በአዲስ አበባ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ስደተኞችና ፍልሰተኞች በዘፈቀደ እየታሰሩ መሆኑ ተሰምቷል

ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ የተሰኘው የመብት ተሟጋች ድርጅት፣ በአዲስ አበባ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ስደተኞችና ፍልሰተኞች በዘፈቀደ መታሠራቸውን እንደሚያውቅ ተናግሯል።

ስደተኞች ‘ወደ መዲናዋ ለምን ገባችሁ?’፤ ፍልሰተኞች ደሞ ‘ለምን የአገሪቱን ድንበር ያለ ጥሳችኹ ገባችኹ?’ በሚል ምክንያት እስከ ሦስት ወራት ታስረው እንደሚገኙ የገለጠው ድርጅቱ፣ መንግሥት እስር ላይ የሚገኙትን ፍልሰተኞች ወደ አገራቸው እመልሳለኹ እያለ እንደኾነ ጠቁሟል።

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የጸጥታ ኃይሎች እስር እየፈጸሙ መኾኑን መረዳቱንም ድርጅቱ ጠቁሟል።

በኤርትራዊያኑና በትግራይ ተወላጆች ላይ በሚፈጸመው እስር ዙሪያ ግልጽ ምርመራ እንዲደረግና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ድርጅቱ የጠየቀ ሲኾን፣ መንግሥት የስደተኞችን፣ ፍልሰተኞችንና ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መብት እንዲያስክብርም አሳስቧል።