ኦነግ፣ ‘በአገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጦርነት ደመና አንዣቧል’ ሲል ስጋቱን ገለጠ

ኦነግ፣ ‘በአገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጦርነት ደመና አንዣቧል’ ሲል በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት ባወጣው መግለጫ ስጋቱን ገለጠ።

ኦነግ፣ ከፊት ለፊት እየመጣ ነው ላለው “ጥፋት” መንግሥት አጽንዖት ሠጥቶ በመመልከትና ችግሮችን ከኃይል ይልቅ እውነተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር በማድረግ አገሪቷን ከጥፋት ሊታደጋት ይገባል ሲል ጥሪ አድርጓል።

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ይስተዋላል ያለው የጦርነት አደጋ በእጅጉ እንዳሳሰበው የጠቀሠው ኦነግ፣ የአገሪቱና የሕዝቦቿ የደኅንነት ሁኔታም ከእለት እለት ፈተና ውስጥ እየገባ ይገኛል ብሏል።

ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የውጭ ኤምባሲዎች፣ ዲፕሎማቶች እንዲሁም የፖለቲካ ሰዎች በአገሪቱ የተከሠተው “ውጥረት” በሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚፈታበትን መንገድ እንዲያፈላልጉ ኦነግ በዚሁ መግለጫው ጠይቋል።