በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

በአገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 8 ዓመታት በነበሩት ግጭቶች ሳቢያ የጠፋው የሰው ሕይወት፣ የወደመው ንብረትና የተናጋው ማኅበራዊ ትስስር ገና ሳይጠገን አኹን ደግሞ በፌዴራል መንግሥቱና በሕወሓት መካከል ዳግም ጦርነት እያንዣበበ መኾኑ ፓርቲያችንን በእጅጉ ያሳስበዋል።

የ2013ቱ የሚሊዮኖችን ነፍስ ያጠፋው፣ ለአካል ጉዳት የዳረገው፣ ከቀያቸው ያፈናቀለውና በቢሊዮኖች የሚገመት ንብረት ያወደመው ደም አፋሳሽ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢቋጭም አኹንም ዳግም በእንቅፋቱ ሊመታን እየተንደረደርንለት የሚመስለው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማዎች፣ ከባቢያዊ ችግሮችና የኃይል አሰላለፎች ሲታዩ አገሪቱን ወደማታውቀውና ይበልጥ ወደከፋ አዘቅት ውስጥ የሚከቱ አቅም ያላቸው አደጋዎች እንደኾኑ መገመት አያዳግትም።

ስለኾነም፣
1. ኹለቱም ኃይሎች የፖለቲካ ልዩነቶችን በጠመንጃ ለመፍታት መሞከር  የአገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል መኾኑን ተረድተው ከማናቸውም አባባሽ ምክንያቶችና የኃይል እርምጃ እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።

2. የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ሲባል ኹለቱም ኃይሎች ወደ ንግግር እና ድርድር እንዲመጡ እናሳስባለን።

3. ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ችግሩ ከመባባሱ በፊት ተገቢውን ጫና እንዲያደርጉና ለዘላቂ ሰላም የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪያችንን እያስተላልፋለን።

4. ሕዝባችን በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ባገኘው አጋጣሚ ኹሉ ጦርነት በቃኝ እንዲል ጥሪያችንን እናቀርባለን።
እናት ፓርቲ!