ሁቲዎች በየመን የኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ እና የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያናትን መዝጋታቸውን ምዕመናን ተናገሩ

 

በሰነዓ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዘማሪያን

የፎቶው ባለመብት, Abreham

የምስሉ መግለጫ, በሰነዓ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዘማሪያን

በየመን ሰነዓ በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እና ወንጌላውያን አማኞች ከሃያ ዓመታት በላይ ሲገለገሉባቸው የቆዩ ቤተ እምነቶችን በሁቲ ባለሥልጣናት ከታሸጉ አንድ ወር እንደሞላቸው የእምነቱ ተከታዮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በየመን ሰነዓ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ያገለግሉ እንደነበር የተናገሩት አቶ አብርሃም በቀለ አምልኮ የሚያካሂዱበት እና ልጆቻቸውን አማርኛ የሚያስተምሩበት ቤተክርስቲያን በሁቲ ባለሥልጣናት የገና በዓል ሰሞን መታሸጉን ገልጸዋል።

በአገሪቱ ዋና ከተማ ሰነዓ ከ23 ዓመት በላይ የኖሩት አቶ አብርሃም ቤተ ክርስቲያኑ ከመዘጋቱ በፊት ዘረፋ እንደተፈጸመ ጠቅሰው፤ ተከትሎ ደግሞ 25 ዓመታት የቆየው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከገና በዓል በኋላ ታሽጓል ብለዋል።

በሰነዓ ከሐያ ዓመታት በላይ መኖሯን የተናገረች የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይም እንዲሁ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በተጨማሪ ቪክቶር በሚባል ሕንዳዊ ከ25 ዓመት በፊት የተቋቋመ እና ኢትዮጵያውያን የወንጌል አማኞች የሚያመልኩበት ስፍራ መታሸጉን፣ ግለሰቡም በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጻለች።

የሁቲ አማፂያን ከኢትዮጵያውያኑ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በፊት በፓስተር ቪክቶር የሚመራውን የወንጌላውያን ቤተ እምነትን ማሸጋቸውን የምትናገረው ግለሰቧ መጽሐፍ ቅዱሶችን እና አንዳንድ ቁሳቁሶችንም መውሰዳቸውን ጨምራ ተናግራለች።

የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆኑት አቶ አብርሃም በቀለ በበኩላቸው ከሦስት ሳምንት በፊት የሁቲ ባለሥልጣናት ወደ ቤተክርስቲያኒቱ በመምጣት “ገንዘብ እና ንብረት ላይ ዘረፋ ፈጽመው” እንደነበር አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስር የሚተዳደረውን የሰነዓ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ከ25 ዓመታት በፊት የቀድሞ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባላት እንደመሠረቱት አቶ አብርሃም ይናገራሉ።

ቤተክርስቲያኑ መጀመሪያ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ እንደነበረ እንደሚነገር የገለጹት አቶ አብርሃም፣ በኋላ በሰነዓ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በሰነዓ ሃዳ አካባቢ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ለእምነቱ ተከታዮች የተለያዩ አገልግሎቶችን ይሰጥ የነበረ ሲሆን “በቤተክርስቲያኑ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ልጆችን ጭምር እየመጡ አማርኛ ይማሩ ነበር” ብለዋል።

ቤተክርስቲያኑ የሚገኝበት ግቢ በወር 2000 ዶላር የሚከፈልበት እንደነበር የተናገሩት አቶ አብርሃም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማም ተሰቅሎ ይውለበለብ እንደነበር ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ወደ የመን ሰነዓ ተልከው የሚያገለግሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች የነበሩ መሆኑን የተናገሩት አቶ አብርሃም፤ አሁን ግን በተለያዩ በዓላት ወቅት ከአዲስ አበባ የሃይማኖት አባቶች በመደወል በስልክ ቡራኬ በመስጠት እንደሚያገለግሏቸው ተናግረዋል።

ቤተ እምነቶቹ ከዚህ ቀደም በየመን መንግሥት ዕውቅና መመሥረታቸውን የሚናገሩት ኢትዮጵያውያኑ በተለይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እስከ ገና በዓል ድረስ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ አገልግሎት ይሰጥ ነበር ብለዋል።

አሁን ሰንደቅ ዓላማው ወርዶ የግቢው በር መታሸጉን የሚገልጽ ወረቀት መለጠፉን ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ላይ አምስት ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሚያመልኩበት ስፍራ እንደነበር የተናገሩት አቶ አብርሃም፤ አሁን ግን “እዚህ ማምለክ አይቻልም” በሚል መታሸጉን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያኑ የክርስትና እምነት ተከታዮች የሚያመልኩባቸውን ቤተ እምነቶች ስለታሸገበት ምክንያት ከሁቲ ባለሥልጣናት በይፋ የተሰጠ ነገር የለም።

ሰነዓ የእርስ በርስ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሰነዓ የእርስ በርስ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት

ቢቢሲ ያነጋገራት ኢትዮጵያዊቷ የወንጌል አማኝ በፓስተር ቪክቶር የተቋቋመው ቤተክርስቲያን በሁቲ ባለሥልጣናት ወረራ ከተፈጸመበት በኋላ ለራሷም ደኅነንት እንደሰጋች ገልለጻች።

“እኔ ራሴ ፈርቼ ነው ያለሁት። የምኖረው ቀድሞ ፓስተር ይኖርበት በነበረ ቤት ውስጥ ነው። የኳየር ልብሶች እና ሌሎች የቸርች እቃዎች እኔ ጋር አሉ።”

ፓስተር ቪክቶር በሚመራት እና 25 ዓመት የቆየች ናት የተባለችው ቤተ እምነት ውስጥ እስከ 400 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የወንጌል አማኞች ያመልኩ እንደነበር የምትናገረው ኢትዮጵያዊት፣ ሌሎች የኢትዮጵያውያን ወንጌላውያን ቤተ እምነቶችም በፍርሃት የተነሳ አገልግሎት ማቋረጣቸውን ትናገራለች።

በየመን ሰነዓ፣ ሐሰር በሚባል አካባቢ በሚገኘው የወንጌላውያን አማኞች ቤተክርስቲያን ዘወትር አርብ እንደሚያመልኩ የምትገልጸው ግለሰቧ የፓስተር ቪክቶር ቤተ እምነት ግን በየዕለቱ ምሽት 11 ሰዓት ጀምሮ የፀሎት እና የአምልኮ ሥርዓት እንደሚያካሂዱ አብራርታለች።

መጋቢ ቪክቶር በየመን ከባለቤታቸው እና ከልጃቸው ጋር አንደሚኖሩ እና በቤተ እምነታቸው ውስጥ ኢትዮጵያውያን ብቻ እንደሚያመልኩ የምትናገረው የቤተክርስቲያኑ ተገልጋይ በተወሰነ ጊዜ መጠነኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያድርጉም ትጠቅሳለች።

እስከ ገና በዓል ድረስ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት ቤተ እምነቶችን ባለሥልጣናቱ በድንገት ለማሸግ ለምን እንደፈለጉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች መረጃው አንደሌላቸው ተናግረዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ታቦት ከሁቲዎች ጋር ባላንጣ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ በ2015 በሁቲ አማፂያን ላይ የተጠናከረ የአየር ድብደባ በምትፈጽምበት ወቅት ወደ ሌላ ስፍራ መወሰዱን የተናገሩት አቶ አብርሃም፤ ከዚያ ውጪ ማንኛውንም ክብረ በዓል በድምቀት በግቢው ውስጥ ያከብሩ እንደነበር ገልጸዋል።

የሁቲ ባለሥልጣናት ከሦስት ሳምንታት በፊት ቤተክርስቲያኒቱን ባሸጉበት ወቅት በስፍራው በቋሚነት እያገለገሉ የነበሩ አንድ ካህን እንደነበሩ አቶ አብርሃም ገልጸው፤ ባለሥልጣናቱ አገልጋዩን በማስጠራት ቤተ እምነቱን አሽገውታል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ታቦቱ ባይኖርም የተለያዩ ክብረ በዓሎች ይከበሩ እንዲሁም ለሕጻናት አማርኛ እንዲማሩ ይደረግ እንደነበር ተናግረዋል።

“በዚህ ዓመት ጥምቀት አላከበርንም” ያሉት አቶ አብርሃም ከመታሸጉ በፊት ግን ለመስቀል ደመራ እንዲሁም ከገና በዓል በኋላ ጥምቀት እንዲሁም ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በድምቀት ይከበሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስሪያን የእምነት ሥርዓት እንዲሁም የኢትዮጵያ ባሕል እና ታሪክ ላይ ትምህርት አንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የኦርቶዶክስ እምነት እንዲሁም የወንጌል አማኞች በአሁኑ ወቅት የሚያመልኩበት ስፍራ እንደሌለ እና በፍርሃት ውስጥ እንደሚኖሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ በኢትዮጵያውያን ቤተ እምነቶች ላይ የተወሰዱትን የመዝጋት እርምጃዎችን በተመለከተ ከሁቲ ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት የሚመለከታቸውን አካላት ለመለየት እና ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የመን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከመግባቷ በፊት በርካታ ኢትዮጵያውያን ለሥራ የሚያመሩባት አገር የነበረች ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና ወደ ሌሎች አረብ አገራት ለመግባት ኢትዮጵያውያን እንደ መተላለፊያነት ይጠቀሙባታል።

በአሁኑ ወቅትም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት መጀመሪያ ላይ በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ደርጅት የተመዘገቡ ከ16 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን አሉ።

በከዚህ ተጨማሪም በየመን ውስጥ ያልተመዘገቡ እና በአገሪቱ ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ይታመናል።