የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለተወሠኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ የክልሉን የባለቤትነት መብት ሠጥቷል

ኢሰመጉ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገመንግስት የሚሻሻልበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠየቀ። የክልሉ ሕገመንግሥት ለተወሠኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ የክልሉን የባለቤትነት መብት ሠጥቷል ያለው ኢሰመጉ፣ ይህ የሕገመንግሥቱ አንቀጽ በክልሉ የሚታዩትን ግጭቶች እና የመፈናቀል ችግሮች አባብሷል ሲል በአገር ዓቀፍ ደረጃ የተፈናቃዮችን ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው ዘለግ ያለ ልዩ ሪፖርት ገልጧል። ኢሰመጉ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተፈናቃዮችን ወደመጡበት አካባቢ የመመለስና ባሉበት አካባቢ የማቋቋም ሃላፊነቱን በካምፓላው የአፍሪካ ኅብረት ስምምነት መሠረት እንዲወጣም ጠይቋል። መንግሥት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የሚመልስ ከኾነ፣ የተፈናቃዮችን “ፍላጎት” እና “ፍቃድ” መሠረት ባደረገ መልኩ “በውይይት”፣ የተፈናቀሉበትን አካባቢ “ሰላማዊነት” በማረጋገጥ እና “ተገቢውን ጥበቃ” በማድረግ እንዲፈጽምም ኢሰመጉ ጥሪ አድርጓል። ኢሰመጉ፣ መንግሥት የተፈናቃዮችን ጉዳይ እና የሕግ ማዕቀፎችን ተፈጻሚነት የሚከታተል ራሱን የቻለ ተቋም እንዲያቋቁም ጭምር ጠይቋል።