በ7ኛው ዙር ምርጫ ተሳትፎየን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ (ደሳለኝ ጫኔ ዳኜው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል )

በ7ኛው ዙር ምርጫ ተሳትፎየን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ለተከበራችሁ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች፣ ለመላው የአማራ ሕዝብ እና ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ፦

ባለፉት ዓመታት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በኩሩው የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ተመርጨ፣ እናንተን ወክዬ፣ ለሕዝባችን ሀቀኛ ድምፅ በመሆን ለማገልገል በመቻሌ ታላቅ ክብርና ኩራት ይሰማኛል። በዚህ ጉዞዬ ላሳያችሁኝ ያልተቆጠበ ድጋፍ፣ ፍቅር፣ አክብሮት እና ጽኑ እምነት ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

በአሁኑ ወቅት ለ7ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ የእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እየተከናወነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በመራጮቼ፣ ደጋፊዎቼ እና በሚዲያዎች ዘንድ በዕጩነት መመዝገብ አለመመዝገቤን በተደጋጋሚ ስጠየቅ ቆይቻለሁ። አንዳንድ ፓርቲዎችም ባሕር ዳርም ሆነ አዲስ አበባ በፈለግሁበት ቦታ በእጩነት እንድቀርብ እድሉን ሰጥተውኝ ነበር። በግልም የመወዳደርን አማራጭ በጥልቀት አስቤበታለሁ።

ሆኖም ግን በመጪው 7ኛው ዙር ምርጫ ራሴን በዕጩነት ላለማቅረብ መወሰኔን ለሕዝቤ ይፋ ማድረግ እፈልጋለሁ። ለዚህ ውሳኔ ያበቃኝ ዋነኛው ምክንያት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ካለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። ነፃ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ መደላድል አለመኖሩ እና በፖርላማ ውስጥ ተጨማሪ 5 ዓመታትን በመቆየቴ ለህዝቤ የሚያበረክተው የረባ ጥቅም የሌለው መሆኑንም ተረድቻለሁ። ስለዚህ የ6ኛው ዙር ፓርላማ እስኪጠናቀቅ ድረስ ባሉት ጥቂት ወራት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደራሴነት ስራየን ቀጥየ ሰኔ መጨረሻ ላይ የዚህን ዙር የአገልግሎት ዘመኔን የማጠናቅቅ ሲሆን፤ ወደፊት ሀገሬን እና ህዝቤን እንዴት ለማገለግል እንደምፈልግ የማሳውቅ ይሆናል።

እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በጽናት አብራችሁኝ ለቆማችሁ ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼ፣ ውድ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች፣ ለአማራ ሕዝብና ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ምስጋናዬ የላቀ ነው።

እግዚአብሔር ይባርካችሁ፣ ህዝባችንን እና ሀገራችንም ይጠብቅልን!

ደሳለኝ ጫኔ ዳኜው
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል