አፍሪካውያን ስደተኞች በሚያንማር ሀገር ካምፖች የሚደርስባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደቀጠለ ነው

My story on Africans suffering in Myanmar’s scam camps, on page A5 of Tuesday’s edition of Canada’s The Globe and Mail newspaper. ( ዘካሪያስ ዘላለም )
  • በሚያንማር ሀገር ስለሚሰቃዩት አፍሪካውያን ስደተኞች ዙሪያ ያቀረብኩት ሪፖርቴ በካናዳው የግሎብ ኤንድ ሜል ጋዜጣ ለእትም ቀረበ።
  • አፍሪካውያን ስደተኞች በሚያንማር ሀገር ካምፖች የሚደርስባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደቀጠለ ነው።
  • ከአፍሪካ ተነስተው በታይላንድ አድርገው ወደ ሚያንማር ታግተው የሚወሰዱ ስደተኞች ችግር እስካሁን መፍትሄ አላገኘም።
በሚያንማር የሚንቀሳቀሱ ቻይናውያን ወንጀለኞች ወይም የማፊያ ቡድን ነገሩን የሚጀምሩት በቴሌግራምና በዋትሳፕ የስራ ማስታወቅያዎችን በመልቀቅ ነው። ስራው በታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ የሚሰራ የኮምፒውተር ስራ መሆኑንና እንግልዘኛን የሚያወሩና የኮምፒውተር አጠቃቀም የሚያውቁ ተመራቂዎችን እንደሚፈለጉለት ማስታወቅያዎቹ ይገልጻሉ። በወር ከ500 ዶላር እስከ 1000 ዶላር ተከፋይ ትሆናላችሁ እያሉ በርካታ ወጣቶችን አታለዋል። ወጣቶቹ ወደ ባንኮክ ካመሩ በኋላ የማፊያው ቡድን ደላላዎች ኤርፖርት በመኪኛ ተቀብለዋቸው እስከ ሚያንማር ድንበር ድረስ ይጓዛሉ። ድንበሩን በግድ ካሻገሯቸው በኋላ ነው እንግልቱ የሚጀምረው። ሚያንማር ድንበሩ አከባቢ ወደሚገኙ ማጉረያ ካምፖች ተወስደው በኮምፒውተር የሳይበር ወንጀል እንዲፈጽሙና ለቡድኑ ገቢ እንዲያስገቡ ይገደዳሉ። ክፍያ የሚባል ነገር የለም። እምቢ ያሉት ለድብደባ ለጾታዊ ጥቃት ይዳረጋሉ። ስደተኞቹ በነዚህ ካምፖች ተገድለው ሁሉ ያውቃሉ። አብዛኛው ታጋች የተማሩ ዲግሪ ያላቸውና ሃገራቸው ላይ በስራ አጥነት ተስፋ ቆርጠው እድሌን ልሞክር ብለው የመጡ ወጣቶች ናቸው።
እአአ በ2021 በሚያንማር የመፈንቀለ መንግስት ይከሰታል። የመንግስት ግልበጣውን የተቃወሙ ሃይሎች ወደ ትጥቅ ትግል ይገባሉ። ከ2021 ጀምሮ ሚያንማር በእርስበእርስ ጦርነት ተናውጣለች።
በጦርነቱ ምክንያት በገዢው መንግስት ቁጥጥር ያለው የሚያንማር መሬት የሃገሪቱ አንድ አምስተኛውን እንኳን አይሞላም። ቀሪው ቦታ በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ቁጥጥር በመሆኑ ከቻይና የመጡ የማፊያ ቡድኖች ከታጣቂዎች ጋር የገንዘብ ስምምነት አድርገው በግዛቶቻቸው የሳይበር ወንጀል የሚፈጸምበት ካምፕ ወይም የ”ስካም” ካምፕ (scam camp) እንዲገነቡ ይፈቀድላችዋል። በካምፖቹ ታግተው ያሉ ስደተኞች በአሜሪካና በአውሮጳ ያሉት የስልክ ተጠቃሚዎችን እንዲያታሉ ነው የሚታዘዙት። የውሸት ፍቅር ግንኑነት በዋትሳፕ ወይም በቴሌግራም አስጀምረው ገንዘብ እንዲላክ ማስደረግ ወይ ደግሞ በክሪፕቶከረንሲ እንዲያጭበረብሩ ነው የሚጠየቁት። በካምፖቹ የመንቀሳቀስ መብት የለም። ቤተሰብ ጋር መደወሉም አይፈቀድላቸውም። በቻይናዎቹ ወንጀለኞች ጥብቅ ክትትል አለው። በወሩ መጨረሻ በማጭበርበር ያስገኙት ገቢ የተጠየቀውን ኮታ የማያሟላ ከሆነ እጅግ አሰቃቂ ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው ከካምፖቹ ወደ ሃገራቸው የተመለሱት ስደተኞች አስረድተውኛል።
እንደ ተመድ ግምት ባለፉት 5 ዓመታት ከ120 ሺህ በላይ ስደተኞች በዚህ መንገድ በህግ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ወደ ሚያንማር ተልከዋል። ከነዚህ መካከል ቢያንስ ከ40 በላይ ሀገራት የተወጣጡ ስራ ፈላጊዎች ሲሆኑ አብዛኛዎቹ ከአፍሪካ እና ከእስያ የመጡ ናቸው።
መሰረት የተባለች አንዲት ተመላሽ ኢትዮጵያዊት ስለሁኔታው ስታስረዳኝ “አንዳንዴ ቻይናዎቹ ቅጣት ሊቀጡን ሲፈልጉ በአከባቢው የሚገኙ የሚያንማር ታጣቂዎችን ይጠራሉ። ከስካም ካምፑ አውጥተውን ወደ ጦር ካምፓቸው ወስደው ያሰቃዩናል።” መሰረት DKBA (Democratic Karen Benevolent Army) ကလို့ထူးဘောဌာနချုပ် የተባለው ሚሊሻ ወደ ካምፓቸው ወስድዋት ለወራት ያህል ምግብ ክልከላ ድብደባ እንደገና ደግሞ እራቁቷን ጸሃይ ፊት እየተቃጠለች ለሰዓታት እንድትቆም አድርገው እንዳሰቃይዋት ነገረችኝ።
ከካምፖቹ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ ያለኝ አንድ ሌላ ተመላሽ ከፓኪስታን ህንድ ፊሊፒንስ ሩዋንዳ ናይጄሪያ ኬንያ እና ከኡጋንዳም የመጡ ዜጎች ከአንድ ካምፕ ወደ ሌላ ካምፕ በደላሎች ሲሸጥ እንዳገኘቻው ገለጸልኝ።
ስልክና ፓስፖርት ተቀምተው ለቤተሰብ ያሉበትን ሁኔታ መግለጽ የሚችሉበት እድል ስለማይገኝ ቤተሰቦች በከባድ ጭንቅና ሃዘን ይዋጣሉ። ሃብታሙ የተባለ አንድ ኢትዮጵያዊ ለአንድ ዓመት ተኩል በካምፖቹ አሳለፈ። እንደ ታላቅ ወንድሙ አገላለጽ ሃብታሙ የተጭበረበረው በካምፑ በሚገኝ የትምህርት ቤት ጓደኛው ነበር። “እዚህ ታይላንድ ና ይለው ነበር። ጥሩ ክፍያ አለ ስራው ቀላል ነው አለው። እሱ ለካ ከደላላዎቹ ጋር ተመሳጥሮ ወንድሜ ላይ ክህደት ፈጸመ። በደካማ ጎኑ መጣበጥ።”
ዘመድ ወይ ጓደኛን በማታለል ወደ ሚያንማር እንዲመጡ የሚያደርጉ ስደተኞች እስከ 300 ዶላር ከቻይናው የማፊያ ቡድን እንደሚቀበሉ የተለያዩ ሰዎች ነግረውኛል። ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ስደተኞች መካከል ተጨማሪ ወገንን በዚህ መንገድ ለስቃይ ዳርገው ገንዘብ ያስገኙ እንዳሉም ሰማን። ሃብታሙ እስኪመለስ ወንድሙ የባንክ ሰራተኛ ሆኖ ለ18 ወራት ሙሉ በጭንቀቱ እና በወላጅ እናቱ ሃዘን ምክንያት ስራውን መስራት እጅግ ከብዶት እንደነበርም አስረዳኝ።
ስደተኞቹ ከወንጀለኞቹ እጅ እንዲያመልጡና ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ከሚጥሩ የታይላንድ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መካከል አንዱ CSNHTV (Civil Society Network for Victim Assistance in Human Trafficking) የተባለው ነው። ጄ ክሪቲያ (Jay Kritiya) ተብላ የምትጠራው የድርጅቱ ተቀጣሪ እንዳስረዳችኝ ባለፉት 5 ዓመታት በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሚያንማር ካሉ ካምፖች በድርድር እንዲለቀቁ አድርጓል ድርጅቱ። ይሄንን ለማድረግ ሚያንማር ካሉ የመንግስትም የተቃዋሚ ታጣቂዎችን በማነጋገርና በተጨማሪም ታይላንድ ካለው የድንበር ጠባቂ ሃይልን በማግባባት ነው። በጥቅምት እና ህዳር ወራት ብቻ በCSNHTV ጥረት ከ130 በላይ ስደተኞች ከካምፕ እንዲወጡ ተደርገው ከነዚህ መካከል ግማሾቹ ኢትዮጵያዋይን እንደነበሩም መረጃው ደርሶናል። ሃብታሙ በዚህ ወቅት ነበር የ18 ወራት የሚያንማር ቆይታው የተጠናቀቀው።
ከካምፖች ወጥተው ከሚያንማር ወደ ታይላንድ ሲመለሱ የታይላንድ መንግስት ታጋቾቹን በቁጥጥር ስር ያውላል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ስደተኞቹ በ “ህገወጥ መንገድ” ወደ ታይላንድ በመምጣታቸው ነው። የስራ እድል አግኝተናል ብለው የሚመጡት ስደተኞች ህጋዊ በታይላንድ ሀገር በተመዘገበ የንግድ ተቋም ተጋብዘው መምጣታቸውን ነው የሚያውቁት። የትም ባልተመዘገበ የማፊያ ቡድን ግብዣ ተታልለው መጠራታቸውን ባያውቁም ሁሉም ወደ እስር ቤት ነው የሚወሰዱት።
ወደ ታይላንድ ከተዘዋወሩ በኋላ የኤምባሲዎች ስራ ይጀምራል። ፊሊፒንስ ህንድ ቻይና የመሰሉ ሀገራት በአፋጣኙ ለዜጎቻቸው የአየር በረራም ሆኖ በህገወጥ መንገድ ለመጡበት የቅጣት ውጪዎችን ሙሉ ሸፍነው ዜጎቻቸውን ከእስር አስለቅቀው ወደ ሀገራቸው ይመልሷችዋል።
 እንደ ኢትዮጵያ ዚምባብዌ ኡጋንዳ ቡሩንዲና ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ግን የዜጎቻቸውን ቲኬት ወጪ የመሸፈን አቅሙ ወይ ፍላጎት ስለሌላቸው ከነዚህ ሃገር የመጡ የሚያንማር ታጋቾች ለበርካታ ወራት በታይላንድ እስር ቤት ቆይታ ይጉላላሉ። የኤምባሲ ሰራተኞች በፓስፖርት እና በመመለሻ ሰነድ ለሚስተናግዱ ጥያቄዎች ወደ እስር ቤቶች የሚያመሩ ቢሆኑም የአየር ቲኬት ጉዳይን በተመለከተ ሃላፊነቱን በተመድ ስር ለሚንቀሳቀሰው ለዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ያስረክባሉ።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለፉት 12 ወራት ወደ ሃገራቸው ሊመለሱ የቻሉት በየዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት ወይ ደግሞ በታይላንድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ትብብር እንደሆነ ተመላሾቹ ያስረዳሉ። የቲኬት ወጪ ለመሸፈን አቅም ያጡ እና እስከ አንድ ዓመት ሙሉ በእስር ቤት የቆዩ ስደተኞች እንዳሉም ጄ ክሪቲያ አስረድታናለች። ይሄ የሆነው ደግሞ የተመድ እና አጋር ድርጅቶቹ የገንዘብ ማነስ ችግር ገጥሞናል በማለታቸው ነው።
በሚያዚያ 2017 የተመድ ባወጣው መግለጫ ቁጥራቸው ከ1000 ያላነሱ ከሚያንማር ካምፖች ለተረፉ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አስተላልፎ ነበር።
የታይላንድ መንግስት በጉዳዩ እጅግ መበሳጨቱ ጄ ክሪቲያ ትናገራለች። አፍሪካውያንን አሳስሮ የማብላት እና የማቆየት አቅም ውስን በመሆኑንና የታሰሩት አፍሪካውያን ቶሎ ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው ምንም ዋስትና እንደሌለ በመረዳቱ የሚያንማር ድንበር ላይ ያሉ የታይላንድ ድንበር ጠባቂዎች አፍሪካውያንን ወደ ሃገር እንዳይገቡ እየተከለከሉ መሆናቸውንም ጨምራ ታስረዳለች። ሚያንማር ድንበር አከባቢ መግቢያ መውጫ ያጡት ስደተኞች ችግር አሳሳቢ የሚያደርገው 1/ ድጋሜ በሌሎች ወንጀለኞች ታግተው እንደአዲስ ወደ ሌላ ካምፕ የመወሰድ እድል አለ 2/ የሚያንማሩ ጦርነት ቅርባቸው በመሆኑ ውግያ ወይም የአየር ድብደባም የሚፈጸምባቸውና የጸጥታ ችግሩ አስከፊ የሆኖ አከባቢዎች ላይ ሆኖ ነው ተንጠልጥለው የሚጠባበቁት።
ከሚያንማር ስቃይ አምልጠው ወደተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት መመለሻቸውን በታይላንድ እስር ቤቶች እየጠባበቁ የሚገኙ አፍሪካውያን ቆይታቸውን የሚያራዝም ሌላ ምክንያት አለ። ከታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ ተነስቶ ወደ አፍሪካ ዋና ከተሞች የአየር አገልግሎት የሚሰጠው በዋናነት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። በታህሳስ ወር ላይ የCSNHTV ድርጅት በላከልን መግለጫ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚያንማር ካምፖች ላመለጡት አፍሪካዊ ስደተኞች (ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ) በአንድ በረራ ከሶስት በላይ እንደማያሳፍር ውሳኔ ላይ መድረሱ ገለጸልን። ለዚህ ውሳኔው አየር መንገዱ እንደ ምክንያት የጠቀሰው ደግሞ “የድህንነት ምክንያት” የሚል ነው። አየር መንገዱ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠፍ ፍቃደኛ አልሆነም።
ከ3 በላይ አናሳፍርም በመባላቸው እስር ላይ ያሉት አፍሪካውያን ስደተኞች ተስፋ በመቁረጥ ላይ እንደሚገኙም ሰማን። በኡጋንዳ ሃገር የአንዱ ስደተኛ ቤተሰብን የማነጋገር እድል አግኝቼ ነበር። በሚያንማር ታግቶ 9 ወራት አንድ ካምፕ ላይ አሳልፎ ድብደባና የኤሌክትሪክ ንዝረት ስቃይን አስቃይተውት በህዳር 2018 ተለቆ ወደ ታይላንድ ሲመለስ የታይላንድ ድንበር ሃይል ወደ ስደተኞች እስር ማቆያ ወሰዱት። ታይላንድ ያለው የኡጋንዳ መንግስት ቆንስላ ፓስፖርትህን ከማሳደስ ውጪ ምንም የምናደርግልህ ነገር የለም በማለቱ ቤተሰቡ የአየር ቲኬት ወጪውን ለመሸፈን ከጎረቤትና ከዘመድ ብድር መጠየቅ ጀመረ። በታህሳስ ወር የፈረንጆቹ ገና እየቀረበ በመምጣቱ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቲኬት እየተወደደ መጣና ቤተሰቡ መሬትና ንብረታቸውን መሸጥ ግዴታ ሆነባቸው።
“ወንድሜ ያለበት ሁኔታ አጅግ አስከፊ ነው። እስር ቤቱ ተጨናንቋል ቆሻሻም ነው። እሱ ስንት ስቃይን አይቶ መታከም ሲገባው ስንት የአይምሮ በሽተኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር ነው ቁጭ ያለው። አየር መንገዱ የሚሰራው ስራ ትክክል አይደለም። እንደምንም ብለን ያለንን ሸጠን ገንዘቡን ብንሰበስብም አሁን ባስቀመጡት ኮታ ምክንያት የበረራ ቦታ መቼ እንደሚገኝም የሚታወቅ ነገር የለም።”
_______________________________________________________________________
ታይላንድ ወይ ካምቦዲያ ጥሩ ስራ አግኝቻለሁ የሚሏችው ቤተሰብ ወይ ጓደኛ ካለ እባካችሁ ስላለው አደጋ ያለውን መረጃ አዳርሱ! ጦርሜዳ ወደሆነችው ሚያንማር ማንም እንደማይመጣ ስለሚያውቁ እስከ ባንኮክ ድረስ ቲኬት ቆርጠው ነው ደላሎቹ በመኪና ከኤርፖርት ተቀብለዋቸው ወደ ሚያንማር የሚወስዷቸው። ከሚያንማርና በአጎራባች የደቡብ ምስራቅ እስያ ሃገራት ላይ በሚመራው የህገወጥ የሰዎች ዝውውርና የሳይበር ብዝበዛ ወንጀሎች የቻይና ማፊያ ቡድኖች በዓመት ከ40 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያተርፉ የተመድ ይገምታል።
ሙሉ ዘገባው “Africans are being confined and beaten in scam camps in Myanmar” ጋዜጣውን በ5$ በመግዛት (ካናዳ ላላችሁ) ወይም በግሎብ ኤንድ ሜል ድረ ገጽ ላይ ያገኙታል።
-ዘካሪያስ ዘላለም።