የትግራይ ታጣቂዎች ከራያ ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ ሠላማዊ ሰልፍ ተደረገ

ባለፈው ሳምንት በመንግሥት ወታደሮች እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ከራያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች የትግራይ ታጣቂዎች ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ ሠላማዊ ሰልፍ በዛሬው ዕለት በራያ ቆቦ ከተማ አድርገዋል፡፡

ሠልፈኞቹ፣ መንግሥት ደኅንነታቸውን እንዲያስጠብቅላቸው፣ ምርጫ ተደርጎ የራያ ማንነትና የወሠን ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝና በአካባቢው ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው ጥቃትና ወከባ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ተፈናቃዮች በራያ ቆቦ እና ወልዲያ ከተሞች እንዲሁም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን በ10 ሺሕዎች የሚገመቱ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ምንጮች ገልጸዋል።

በቆቦ ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ከቀያቸው ከተፈናቀሉ አንድ ሳምንት እንደተጠጋቸው ገልጠው፣ ኾኖም እስካሁን መጠለያም ሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ ያቀረበላቸው አካል እንደሌለ ቆቦ ነግረውናል።

አብዛኞቹ ነዋሪዎች የተፈናቀሉት፣ በአወዘጋቢ የራያ አካባቢዎች ተሠማርቶ የነበረው የፌደራል መንግሥት ኮማንድ ፖስት ግጭቱ በተቀሠቀሠበት ወቅት ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ነበር።