I’ve co-produced an episode of Al Jazeera English’s The Listening Post and it airs tomorrow. We investigated the Israeli government’s flying out of journalists and influencers from African countries to Israel, where they produce content that polishes Israel’s reputation and downplays genocide in Gaza. Ethiopian journalists were among the most effective of those commissioned. Tune in from 19h30 GMT (time edited).
ላለፉት 5 ወራት ከአል ጀዚራ ጋር በመስራት ያዘጋጀሁትን ስራ ነገ በአል ጀዚራ ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከምሽቱ 4:30 ጀምሮ ይተላለፋል። ከዛ በኋላ አልጀዚራ በዩቱብ ቻነሉ ያስቀምጧል።
የእስራኤል መንግስት በጋዛ ግዛት በሆኑት ፍልስጤማውያን ላይ ከፈረንጆቹ 2023 ዓመት ጀምሮ የዘር ፍጅት ወንጀል በመፈጸሙንና በግምት እስከ 70ሺህ ሰዎችን መግደሉ በሰፊው ተዘግቧል። ከተጨፈጨፉት መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት ናቸው። አምኔስቲ፤ ሂውማን ራይትስ ዋች እና በተመድ የተመደቡት የሰብዓዊ መብት ተመራማሪዎች ሁሉ በጋዛ የተፈጸመው ጭፍጨፋ የዘር ፍጅት መሆኑን ሶሥቱ ተቋማት በመሩት ምርመራዎች አረጋግጠዋል።
እስራኤል ወታደሮቿን ወደ ጋዛ መላክ ሲጀምር ከምዕራብ ዓለም ከባድ ተቃውሞ ግጥሞታል። ምንም እንኳን በበርካታ ምዕራብ አለም መንግስታት የቁሳቁስና የመሳሪያ ድጋፍ እያገኘ ቢሆንም በህዝብና በተለይ በወጣቱ ትውልድ እስራኤል እየተጸየፈ መጥቷል። በተለይ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የገጠመው ተቃውሞ ካምፐሶች እና የታላላቅ ከተማ መንገዶች በየ ሳምንቱ በፍልስጤም ባንዲራ እንዲጥለቀለቁ ተደርገዋል።
የእስራኤል መንግስት በአሜሪካና በአውሮጳ ባሉት ወጣቶች ተስፋ የቆረጠ ይመስላል።
ትኩረቱን ወደ አፍሪካ አዙሯል።
ከ2024 ጀምሮ የእስራኤል መንግስት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጋዜጠኛን እየመረጠ ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፈን ወደ እስራኤል ያመጣችዋል። በአንድ ሳምንት ቆይታቸው የተለያዩ የቱሪስት መዝናኛዎች ታሪካዊ የሃይማኖት ስፍራዎችን እንደገና ደግሞ በኦክቶበር 7 የሃማስ ጥቃት የተፈጸመበት ስፍራም ያስጎብኟችዋል።የእስራኤል መንግስት ከጋዜጠኞቹ የሚጠይቀው አንድን ነገር ብቻ ነው፤ የእስራኤል መንግስቱ “እውነት” ብሎ የሚያምነውን እንዲዘግቡ።
እስካሁን ድረስ ከተመላሽ ጋዜጠኞች ተዘጋጅቶ የሚቀርቡ ሪፖርቶች በሙሉ ለእስራኤል አድሎዓዊነት የሚያሳዩ የፍልስጤምን ህዝብ መጨፍጨፍን የሚያደባብሱ እና የእስራሌል ስራዊት የወሰደው እርምጃ ራስን ለመከላከል እንደተደረገ አድርጎ ነው የሚቀርቡት።
ከኢትዮጵያ ጨምሮ ከሴኔጋል ሞሮኮ ካሜሩን ሩዋንዳ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ሁሉ ሳይቀሩ የተጓዙ አሉ። የእስራኤል መንግስት ከሃገር ሃገር ያለውን ሁኔታ እያጠና ነው ሰውን መልምሎ የሚልከው። ለምሳሌ፤ ከኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት መርህ የማያከብሩ ባለሙያዎችን አፈላልጎ መላክ ቀላል ሆነላቸው። በኬንያ እጅግ ጠንካራ የፕሬስ ባህል ያለበት ሃገር በመሆኑ ጋዜጠኞችን አፈላልጎ መላክ አልቻሉም። ከኬንያ ተመልምለው የተላኩት ቲክቶከር እና የክርስትያን መዝሙር ዘማሪን ብቻ ነው።
ከሞሮኮ እና ከደቡብ አፍሪካ የተላኩት ጋዜጠኞች ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ ከሙያ ባልደረቦቻቸው ከባድ ተቃውሞ ስለገጠማቸው የረባ ሪፖርት ማቅረብ ተሳናቸው። 3 የደቡብ አፍሪካ ጋዜጦች ከእስራኤል ባቀረቡት ዘገባ በኋላ የይቅርታ መልዕክት በየሪፖርቶቻቸው ለማቅረብ ተገደዱ። ከሞሮኮ ሁለተኛ ጉዞ ለማዘጋጀት ታስቦ ጋዜጠኛ ባለመገኘቱ ባህላዊ ዘፋኝ እና ተወዛዋዦች ናቸው የሄዱት።
አሳፋሪ የሆነበት ምክንያት አንዱ እሱ ነው። በሌሎች አፍሪካዊ ሃገራት በምሁሮች በጋዜጠኞችና በሰፊው ማህበረሰብ የህዝብን ቁጣ የቀሰቀሱ ሆነው እኛ ሀገር ምንም አለመባሉ ነው። የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ሀገር ሆነን ለሌላው አርዓያ ነን እያልን የምንፎክር።
ወደ እስራኤል የተጓዙት ኢትዮጵያዊ የሚዲያ ተቋማት የትኞቹ ናቸው?
ወደ እስራኤል ያመሩት ኢትዮጵያዊ የሚዲያ ስብስብ ሲዘረዘር አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ አሃዱ ራዲዮ፤ ኤንቢሲ፤ ኦቢኤን፤ አሚኮ፤ ኢቢኤስ፤ አርትስ ቲቪ፤ ቁምነገር መጽኤት፤ እግረኛው ሚዲያ እና ትንሽ ስም ያለው የ ዘ ሪፖርተር ጋዜጣ ሁሉ ሳይቀር ነው በህዳር ወር አንድ ሳምንትን በቴል አቪቭ በእየሩሳሌም እና ሌሎች ቦታዎችን ያሳለፉት። በአጠቃላይ ከነዚህ ተቋማት 20 ባለሙያዎች ናቸው የተጓዙት።
ከእስራኤል መልስ በተላላኪዎቻችን የቀረቡ ሪፖርቶች ዶኩመንተሪ ፊልሞች የጋዜጣ እና የመጽሄት እትሞችን በሙሉ መርምርያለሁ ማለት እችላለሁ። ጠቅላላው ለማየት እና ለማንበብ የሚያሳፍሩ የሚዘገንኑ የሙያችን ስነ ምግባርን የሚጥሱ ናቸው። ፍልስጤም የሚባል ህዝብ እንደሌለ ወይ ደግሞ አብዛኛው ሟች በእስራኤል በኩል እንደነበር ተደርጎ የተሰሩ ስራዎችም ነበሩ። ሌሎቹ ስለ ልማት ስለ ግብርና እና ቴክኖሎጂ ወይ ሃይማኖታዊ ትኩረት ያሉ ሪፖርቶችን አዘጋጅተዋል። በብዙዎቹ ዘገባ በቤንጃሚን ነታንያሁ የሚመራው በገዢው ሊኩድ ፓርቲ አባል የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊት የእስራኤል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቅርቧል። እንግዲህ የሊኪድ ፓርቲ ነው ጦርነት አስነስቶ ለብዙ ጦር ወንጀል ተጠያቂው የሆነው።
እስካሁን ድረስ በእስራኤል መንግስት ተመልምለው ወደ ሃገራቸው ከተመለሱት አፍሪካዊ ተላላኪዎች መካከል የኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞቹ ያህል እስራኤልን ያገለገሉ አልተገኘም። ከመንግስት እና ከግል ሚዲያ ተመልምለው ደርሰው የተመለሱት በየሪፖርቶቻቸው እስራኤልን ሲያሞግሱ ነው የከረሙት። አንዳንዶቹ ሳይጓዙ ሁሉ ነበር ስለ እስራኤል በጎነት ሲዘግቡ የነበሩት።
ከማንኛውም ሀገር መንግስት ገንዘብ ተቀብሎ ጉዞ አድርጎ ላኪው ሃገር ባዘዘው ኤዲቶሪያል አካሄድ ሪፖርት ማዘጋጀት በጋዜጠኝነት ሙያ የደንብ ጥሰት ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ Society of Professional Journalists ተብሎ የሚጠራው የጋዜጠኞች ስብስብ ተስማምተው ባሳተሙት የአስራር ዝርዝር ውስጥ በሁለተኛው ምዕራፍ ሁለተኛው አንቀጽ ይሄ ነገር መከልከሉን ይገልጻል። አፍሪካ ላይም ቢሆን የደቡብ አፍሪካው ፕሬስ ካውንስል (The Press Council of South Africa) ባወጣው የባለሙያዎች ደንብ እና አሰራር ዝርዝር ውስጥ በምዕራፍ 2 አንቀጾች 2.1 እና 2.2 ይሄ ነገር የተከለከለ ነው። በኛ ሃገር ምንም እንኳን መንግስቱ ራሱ የማያከብረው ቢሆንም ከ5 ዓመታት በፊት መንግስት ያጸደቀው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ላይም ሳይቀር ክፍል 4 አንቀጽ 2 ሚዲያ “ከመንግሥት፣ ከፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ቁጥጥር” ነጻ መሆን አለበት ተብሎ ተዘርዝሯል።
ከሙያዊ ስነምግባር ጥሰት አልፎ የህጻናት እና የሴቶች አሰቃቂ እልቂት በሚፈጸምበት ወቅት የግፍ ፈጻሚውን ገጽታን ለመገንባት ተስማምቶ ወደ እስራኤል መጓዙ ተጓዦቻችን ጋር ሞራላዊ ጥያቄ አለማስነሳቱ እጅግ አሳዛኝም አስገራሚም አስፈሪም ጭምር ነው። የተጠቂዎችን ድምጽ ማፈንም ሞራላዊ ሙያዊ ጉድለት ያሳያል። በተለይ ከሌሎች አፍሪካውያን ሃገራት ጋር ሲነጻጸር የሃገራችን ፕሬስ ያለበትን ዝቅተኛ ቦታ ግልጽ አድርጎ ያሳያል።
እጅግ አስቂኙ ነገር እዚህ መሃል ወደ እስራኤል ካመሩት ጋዜጠኞቻችን መካከል አንዱ አቶ ታምራት ሃይሉ ይባላሉ። አቶ ታምራት የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ቦርድ አመራር ውስጥ ያሉ ሰው ናቸው። ካውንስሉ የተቋቋመበት አንዱ ምክንያት የጋዜጠኝነት ሙያዊ ስነምግባርና አሰራር በኢትዮጵያ እንዲጠበቅ ማበረታታት ነው። የካውንስሉ አመራር ለራሱ የማያከብረው ስነምግባርና አሠራርን ነው እንግዲህ ካላከበራችሁ ለመንግስት ነው የምንጠቁመው እያሉ ጋዜጠኞች ላይ የሚዝተው።
እስራኤል መሄዳቸው ችግሩ አይታየኝም የሚል ሰው አይጠፋም። እንዲህ የሚል ሰው እነ አሚኮ በድሮን ጥቃት ብንትንትናቸው ወደ ወጡ የአማራ ክልል ስፍራዎች አምርተው ስለ ኮሪዶር ልማቱ ነገ ቢዘግቡ መቆጣት አይችሉም!
እኛ ምን አገባን የሚል ሰው አይታጣም። “የራሷ አሮባት” የሚል ምላሽ ለዚህ ጥያቄ ሲሰጥ እይቻለሁ ከዚህ ቀደም።
ይሄ አቋም የጭካኔ ጥግ ከመሆኑ አልፎ በሙያችን ቦታ የሌለው አስተሳሰብ ነው። ሰው ሰው ነው፤ ከየትም ይምጣ። ከጋዛም ይምጣ ከጋሞ።
ሁለተኛው ነገር እነዚህ ሚዲያዎች ለሀገር ውስጡ እልቂት ቦታ አለመስጠታቸው ቢያሳዝንም የፕሬስ ነጻነት የሌለበት ሀገር ላይ ስራውን መስራት የት እንደሚያደርስ ስለምናውቅ እዚህ ላይ ብዙም አልፈርድባቸውም።
ሆኖም ግን እስራኤል ድረስ ያለመሄድ አማራጩ ነበራቸው። ከእስራኤል ያዘጋጁትን ስንመለከት ሁሉም አምነውበት እንደሄዱ ያሳያል። ለዚህ ደግሞ ሙያዊና ሞራላዊ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል።
ከዛ አልፎ በየ ስልኮቻችን በየሚዲያውና ማህበራዊ ድረገጾች ላይ ሁለቱን ዓመት ሙሉ የጋዛ ህጻናት እና እናቶች ሞትና ለቅሶን ያላየ ሰው አለ ማለት አይቻልም። የጋዛ ህዝብን ሰቆቃ የዓለም ህዝብን በሃዘን እና በብስጭት ያዋሃደ ነው። ሰብዓዊነት የሚሰማው ማንኛውም ሰው ሰው አይጨፍጨፍ ህጻናት አይራብ ነው ማለት ያለበት። በተለይ ኢትዮጵያዊ ሆነን የረሃብ እና የድሮን ጥቃት ሰለባ የሆኑት ምስኪን ህዝቦች በሁሉም ክልል ነዋሪ በሆኑበት ሀገር በረሃብና በእስራኤል አየር ድብደባ ለሚያልቀው ህጻናት ልባዊ ሃዘኔታ ሊኖረን ይገባል።
ሰፊው የኢትዮጵያ ፕሬስ ቤተሰብን ወክለው የሄዱት ጋዜጠኞች አዋርደውናል ማለቱ ማጋነን አይሆንም።
ፎቶዎች፡ የኛ ጋዜጠኞች በእስራኤል ፓርላማ እና በጋዛ ጉዳይ ሃሰተኛ መረጃን በመዘገብ እና ጦርነት በማቀጣጠል የሚታወቀው እስራኤላዊው የ I24 News ዜና ጣብያ ተሰብስበው ሲጎበኙ የተነሱት ፎቶ።
ነገ በአል ጀዚራ በቴሌቪዥን ቻነሉ ከምሽቱ 4:30 ጀምሮ ይጠብቁን! ምርጥ እህቴ የሆነችው ዶክተር ትምኒት ገብሩም በጉዳዩ አስተያየቷን ትሰጣለች።
የነገ ሰው ይበለን!