የሟቿ የቀዳማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ሁለተኛ ልጅ እና የንጉሥ ቻርለስ ሳልሳዊ ታናሽ ወንድም አንድሪው ማውንትባተን-ዊንድሶር ከሕፃናት ወሲባዊ ጥቃት ወንጀል ፈፃሚው ጄፍሪ ኤፕስታይን ጋር በነበራቸው ግንኙነት ላይ በፖሊስ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ነው በቅጥጥር ስር የዋሉት። አንድሪው ከዚሁ ወንጀል ጋር ባላቸው ግንኙነት የልዑልነት ማዕረጋቸው ቀደም ሲል እንዲነሳ ተደርጎ ነበር።
ዛሬ ሐሙስ ከጠዋቱ 2 ሰዓት በኋላ በሳንድሪንግሃም ግዛት ዉድ ፋርም ውስጥ ምልክት የሌላቸው የፖሊስ መኪኖች እና ሲቪል የለበሱ የፖሊስ መኮንኖች ፎቶግራፎች መታየታቸውን ዘገባዎች ያሳያሉ።
የቀድሞው ልዑል አንድሪው ማውንትባተን-ዊንድሶር፤ ከሦስት ሳምንት በፊት ከሚኖሩበት የዊንድሶር ቤተመንግሥት እንዲለቁ ተደርገው በዉድ ፋርም ውስጥ ሮያል ሎጅ በሚባለው አነስተኛ መኖሪያ ውስጥ ነበሩ። ፖሊስ በመንግሥት ቢሮ ውስጥ በሥነ ምግባር ብልሹነት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውም በዚሁ መኖሪያቸው ነው።
ቀደም ሲል ኤፕስቲንን ከከሰሱ ሴቶች አንዷ የሆነችው ቨርጂንያ ሮበርትስ እንዳለችው ከልዑል አንድሪው ጋር ወሲብ እንድትፈጽም የተገደችው በ17 ዓመቷ ነበር። የ66 ዓመቱ አንድሪው ማውንትባተን-ዊንሰር የቀረበባቸውን ክስ እና ጥፋት ሲክዱ ቆይተዋል። በማስረጃነት የቀረበባቸውን ከእሷ ጋር የተነሱትን ፎቶም እንደማያስታውሱ ገልጸዋል። የኤፕስታይን ፋይሎች በአሜሪካ የፍትህ መምሪያ በቅርቡ ይፋ ሲሆኑ ግን ለዓመታት የተዳፈኑት ክሶች እንደገና እንዲንቀሳቀሱ ሆነዋል።
ልዑል አንድሪው የቀረበባቸውን የወሲባዊ ብዝበዛ ክስ በጎርጎሪዮሳዊው 2022 ላይ ሚሊዮኖች ለመክፈል በመስማማት አልፈዋል የሚል ክስም ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
በሕጻናት የወሲብ ንግድ ፣ ጾታዊ ጥቃት እና በሌሎች አካላዊ ጥቃቶች የተከሰሰው አሜሪካዊው ጀፈሪ ኤፕስቲን በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረ ሲሆን፤ በእስር ቤት እያለ ራሱን ማጥፋቱ ይፋ ሆኗል።
በኤፕስቲን ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ክስ እና ከኤፕስቲን ጋር ትስስር ያላቸው ሰዎች ዝርዝር መውጣት ግን አሁንም ቀጥሏል።