“የባለስልጣናት ያልተገሩ ንግግሮችና የመንግስትም ተቀዳሚ ተግባሩን ፍጹም መርሳት ሕዝብን ለእልቂት እየዳረገ ነው”- እናት ፓርቲ

“የባለስልጣናት ያልተገሩ ንግግሮችና የመንግስትም ተቀዳሚ ተግባሩን ፍጹም መርሳት ሕዝብን ለእልቂት እየዳረገ ነው”- ፓርቲው

እናት ፓርቲ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባወጣውና ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በላከው መግለጫ፣ “መልኩንና ቦታውን እየቀያየረ መላ ኢትዮጵያውያንን የደኅንነት ዋስትና ያሳጣው ሀገራዊ እልቂት አሁን አሁን ወደ ሀገራዊ ቀውስነት እያደገ ነው ለማለት ያስደፍራል” ሲል ተችቷል።

አክሎ፣ “ለዚህ ደግሞ ብዙ የተጠራቀሙና ያልተፈቱ የችግር ቋጠሮዎች ቢኖሩም በዋናነት ባለስልጣናት የሚያደርጓቸው አደገኛ የእልቂት ጠመቃ ንግግሮች ዋነኞቹ ናቸው” ብሏል።

“መንግስት በተደጋጋሚ ቢነገር ችላ ያለውን የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ አለመስራት አሁን ያለንበት ሁኔታ ምን አልባት ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ እያደረሰው ይገኛል” ሲል ወንጅሏል።

በዚህም ሰሞኑን በጅማ ዞን ጌራ ወረዳ ቀበሌዎች በአንድ ግለሰብ ግድያ ምክንያት የተስተዋለውን “ቀውስ” ያወሳው ፓርቲው፣ ግድያውን አውግዞ፣ “ድርጊቱም በውል ተጣርቶ አጥፊዎች ከሕግ ፊት እንዲቀርቡ እናሳስባለን” ሲል ጠይቋል።

የስፍራው ነዋሪዎች ዘርፈ ብዙ በደል እየደረሰባቸው መሆኑን ነዋሪዎች እንደገለጹለት ያተተው መግለጫው፣ በጅማው “ቀውስ” “በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ተቃጥለዋል። ወፍጮ ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ሱቆች እየጋዩ ነው። ‘ይህም ማንነት ተኮር ነው’፣ ‘አማራ ነው ያሉትን ንብረት እየመረጡ ነው የሚያቃጥሉት’ ብለዋል” በሚል ተጠናቅሯል።

“ብዙ ሺህ ሰው አካባቢውን ለቆ ከፋ ዞን ተጠልሏል። በተለይ የአቅመ ደካሞች፣ ሕጻናትና ነብሰ ጡሮች ስቃይ አሳዛኝ ነው፤ በሽሽት ላይ ሳለች የወለደች እናት እንዳለችም ይናገራሉ” በማለት የነዋሪዎቹን እሮሮ ጠቃቅሷል።

የከፋ እለቂት ሳይደርስ መንግስት ድርሻውን እንዲወጣ፣ ተፈናቃዮች እንዲመለሱ እንዲደረግ፣ ገዳዮችና አሳዳጆች ለፍትህ እንዲቀርቡ፣ ‘የሰባብረናቸዋል’ ዓይነት ንግግሮች እንዲቆሙና ማስተባበያዎች ይቅርታ እንዲጠየቅባቸው ፓርቲው በመግለጫው ጠይቋል።