኤርትራን ያስገነጠለዉ? ስለዚህ ጉዳይ እስካሁን እርስዎ ደራሲ ነኝም ይላሉ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላልፉት መልዕክት አለ? እነ ሐስን ዑመር አብደላ/ዩሱፍ ያሲን ግን በተለያዩ ወቅቶችና መድረኮች፤

-,,የወያኔ መቅሰፍቱ…. የሻዕቢያ ቁርኝቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ርቀቱ,, (ሰኔ 1991)፣
-ኢትዮጵያና ኤርትራ-ያልተጠናቀቀ ፍቺ፣ ያልተሳካ ጉርብትና (ኅዳር 1991)፣
-በባድመ ወረራ ወቅት፤ – ማነዉ ታሪካዊ ስህተት የፈጸመዉ? ኢሳይያስ ወይስ መለስ? ፣

ወዘተ….በማለት የኤርትራዉ ኢሳይያስ ታላቅ ስህተት ሠርቶ አላስፈላጊ ጦርነት ዉስጥ መገባቱንና በመሳሰሉትም ወቅታዊ የሀገር ጉዳዮች ፅፈዉ በብዕራቸዉ በአደባባይ ታግለዋል። ወይንስ እርስዎ የኤርትራን ጥያቄ አካኪ ዘራፍ የሚሉበት፣ በተግባር የማይገለጥ፣ ግን የሚጠሉትን ሰዉ ለማስጠላት ሲሉ ደግሞ የሚመዙት የማስመሳያ ካርድ ነዉ? ሀገራችን ኢትዮጵያ በሻዕቢያና በወያኔ ሸርና ተንኮል ቲያትር የተሰራባት ሀገር ነች። እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለዉ፣ በኤርትራ ጉዳይ፣ እኔና እርስዎ የአቑም ልዩነት አይኖረንም። ኢትዮጵያና ኤርትራ ፊዴሬሽኑ ሳይፈርስ ቀጥሎ ቢሆን ኑሮ፣ ውህደቱም ሲፈጸም ፣ (ኤርትራም ከእናት ሀገሯ ከኢትዮጵያ ተቀላቀለች ሲባል) ዓለም አቀፍ ሕግን ተከትሎ ቢሆን ኖሮ፣ እንደገናም የፖለቲካ ጥበብ ታክሎበት የፌዴሬሽኑ መብት ተከብሮ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን ደግሞ በጊዜያችን ሕዝበ ዉሳኔዉ (ሪፈረንደሙ) የሪፈረንደም መስፈርቱን ቢያሟላ ኖሮ (ነጣነትህን ወይንስ ባርነትን) የኤርትራ ሁኔታ የአሁኑን መልክ ላይዝ ይችል ነበር። እንዲያም ሆኖ ግን አሁን ጊዜዉ ,,ኤርትራ ወይም ሞት,, የሚል መፈክር አንግበን በአደባባይ የምንጮህበት ወቅትም አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብም ሻዕቢያን ከማጠናከር ጎኑ ባሻገር ለኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፋይዳ እንደማይኖረዉ ላረጋግጥልዎ እወዳለሁ። እንደ እርስዎና እንደኔ ባለ ምስኪን ስደተኛ ዜጋም የሚወሰን ብሔራዊ አጀንዳም አይሆንም።ችግሩ እኮ አካኪ ዘራፍ ማለቱ ላይም አይደለም። በየጊዜዉ አንደኛዉ የሌላኛዉ ሥጋት ሳይሆን ወይም እንደ አንድ ሀገር ወይም እንደ ድንበርተኛ ጎረቤት ሀገር እንዴት በሰላማዊ መንገድ መኖር ይቻላል ነዉ? ባሉባልታ ነዉ እንጅ የምንለያየዉ በኤርትራ ጉዳይ እንዝመት ካሉም መፍትሄዉም ይሕ ነዉ ብለዉ ካመኑም፣በእኔ በኩል ለመዝመቱ ችግር የለብኝም።በቃ እንዲያዉም ናቅፋ እንገናኝ! ለእርስዎም ከኖርዌይ ብርድ ትንሽ ይገላገሉ። ምናልባት ከዩሱፍ,, ሀገር,, በሰላም ደርሰዉ ከተመለሱም የባሕርይ ለዉጥም ሊያደርጉ ይችላሉና እንሞክረዉ።