ለተከታታይ አራት ቀናት በተደረገ ውጊያ 171 የአገዛዙ ወታደሮች ሙትና ቁስለኛ ተደረጉ!

ለተከታታይ አራት ቀናት በተደረገ ውጊያ 171 የአገዛዙ ወታደሮች ሙትና ቁስለኛ ተደረጉ!

በቋራ ግንባር አባድግሱ ተብሎ የሚጠራው አከባቢን ጨምሮ ጋዝጌ እና ባርባስ እንዲሁም በአዳኝ አገር ጫቆ ደግሞ ነጋዴ ባህር ከተማ አከባቢ ነው ባለፉት አራት ተከታታይ ቀናት ከባድ ውጊያ የተደረገው።

በአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ሰሜን አማራ ቀጠና ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዕዝ ስር የሚገኘው ግዙፉ መይሳው ካሳ ኮር ከጥር 26/2018 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ትናንት ጥር 29/2018 ዓ/ም ረፋድ ድረስ ባደረገው ተጋድሎ የጠላት ብልፅግና ወታደሮችን አከርካሪ በመስበር አንፀባራቂ ድል ማስመዝገቡን መረብ ሚዲያ ከዕዙ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ለማረጋገጥ ችሏል።

ጥር 28/2018 ምሽት ጀምሮ እስከ ትናንት ረፋድ ድረስ በቋራ ወረዳ አባድግሱ ተብሎ በሚጠራው ቀጠና የጠላት ብልፅግና ወታደሮች በፋኖ 360° ድግሪ ተከበው ከባድ የሆነ ሰብአዊና ቁሣዊ ካሳራን ተከናንበዋል።

የፋኖ የማጥቃት አቅም በምን ያህል ደረጃ እንዳደገ በታየበት በዚህ የቆረጣና የከበባ ማጥቃት፡ 36 ወታደሮች ሲገደሉ 45 ወታደሮች ደግሞ ክፉኛ ቆስለው በሞትና በሕይወት መካከል እንደሚገኙ ታውቋል።

በውጊያው ከተገደሉት የአገዛዙ ወታደሮች መካከል የሃምሳ አለቃ ማዕረግ ያለው መስመራዊ አዋጊና ሌሎች የሬጅመንት አመራሮች እንደሚገኙበት ዕዙ በሕዝብ ግንኙነት መምሪያው በኩል የገለፀው።

በዚህ ተጋድሎ አንድ የዶሽቃ አፈሙዝን ጨምሮ 12 ክላሽንኮቭ መሣሪያ እና 650 የክላሽ ተተኳሽ በፋኖ ቁጥጥር ስር ውሏል።

በቀጠናው በተመሣሣይ ጋዝጌ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ልዩ ስማቸው ሮቡዕ ገበያና ኤፈርት ተብለው በሚጠሩ አከባቢዎች በተደረገው ተጋድሎ 30 የፀረ አማራው ብልፅግና ወታደሮች ሲገደሉ ሌሎች 30 ወታደሮች ደግሞ ቆስለው በአከባቢው ወደሚገኝ ጤና ተቋም መወሰዳቸውን ነው መረብ ሚዲያ ከዕዙ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ለማረጋገጥ የቻለው።

በተጋድሎው 10 ክላሽንኮፍ መሣሪያን ጨምሮ ከ3 ሺ በላይ ተተኳሽና ሌሎች ወታደራዊ ግብአቶች በፋኖ ተማርከዋል።

በተመሣሣይ በዚኸው ግንባር ከአባድግሱ ወደ ባርባስ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የአገዛዙ ወታደሮች ላይ በተከፈተ ጥቃት አምስቱ ወዲያውኑ ሲገደሉ 12ቱ ደግሞ መቁሰላቸው ተረጋግጧል።

ከቋራ ወረዳ በተጨማሪ በአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ በተደረገ ተጋድሎ፡ ፋኖ በጠላት ላይ ፈጣን የፀረ ማጥቃት እርምጃ በመውሰድ ይዞታዎችን አስከብሮ ድል ተቀዳጅቷል።

በዚህ ቀጠና ለጠላት መንገድ መሪ በመሆንና የፋኖ ደጋፊ ናቸው በሚል ንፁኋንን በማስገደልና በማሳሰር እኩይ ድርጊት ላይ ተሰማርቶ የነበረ አንድ ባንዳን ጨምሮ አምስት የአገዛዙ ወታደሮች ሲገደሉ፡ ስምንቱ ደግሞ ቆስለዋል፡ አምስት ክላሽንኮፍ መሣሪያ ከነ ተተኳሹ በፋኖ ቁጥጥር ስር ውሏል።

በበላይ ዘለቀ ዕዝ ስር የመይሣው ካሳ ኮር ሰራዊት ከጥር 26/2018 ዓ/ም ጀምሮ በቋራ እና በአዳኝ አገር ጫቆ ግንባር ላለፉት አራት ቀናት ባደረገው ተጋድሎ በድምሩ 76 የአገዛዙ ወታደሮችን ሲገድል፡ 95 ወታደሮችን ደግሞ ማቁሰሉን ነው ጣቢያችን መረብ ሚዲያ ከዕዙ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ለማረጋገጥ የቻለው።

በተጋድሎው ሙትና ቁስለኛ እንዲሁም ምርኮኛ ከተደረጉ ወታደሮች በተጨማሪ አንድ የዶሽቃ አፈሙዝ እና 27 ክላሽንኮቭ መሣሪያ፣ 4ሺ የሚደርስ ተተኳሽና ሌሎች ለትግሉ ግብአት የሚሆኑ ወታደራዊ ቁሳቁሶች በፋኖ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

አገዛዙ በቀጠናው የኔትዎርክና የመብራት አገልግሎቶችን በማቋረጥ በበርካታ ከባባድ መሣሪያዎች ታግዞ ተኩስ የከፈተ ቢሆንም፡ ነገር ግን ከወደ ፋኖ የተወሰደበትን አፀፋዊ የፀረ ማጥቃት እርምጃን መቋቋም አቅቶት ቆሞ መዋጋት እስኪያቅተው ድረስ ተሽመድምዶ ቀጠናውን ለቆ ወጥቷል።