በእነ ዶ/ር ወንድ ወሰን አሰፋ መዝገብ ከተከሳሾች መካከል 6 ሰዎች ከ3 ዓመት ገደማ የግፍ እስር ቆይታ በኋላ በነጻ ሲሰናበቱ ለሁለት ሰዎች ብቻ የአንቀጽ መሻሻል ተደርጎላቸዋል ።
በእነ ዶ/ር ወንድ ወሰን አሰፋ መዝገብ በሽብር ወንጀል ተከሰው ጉዳያቸውን በፌደራል ማ/ቤት ሆነው እየተከታተሉ ከሚገኙ 23 ተከሳሾች መካከል 6 ሰዎች ከ3 ዓመት ገደማ የግፍ እስር ቆይታ በኋላ በነጻ ተሰናብተዋል።
ጉዳዩን የሚከታተለው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ከብዙ ቀጠሮ በኋላ ጥር 28/2018 እንደተለመደው በፕላዝማ በዋለው ችሎት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃል እና የግራ ቀኙን የሰነድ ማስረጃ አስተያየትን ከመረመረ በኋላ ብይኑን በንባብ አሰምቷል።
በዚህም መሰረት ፍ/ቤቱ ከተከሳሾች መካከል፦
1) አርቲስት ዮርዳኖስ አለሜ ፣
2) ተስፋዬ መኩሪያ ፣
3) ቢሰጥ ተረፈ ፣
4) ዳዊት እባቡ ፣
5) ማስረሻ እንየው እና
6) አብርሃም ጌትነትን በነጻ አሰናብቷል።
በተያያዘም የሁለት ተከሳሾችን ማለትም ፦
1) የዶ/ር ሲሳይ አውግቸው እና
2) ሞላልኝ ሲሳይ የተከሰሱበት የፀረ ሽብር አንቀጽ 3 (2) የተሻሻለላቸው መሆኑን ችሎቱ አስታውቋል።
ዶ/ር ሲሳይ ወደ አንቀጽ 9 (1) የተሻሻለለት ሲሆን ሞላልኝ ሲሳይ ደግሞ ከሕገ ወጥ መሳሪያ ጋር ተያይዞ ክሱ ከሽብር አንቀጽ እንዲወጣ የተደረገ መሆኑ ተሰምቷል።
የክስ አንቀጹ የተሻሻለላቸው የዋስትና ክርክር የሚያደርጉ ሲሆን እንዲከላከሉ የተባሉ ተከሳሾች ደግሞ ከሚያዚያ 26/2018 እስከ ግንቦት 30/2018 ተከላካይ ምስክሮችን አቅርበው እንዲያሰሙ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
በሌሉበት የተከሰሱትን ጨምሮ በቅርቡ ከጫካ የአማራ የሕልውና ትግል ተመልሰው በብልጽግና አገዛዝ ትዕዛዝ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ኮሎኔል ፈንታሁን ሙሀባም ይከላከሉ ሲል ፍ/ቤቱ ወስኗል።