በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የግራር ጃርሶ ወረዳ የጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታደሠ ተፈሪ፣ ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ትናንት ምሽት 11 ሰዓት ገደማ በፈጸሙት የደፈጣ ጥቃት መገደላቸውን ተሰምቷል።
ታጣቂዎቹ የደፈጣ ጥቃቱን የፈጸሙት፣ በወረዳው አዲስጌ ቀበሌ ልዩ ስሙ ”ሲልሚ” በተባለ ሥፍራ እንደኾነ ምንጮች ተናግረዋል።
ከሟቹ ጋር አብረው የነበሩት የወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዝናቡ በለጠ፣ ከታጣቂዎቹ የእሩምታ ተኩስ ለማምለጥ ሲሞክሩ ድንጋያማ ገደል ውስጥ ጉዳት እንደደረሰባቸውና ፍቼ ሆስፒታል ለሕክምና መግባታቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል።
አመራሮቹ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው፣ ባካባቢው በሚገኝ አንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምልከታ አድርገው ሲመለሱ እንደኾነ ታውቋል።
ወረዳው ከአማራ ከልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለሚ ወረዳ ጋር ድንበር ይጋራል።