እናት ፓርቲ፣ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጣለው የጣርያና ግድግዳ ግብር እንዲታገድ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያሳለፈው ውሳኔ አፈጻጸሙ እንዲታገድ ማዘዙን አስታውቋል።
ፍርድ ቤቱ የአፈጻጸም እግድ ውሳኔ የወሰነው፣ የከተማዋ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ የፍርድ አፈጻጸሙ እንዲታገድለት ያቀረበውን ይግባኝ ከመረመረ በኋላ እንደኾነ ፓርቲው ጠቅሷል።
ኾኖም ፓርቲው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እግድ ተገቢነት እንደሌለው ገልጦ፣ ትላንት ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቤቱታ ማቅረቡን ገልጧል።
የይግባኝ ሰሚ ችሎቱም፣ ይግባኝ ባዩ የከተማዋ ፋይናንስ ቢሮ በፓርቲው አቤቱታ ላይ አስተያየት እንዲሠጥ ትዕዛዝ በመስጠት መጋቢት 10 ቀን በጉዳዩ ላይ የመጨረሻውን ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሠጥቷል ተብሏል።