‘በጥቁር ገበያ ነጋዴዎች’ እጅ የወደቀው የትግራይ ክልል የነዳጅ አቅርቦት

በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ነዳጅ የሚፈልግ ባለ አሽከርካሪ ዐይኖቹን የሚያማትረው በነዳጅ ማደያዎች ላይ አይደለም።

ከዚያ ይልቅ ነዳጅ በጄሪካን እና በፕላስቲክ የውሃ ማሸጊያዎች የሚሸጡ ወጣቶች ጋር ነው የሚሄደው። እነዚህ ነጋዴዎች ናቸው ገበያውን የተቆጣጠሩት።

ነዳጅ በጥቁር ገበያ ዋጋ የሚሸጡ ወጣቶች በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ዛፎች ስር ተቀምጠው ሸማች ይጠባበቃሉ።

የከተማዋ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ከእነዚህ ወጣቶች መንግሥት 110 ብር እንዲሸጥ ዋጋ የቆረጠለትን ነዳጅ በሊትር ከ220 ብር እስከ 250 ብር እንደሚገዙ ይናገራሉ።

በትግራይ መዲና መቀለ መሃል የሚገኙ በርካታ የነዳጅ ማደያዎች ባዶ ከመሆናቸው የተነሳ ለመታሰቢያ የቆሙ መስለዋል።

ማደያዎቹን ተከትለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት በሥራቸው የሚገኙ ትናንሽ የገበያ ስፍራዎች ተዘግተዋል።

የዕለቱን የነዳጅ ዋጋ የሚያሳዩት ዲጂታል ስክሪኖች ምንም የሚነግሩት አዲስ መረጃ ስለሌላቸው ቆመዋል።

የመኪና መግቢያ እና መውጫ በሮቻቸው ተዘግተዋል

በአንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች ግቢ ውስጥ ከሰው እና ከመኪና ይልቅ ውርውር የሚሉት ውሾች ናቸው።

የከተማዋን የነዳጅ ፍላጎት የሚያሟሉት በጥቁር ገበያ ላይ ነዳጅ በጄሪካን እና በተለያዩ የፕላስቲክ የውሃ ማሸጊያዎች የሚሸጡት ወጣቶች ናቸው።

ይህ የመቀለ ብቻ እውነታ አይደለም፤ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎችም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

የመቀለ ከተማ ነዋሪዎች ቀደም ሲል የከተማዋ ውበት የነበሩትን የተለያዩ ዕጽዋት ሥራቸው ከጀሪካኖቹ በሚፈሰው ቤንዚን ሲደርቁ እየታዘቡ ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች በክልሉ ውስጥ ያለው መደበኛ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እና የሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር እንዲሁም የነዋሪዎች እንቅስቃሴ እንዲገደብ ማድረጉን ገልጸዋል።

ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ደም አፋሳሽ የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በርካታ የኢኮኖሚ ዘርፎች በወደሙበት ክልል ውስጥ ወጣቶች በመንገድ ዳር ነዳጅ በፕላስቲክ ኮዳ በመነገድ ለራሳቸው ሥራ ፈጥረዋል።

በክልሉ ውስጥ የተከሰተው ከፍተኛ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ግን ለነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ከፍተኛ ኪሳራን ማስከተሉን ነጋዴዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተራውን ማኅበረሰብ ደግሞ ለአላስፈላጊ የዕለት ተዕለት የትራንስፖርት ወጪዎች እና የሸቀጦች ዋጋ መናር እያጋለጠ ነው።

አቶ ጽጋብ ኃይለ በክልሉ ውስጥ ካሉት 70 የሚጠጉ የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ የሁለቱ ባለቤት ናቸው። በመቀለ እና በማይጨው የገነቧቸው ማደያዎች በአቅርቦት እጥረት ምክንያት ከተዘጉ ከአራት ወራት በላይ እንደሆናቸው ይናገራሉ።

“ከ100,000 ሊትር በላይ በመሸጥ ማኅበረሰቡን እያገለገልን ነበር። ከወራት በፊት (ከጂቡቲ) መኪኖች አዘን ነበር፤ በአራት ወራት ውስጥ አንዱም አልመጣም፤ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አላውቅም።”

ከጂቡቲ የሚመጣ ናፍጣ እና ቤንዚን የሚያቀርብ የነዳጅ ማደያ ባለቤት የሆኑት አቶ ጽጋብ፤ ለስምንት ወራት ጠብቀው አንድ ቦቴ ነዳጅ ማይጨው ወደ ሚገኘው ማደያቸው መድረሱን ይጠቅሳሉ።

በዚህም ከ38 በላይ ሠራተኞቻቸው ከሥራ ውጪ እንደሆኑ እና ነዳጅ ለመጫን ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር እንዲከፍሉ እንደሚጠየቁ ጨምረው አስረድተዋል።

አቶ ጽጋብ በነዳጅ አቅርቦት እና በሌሎች ገደቦች ዙሪያ ባሉ ችግሮች ምክንያት የተፈጠረውን ከባድ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሲያስረዱ ተስፋ በቆረጠ ድምጽ ነው።

“እኛ ሥራ ላይ አይደለንም፤ ሥራችን ከባንክ [ብድር] ጋር የተያያዘ ስለሆነ ደግሞ ለባንኩም ሆነ ለሠራተኞቻችን መክፈል አልቻልምንም።”

ነጀጅ በፕላስቲክ ኮዳ

‘የጥቁር ገበያ ነጋዴዎች’

በክልሉ የተካሄደው ጦርነት በኋላ በሰላም ስምምነት ሲያበቃ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ወደ መደበኛ ሁኔታቸው ይመለሳሉ የሚል ጉጉት ነበር።

ምንም እንኳን መሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ ቢጀምሩም፤ በጦርነት የተጎዳው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴም ሆነ የክልሉ አመራር ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት ግን ገና አልጠነከረም።

በዚህም ምክንያት አስተዳደሩ የበጀት እጥረት፣ የተፈናቃዮች አለመመለስ እና ሌሎች ጥያቄዎችን ዘወትር ሲያነሳ ይደመጣል።

ይህ የፌደራል መንግሥት እና የህወሓት አለመግባባት ባለፉት ቀናት የትግራይ እና የአማራ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡበት አካባቢ ወደ ግጭት ተሸጋግሮ ነበር።

ይህንን ተከትሎም ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች ለተከታታይ አምስት ቀናት ተቋርጠው ጥር 26/2018 ዓ.ም. ዳግም ጀምረዋል።

በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስር የሚገኘው የትግራይ ንግድና ኤክስፖርት ኤጀንሲ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለንግድ ሚኒስቴር፣ ለነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን እና ለኢትዮጵያ ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን የነዳጅ አቅርቦት ማነስን የሚመለከቱ ደብዳቤዎችን መጻፉን ይገልጻል።

በመደበኛው ሁኔታ በየወሩ 15 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ክልሉ እንደሚገባ ቢጠበቅም፤ ባለፈው ዓመት ወደ 2.09 ሚሊዮን ሊትር እንደወረደ እና ከጥር 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የትግራይ ንግድ እና ኤክስፖርት ኤጀንሲ ገልጿል።

“ባለፉት አስር ወራት ወደ ትግራይ የሚደረገው የነዳጅ ጭነት በመቆሙ ምክንያት በክልሉ የሚሠሩ የሰብአዊ እርዳታ፡ አምቡላንስ፡ የመድኃኒት ሥርጭት እና የመስኖ ሥራዎች ተቋርጠዋል። የሕዝቡ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ከፋ ደረጃ እያመራ ነው” መሆኑን ኤጀንሲው በደብዳቤው ላይ ገልጿል።

ይህ ሁኔታ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ላይ ሰፊ ቀውስ እየፈጠረ መሆኑን ነዋሪዎች፣ አሽከርካሪዎች፣ የግል ትራንስፖርት ባለሥልጣናት እና “ክፍተቱን ለመሙላት በጥቁር ገበያ ነዳጅ እያቀረቡ” ያሉ ግለሰቦች ተናግረዋል።

በብዙ አካባቢዎች በተጠቃሚዎች ታክሲዎች እና ባለ ሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች ) ባደረጉት የአገልግሎት ዋጋ ጭማሪ ምክንያት አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ማየት የተለመደ ሆኗል።

በባጃጅ ትራንስፖርት ውስጥ የተሰማራው ተስፉ ገብረመስቀል ብዙ አሽከርካሪዎች ነዳጅ አዘውትረው የሚያገኙት በጥቁር ገበያ መሆኑን ይናገራል።

“ከ220 እስከ 250 ብር [በሊትር] እየገዛን ነው የምንጠቀመው። ከየት እንደሚመጣ ስለማይታወቅ፣ የነዳጁ ጥራት በጤናችን እና በንብረታችን ላይ ችግር እየፈጠረ ነው። ሕብረተሰቡ ደግሞ ለነዳጅ በምንከፍለው ልክ እንድናስከፍለው ስለምንገደድ ያማርራል” ሲል ያስረዳል።

የመንግሥት የነዳጅ ዋጋ ተመን 110 ብር አካባቢ ነው። ሆኖም ግን በክልሉ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ አሽከርካሪዎች እንደሚሉት፣ በጥቁር ገበያ ከ220 እስከ 300 ብር እየተሸጠ ነው።

የሰላም አውቶብስ ማኅበር የመቀለ ቅርንጫፍ የባለአክሲዮኖች ኃላፊ አቶ ብርሃነ ከበደ ይህንን ያረጋግጣሉ።

የሕዝብ ትራንስፖርት ኩባንያው በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሽረ እና ወደ መቀለ የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ይሰጣል።

“ባለፉት አራት ወራት ክልሉ የነዳጅ አቅርቦት ችግር ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ገልጾልናል፤ በመሆኑም እኛም እንደ ባጃጅ እና ሚኒባስ በጥቁር ገበያ ላይ ያለውን ነዳጅ እየተጠቀምን ነው። ይህ ማለት ለተጠቃሚዎች የምናስከፍለው ዋጋ ይጨምራል ማለት ነው” ይላሉ።

ነዳጅ ማደያዎች አቅርቦት ስለሌላቸው ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆነዋል
የምስሉ መግለጫ, ነዳጅ ማደያዎች አቅርቦት ስለሌላቸው ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆነዋል

ለጥቁር ገበያው ነዳጅ የሚያቀርበው ማን ነው?

ከትራንስፖርት ዋጋ የጨመረባት ከመቀለ ወደ አዲግራት በመጓዝ ላይ እያለች የቢቢሲ ሪፖርተር ያገኛት መብራት ገብረክርስቶስ ከነዳጅ ማደያዎች ውጪ የሚሸጠው ነዳጅ ከየት እንደሚመጣ ጥያቄ ሆኖባታል።

“በርካታ መንደሮች በፕላስቲክ ኮዳዎች እና ጀሪካኖች የሞሉ ናቸው። ግን የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በአግባቡ መቅረብ ካለበት ቦታ ነዳጅ አያገኙም፤ ይህ ታዲያ ከየት ነው የሚመጣው?”

የአዲግራት ከተማ ነዋሪ የሆነው ሌላ አስተያየት ሰጪ በከተማው ዙሪያ ያሉ የነዳጅ ማደያዎች መዘጋታቸውን ይናገራል።

ሆኖም የረጅም ርቀት መኪና አሽከርካሪዎች ነዳጅ የሚያቀርቡባቸው አጋጣሚዎች እንዳስተዋለ እና ከእነሱ የሚገኘው ነዳጅ በትንሹም ቢሆን ለሕዝቡ እንቅስቃሴ የሚሆን ነዳጅ እንደሚያስገኝ ገልጿል።

“አንዳንዶቹ በተሽከርካሪዎቹ ውስጥ ሞደፊክ ያሰሯቸው ታንከሮች አሏቸው። እነዚህ እስከ 200 ሊትር መያዝ ይችላሉ” ሲል ያስረዳል።

በዚህ መልኩ በሚመጣው ነዳጅ ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ግን እስከ 240 ብር ይደርሳል።

በዚህም ምክንያት ተጠቃሚዎች እንደሚሉት ቀደም ሲል 100 ብር አካባቢ የነበረው የነበረው የአዲግራት-መቀለ መንገድ አሁን 500 ብር እና ከዚያ በላይ ሆኗል።

በመቀለ በፕላስቲክ ኮዳዎች ነዳጅ ከሚሸጡት አንዱ የሆነው ወጣት “ከነዳጅ ማድያው አውጥተው ለእኛ የሚሸጡልን አካላት አሉ። አብዛኛው ጊዜ በሌሊት ነው የሚወጣው። እነዚህ ለእኛ በ210 ብር ይሰጡን እና እኛ ደግሞ እስከ 230 ብር እናጣራዋለን” ይላል።

ቢቢሲ በጥቁር ገበያ የሚሸጠው ነዳጅ የግል ባለሃብቶች ከሚያስገቡት ይሁን መንግሥት ከሚያቀርበው እንደሆነ በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

ነገር ግን ይህ አስተያየት ሰጪ እንደሚለው “በከተማው ውስጥ ነዳጅ የለም የማይሉ አራት የነዳጅ ማድያዎች አሉ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ነዳጅ በኮዳ

የሚመለከታቸው አካላት ምን ይላሉ?

በተለያዩ አጋጣሚዎች የትግራይ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ከሚመለከታቸው የፌደራል አካላት ጋር ለመገናኘት ወደ አዲስ አበባ ማቅናታቸው የሚናገሩት አቶ ጽጋብ “ፖለቲካችሁን አስተካክሉ የሚል መልስ ነው የሚሰጡን” ይላሉ።

በትግራይ ክልል እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ያለው ግንኙነት ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ በተወሰነ መልኩ መሻሻል አሳይቶ የነበረ ቢሆንም፤ በተለይ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ እየተበላሸ እና መካሰስ እየተጨመረበት መጥቷል።

“እኛ ነጋዴዎች ነን፤ ማኅበረሰቡን ነው የምናገለግለው። ግን በዚህ መሃል ተጎድተናል፤ ማኅበረሰቡም እየተሰቃየ ነው። ሕዝቡ ሰሚ ያለው አይመስልም” በማለት በሁኔታው ማዘናቸውን አቶ ጽጋብ ይናገራሉ።

ቢቢሲ ከትግራይ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ጽህፈት ቤት ያገኘው መረጃ በክልሉ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከ70 በላይ የነዳጅ ማደያዎች በሥራ ላይ እንደነበሩ ይገልጻል።

እንደ የክልሉ ባለሥልጣናት ገለጻ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ በውሱን አቅርቦት እና አቅም ሲሠሩ የቆዩት ማደያዎች በአሁኑ ጊዜ ከአገልግሎት ውጪ ናቸው።

የትግራይ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዝዳንት በሪሁ ሃፍቱ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ለአጠቃላይ ምርታማነት፣ አቅርቦት እና የግብይት ሂደት ትልቅ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።

“ከነዳጅ ማደያዎች በቀጥታ ማግኘት ስለማይቻል በኮንትሮባንድ የሚመጣ ጥራቱን ያልጠበቀ ነዳጅ ነው በክልሉ ያለው” በማለት ይህ የትራንስፖርት ዋጋ ላይ ትልቅ ጭማሪ እንዳስከተለ ይናገራሉ።

አክለውም የምግብ እህል እና ሸቀጦች በተገቢው የዋጋ ተመን እንዲጓጓዙ ማድረግ ባለመቻሉ በየዕለቱ የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱንም ያስረዳሉ።

የትግራይ ንግድ እና ኤክስፖርት ኤጀንሲ እንደሚለው ከጦርነቱ በፊት ወደ ክልሉ በወር 10 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ይገባ እንደነበር እና ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ በአማካይ በወር ከ8 እስከ 9 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ይቀርብ ነበር።

የኤጀንሲው ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ካለው የተጠቃሚዎች ፍላጎት አኳያ በወር 15 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ እንዲቀርብ ይጠበቃል።

ሆኖም ለአንድ ዓመት ያህል የታየው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት “ለአጠቃላይ ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እና የክልሉ መልሶ ግንባታ ሥራዎች የሚመጥን አይደለም። ከጥር 2017 ዓ.ም. ጀምሮ አቅርቦቱ እየቀነሰ አሁን ካለበት ደርሷል” ሲሉ የኤጀንሲው ምክትል ኃላፊ አቶ ሃብቶም ፋንታሁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በመጋቢት 2017 ዓ.ም. የክልሉ ሚዲያዎች የኢትዮጵያ የነዳጅ እና የኢነርጂ ባለሥልጣን ችግሩ በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተ መሆኑን በመጠቆም ተስተካክሎ ወደ ክልሉ ነዳጅ እንደሚገባ ዘግበው ነበር።

በወቅቱ በጂቡቲ ‘የነዳጅ ዲፖ ችግር መከሰቱን ተከትሎ የተፈጠረ የሎጀስቲክስ ችግር’ ነው ተብሎ የነበረ ሲሆን የሐረር፣ የጋምቤላ እና የአማራ ክልሎችም በተወሰነ ደረጃ ተመሳሳይ ችግሮች እንደተከሰተ ተገልጿል።

አቶ ሃፍቶም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከፌዴራል ባለሥልጣናት ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፣ ነገር ግን “የመቋረጡን ምክንያት በተመለከተ በጽሑፍ ወይም በሌላ መንገድ መልስ እስክናገኝ ድረስ ምንም ዓይነት ግልጽ መልስ አልተሰጠንም” ሲሉ ተናግረዋል።

ቢቢሲ የፌዴራል የነዳጅ አቅርቦት ድርጅት ዳይሬክተር እስማለም ምህረቱን እንዲሁም ከነዳጅ እና ኢነርጂ ዳይሬክተር በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም።