ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የተዘጋጀ ትምህርተ ወንጌል በድጋሚ አቅርበንላችኋል። ቀሲስ በትምህርታቸው አፅንኦት የሰጡበት በቤተክርስቲያን ላይ የሚፈጸሙ ህጸጾችና ወንጀሎች መፍትሄ በማግኘት ፋንታ ጭራሽ እየተባባሱና ስር እየሰደዱ መጥተዋል።
“ምኩራብ” በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
ባለንበት ዘመን የኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ የምትከለክለውን በጳጳሳት፣በመነኮሳት፣ በቆሞሳት፣በቀሳውስትና በዲያቆናት የሚፈጸሙ መታረም የሚገባቸው ብዙ ጥፋቶች አሉ። ምኩራብ ውስጥ መግባት የማይገባቸው የተለያዩ በሬዎች፣ በጎች፣ርግቦች እንደገቡ ሁሉ አሁንም በዘመናችን በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ መከሰት የሌለባቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ። ባጭሩ ለመጠቆም፤
1ኛ፦ የተደራረቡ የቅጽል ስሞች፣
2ኛ፦በተለይ በውጭ ዓለም ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ “ድርብ ታቦታት” እየተባሉ የሚነገሩ ጽላቶች፣
3ኛ፦በዝሙትና በዘረፋ የሚወቀሱት ጳጳሳት፣ መነኮሳት፣ ካህናትና ዲያቆናት ያላንዳች ሀፍረት በድፍረት በቤተ መቅደስ ውስጥ አገልግሎት መሰለፋቸው፣
4ኛ፦ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚደረገው ጥፋት ይታረም ከሚሉት እንደ ቀሲስ አስተርአየ ዓይነት ሰዎች ጋራ ከመተባበርና አብሮ ከመስራት ይልቅ፤ ጥፋቱና አጸያፊው የሃጢአት ስራ እንዲቀጥል የሚረባረቡ እንዲሁም ይታረም የሚለውን ድምጽ ለማፈን የሚታገሉት ሰዎች የበዙበት ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው።
ለሀገር፣ ለእምነት፣ ለታሪክና ለትውልድ የሚዋደቁትን ቀቅለው የበሉ፤ ከሚካሄደው የኃጢአት ዝቅጠት ውስጥ ትርፍ በመሸመት ላይ ያሉ፤ ለግል ጊዜያዊ ደስታ ብቻ ሲሉ፤ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ይህን በምኩራብ ውስጥ የሚደረገውን ስህተት ለመቃወም ስልጣን ማን ሰጠህ?” እያሉ እንደታገሉት ሁሉ አሁንም በዘመናችን “በቤተክርስቲያን ላይ የሚሰራው ወንጀል ይቁም፣ የሚደረገው ጥፋት ይታረም” ከሚሉት ጋራ ተሰልፈው መታረም የሚገባው እንዲታረም ከመታገል ይልቅ ከአጥፊዎቹ ጋር የሚተባበሩት በርክተዋል። የመከራውም ዘመን እንዲራዘም የሚያደርጉም አነሱና ተከታዮቻቸው ናቸው።
ለአብነት ለመጥቀስ ያህል አሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ ውስጥ በዝሙት ምክንያት ከስልጣነ ክህነቱ የተወገዘውን ታደሰ ሲሳይን እንዲሁም ዋሽንግተን ሲያትል ውስጥ ይማሩ ከነበሩበት መንፈሳዊ ኮሌጅ ውስጥ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር የዝሙት ድርጊት እንደፈጸሙ በማስረጃ አረጋግጦ ያባረራቸውን “አቡነ” ኤውስጣጢዎስን “የተቀደሰውን ቤተክርቲያን ማርከሳቸውን ያቁሙ፣ በዝሙት ስለወደቁ የክህነት አገልግሎት መስጠት አይችሉም” በማለት የሚታገሉ እውነተኛ አባቶችን የሚተናነቁና የሚያሳድዱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ላይ ከሰነዘረው ጅራፍ፤ እጅግ የበለጠ የእሳት ጅራፍ እንደሚጠብቸው ይህ ትምህርተ ወንጌል በአጽንኦት ያስገነዝባል። ይህን አብይ ጉዳይ በዝርዝር አብላልቶ ለመረዳት ቪድዮውን ይመልከቱ።