ኦሮሚያ ክልል የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በተፈጸመባቸው ጥቃት ሳቢያ ከቀያቸው ተፈናቀሉ

በኦሮሚያ ክልል፣ በጅማ ዞን፣ ጌራ ወረዳ፣ ዋላ በሚባል ቀበሌ በሺሕ የሚቆጠሩ የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በተፈጸመባቸው ጥቃት ሳቢያ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ወደ አጎራባች ክልሎች መሄዳቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ዘግቧል።

ከሐሙስ ጀምሮ እምነቱ ተከታዮች ላይ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት፣ የበርካታ የዕምነቱ ተከታዮች መኖርያ ቤቶች፣ የንግድ መደብሮችና ሌሎች ንብረቶች እንደተቃጠሉ ተፈናቃዮቹ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

ጥቃቱን ተከትሎ፣ በቀበሌው የሚገኙ ስምንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናትም ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል። የጥቃቱ መነሻ ምን እንደኾነ ለጊዜው እንዳልታወቀ ዘገባው የገለጠ ሲኾን፣ የጥቃቱን ፈጻሚዎች ማንነትም የዜና ምንጩ አልጠቀሰም።