የካቲት ፲፪፡ የኢትዮጵያ ሰማዕታት ቀን!!

የካቲት ፲፪፡ የኢትዮጵያ ሰማዕታት ቀን!!
በመምህር ጌታቸው በቀለ
የካቲት ፲፪፡ የኢትዮጵያ ሰማዕታት ቀን ዘንድሮ 89ኛ ዓመቱ ላይ ነው።
የካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም በአዲስ አበባና አካባቢዋ ውስጥ ብቻ ወደ 30 ሺህ ኢትዮጵያውያን ተጨፍጭፈው ተገድለዋል።ይህ ዕለት ኢትዮጵያውያን በተለያየ ዝግጅቶችና ፕሮግራሞች በግፍ የተገደሉ ሰማዕታትን ያስባሉ፡፡
ከአርባ አንድ ዓመታት በኋላ ተመልሶ ለወረራ የመጣው በማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ የሚመራው የፋሺስትም ጦር፣ ከየካቲት ፲፪ ቀን እስከ የካቲት ፲፬ ድረስ ባሉት ሦስት ቀናት ከሠላሳ ሺህ በላይ ሰላማዊ ኢትዮጵያውያንን ገደላቸው። በዕለቱ የጣሊያናዊው ኔፕልስ ግዛት መሥፍን ሴት ልጅ ስለተወለደችለት ፌሽታ በማድረግ የአዲስ አበባ ድኾችንና ነዳያንን ሕጻናትንና ልጆችንም ይዘው እንዲገኙ ተደርጎ ነበር፤ የገንዘብና የሌሎችም ዕርዳታ ስለሚደረግ፣ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ (የዛሬው 6 ኪሎ ዋና ዩኒቨርሲቲ ግቢ) እንዲገኝ ተጠርቶ ነበር። ዕርዳታ ሳይጀመር፣ አጋጣሚውን በመጠቀም በተነሣው ዐመጽ የግድያ ሤራውን አሢረው ሲዘጋጁ የነበሩት ወጣቶች፣ የያዟቸውን ቦንቦች በመወርወር፣ ግራዝያኒና በወቅቱ አብረው ከከነበሩት ጥቂት ሰዎች ቆሰሉ። በተነሣው ዐመጽ ብዙ ኢትዮጵያውያንን እልቂት ምክንያት የሆነበት ዕለት ነው፡፡
ይህን ሙከራ ተከትሎ ለሦስት ቀናት ያህል የቆየ የጅምላ ጭፍጨፋና አፈሳ ዘመቻን ዐወጀ፡፡ በዚህም ከከተማዋ ነዋሪዎች በተገኘው መሣርያና መግደያ ተገደለ። አረጋውያንን፣ ሕፃናትን እና ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ፣ በአካፋና በዶማ፣ በጠመንጃዎችና በሽጉጦች፣ በካሚዮኖች በመጎተትና በላያቸው ላይ በመንዳት፣ ወ.ዘ.ተ ተገደሉ። ሸሽተው ቤታቸው መግባት የቻሉትና ከቤታቸው ያልወጡትን በላያቸው ላይ በመዝጋት እሳት ለኮሱባቸው።
አዲስ አበባ ውስጥ ስድስት ኪሎ ቆሞ የሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት የካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም በይፋ ማክበር የተጀመረው በ፲፱፻፴፬ ዓ.ም ነው። የሰማዕታት ሐውልት የካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት ያኽል በፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች ለተጨፈጨፉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መታሰቢያ ይኾን ዘንድ የቆመ ሐውልት ነው። በየካቲት በ፲፱፻፴፬ ዓ.ም ሙሉ ሥራው ተጠናቅቆ የተመረቀው ይህ ሐውልት የፋሺስቱን ግራዚያኒ የጭካኔ ድርጊት “ለዓለም እንዲናገር፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እንዲያስቡት” ተብሎ የተሠራ ነው፡፡
ዋቤ መጻሕፍት
✍️ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም
✍️ የኢትዮጵያ ታሪክ
✍️ የቤተክርስቲያን ታሪክ በኢትዮጵያ