በመቐለ ከተማ የፈንጂ ፍንዳታ ተከስቶ ነበር

የመቐለ ነዋሪ ተረጋግቶ አካባቢውን እንዲጠብቅ ጥሪ ተላለፈ።

በመቐለ ከተማ ዛሬ የካቲት 5/2018 ዓ.ም ከምሽቱ 3:30 ሰዓት አከባቢ የፈንጂ ፍንዳታ ተከስቶ ነበር።

በሰው እና በንብረት ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም ተብሏል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ መቐለ የተመለከተውና የከተማው ሰላምና ፀጥታ ፅ/ቤት ለመቐለ ኤፍ ኤም በሰጠው መረጃ፣ ምሽት 3:30 አካባቢ በዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ መቐለ ዩኒቨርስቲ ዓዲ ሓቂ ካምፓስ ዙሪያ የፈንጂ ፍንዳታ ተከስቶ ነበር።

በፍንዳታው የሰውም ይሁን የንብረት ጉዳት እንዳልደረሰ ተገልጿል።

” የፈነዳው ፈንጂ የመቐለ ከተማን ሰላምና ጸጥታ ለማናጋትና ሕዝቡን ለማሸበር ዓላማ ባላቸው የጥፋት ኃይሎች ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው ” ያለው ፅ/ቤቱ ” ጥቃቱ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ያደረሰው ምንም ዓይነት ጉዳት ባይኖርም፣ በፍንዳታው ድምፅ በርካታ ሕዝብ ተደናግጧል ” ሲል ገልጿል።

” ፍንዳታው የመቐለ ሕዝብን ለማሸበርና የየካቲት 11 በዓል በሰላም እንዳይከበር በሚፈልጉ ተላላኪዎች ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው ” ሲልም አክሏል።

” ከወራት በፊትም በተመሳሳይ ቦታ መሰል የሽብር ተግባር ተፈጽሞ ነበር ” ሲል አስታውሷል።

” ይህንን ድርጊት የፈጸሙ ፀረ-ሕዝብ ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የመቐለ ከተማ ፖሊስ ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በትኩረት እየሰራ  ነው ” ብሏል።

ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ አካባቢውን መጠበቅ እንዳለበት ያሳሰበው ፅ/ቤቱ ” ስለ ፍንዳታው አፈጻጸም እና ስለ ፈጻሚዎቹ የሚመለከት ዝርዝር ማጣራት ተጠናቆ ሲያልቅ ይፋ ይደረጋል ” ሲል አሳውቋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይ ያለው ሁኔታና በሚዲያዎች ላይ የሚፃፈው ሁሉ ነዋሪዎችን በእያንዳንዱ ነገር ስጋት ላይ የሚጥል ሆኗል።

ክልሉ ካለፈው ደም አፋሳሽ ጦርነት ገና ያላገገመ ቢሆንም አሁንም የሚታየው የጦርነት መሰል ድባብ ለነዋሪዎች ጭንቀት እየፈጠረ ነው።