ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ባጋጠመው የሸንኮራ አገዳ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ከትላንት ሰኞ ጥር 25፣ 2018 ዓ፣ም ጀምሮ ለተከታታይ 45 ቀናት ምርት እንደሚያቆም ተሰማ።
የፋብሪካው አሥተዳደር ከዚህ ቀደም ለስኳር ኮርፖሬሽን ባቀረበው ሪፖርት፣ ዓመቱን ሙሉ ለስኳር ምርት የሚበቃ የሸንኮራ አገዳ ምርት ክምችት እንዳለ አስታውቆ ነበር።
ሆኖም በተያዘው ዓመት አጋማሽ የፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ አቅርቦት ማለቁንና በዚሁ ምክንያት ፋብሪካው ለመጪዎቹ 45 ተከታታይ ቀናት ሥራ ለማቆም መገደዱን እንደተነገራቸው የፋብሪካው ምንጮች አስረድተዋል።
ከ45 ቀናት በኋላ ባሁኑ ወቅት እየለማ ያለው የሸንኮራ አገዳ ለስኳር ምርት እንደሚደርስና ፋብሪካው ዳግም ወደ ሥራ ይመለሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከምንጮቿ ተረድታለች።
ፋብሪካው በተያዘው 2018 የሥራ ዘመን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ለማምረት አቅዶ እንደነበር የጠቀሱት ምንጮች፣ እስካሁን 410 ሺሕ ኩንታል ስኳር አምርቶ ለገበያ ማቅረቡን ገልጸዋል።