ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ በውጭ ምንዛሬ ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችል ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርድ ማግኘት ተፈቀደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ (አካውንት) ያላቸው ደንበኞች የቪዛ እና የበረራ ትኬት ማቅረብ ሳይጠበቅባቸው ለዓለም አቀፍ የበይነ መረብ (ኦንላይን) ግብይቶች የሚውል የውጭ ምንዛሬ ክፍያ ካርድ እንዲያገኙ ፈቀደ። የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ ለመክፈት ተቀምጦ የነበረው የ100 ዶላር የግዴታ ተቀማጭ ገንዘብም እንዲቀር ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትናንት ረቡዕ የካቲት 4/2018 ዓ. ም. የውጭ ምንዛሬ መያዝ፣ ማግኘት እና መጠቀምን በተመለከተ የተቀመጡ ገደቦችን ይበልጥ ያላላ ማሻሻያ ይፋ አድርጓል። ብሔራዊ ባንክ አዲሶቹን ለውጦች ይፋ ያደረገው በሐምሌ 2016 ዓ. ም. በወጣው የውጭ ምንዛሬ መመሪያ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ነው።

አረንጓዴው መጽሐፍ በመባል የሚጠራው ይህ መመሪያ የወጣው በሐምሌ 2016 ዓ. ም. የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊ መሆን ሲጀመር ነበር። መመሪያው የውጭ ምንዛሬ ከመንግሥት ተመን ወጥቶ ገበያ መር እንዲሆን ያስቻለ መሆኑም ይታወሳል።

አሁን የተደረገው ማለውጥም ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎ በውጭ ምንዛሬ ላይ የተደረጉ ለውጦች አካል እንደሆነ ብሔራዊ ባንክ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። አዲሶቹ ማሻሻያዎች “የውጭ ምንዛሬ ገበያን የበለጠ ለማጎልበት በማሰብ” ተግባራዊ እንደሆኑም ገልጿል።

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ባንኮች እና የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶችን መስጠት የሚችሉት ወደ ውጭ ለሚጓዙ ደንበኞቻቸው ነበር። የውጭ ምንዛሬ የሚጫንበትን ይህንን ካርድ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎችን የውጭ ጉዞ ትኬት እና ቪዛ ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር።

ይህም ኢትዮጵያውያን ከዓለም አቀፍ የበይነ መረብ (ኦንላይን) የግብይት መድረኮች እቃዎችን እንዳይሸምቱ ወይም የሚፈልጓቸው አገልግሎቶች ለማግኘት የደንበኝነት ምዝገባ (subscription) እንዳይፈጽሙ አድርጓቸው ቆይቷል።

ብሔራዊ ባንክ ትናንት ይፋ ባደረገው ማሻሻያ ዓለም አቀፍ ካርድ ለማግኘት ተቀምጦ የነበረውን የውጭ ጉዞ ቅድመ ሁኔታ አንስቷል።

ባንኮች ለደንበኞቻቸው “በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ካርዶችን እንዲያወጡ እና በሒሳብ ባለቤቱ ጥያቄ መሠረት የቪዛ እና የጉዞ ትኬት ሳያስፈልግ የውጭ ምንዛሬ እንዲጭኑ” እንደተፈቀደላቸው አዲሱ መመሪያ ያስረዳል።